በይስሀቅ በላይ
“ክልሎች ወጪያችሁን ችላችሁ ኑ” መባላቸው የአባላት ቁጥር እንዳይቀንስ ስጋትን ፈጥሯል
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈፃሚ
ኮሜቴ ምርጫ አሁንም እልባት
አላገኘም፤ፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ጠቅላላ
ጉባኤውን ጥቅምት 30 እና ኅዳር 1 ቀን
2010 ዓ.ም ቢያከናውንም መሰረታዊና
እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የፕሬዝዳንትና
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን
አስመራጭ ኮሚቴ በጉባኤው ሳይስመርጥ
ጉባኤው ለ45 ቀናት እንዲሁም ሠመራ
ላይ ምርጫው እንዲካሄድ ወስኖ መብተኑ
የሚታወስ ነው፡፡
ዛሬም ድረስ ግለሰቦች ከሀገራቸው
ይልቅ የግል የስልጣን ጥማታቸውን
ለማርካት በቡድን ተደራጅተው
እየተንቀሳቀሱ ያሉበት የዘንድሮው
የፌዴሬሽኑ ምርጫ ውዝግብ ጋብ ከማለት
ይልቅ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
አሁንም በየቦታው የጉባኤው
አባላትን ድምፅ ለማግኘት ከፍተኛ
ገንዘብ እየተረጨና የማባበል ሥራ
እየተሰራ እንደሆነ ጉዳዩን እየታዘቡ
ያሉ ወገኖች እየገለፁ ሲሆን “ሥልጣን
ወይም ሞት” በሚል ምለው ተገዝተው
የተነሱ የሚመስሉ አንዳንድ እጩዎች
ገንዘብ ከመርጨትና ሰዎችን ከማባበል
የዕለት ተዕለት ሥራቸው ወጥተው
በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ እነማን
መካተት አለባቸው? እነማንስ ከህልማችን
ጋር ያገናኙናል በሚል ሌላ ስትራቴጂ
ተጠምደው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ነው
ጉዳዩን እየታዘቡ ያሉ ወገኖች በተለይ
ለዝግጅት ክፍላችን እየጠቆሙ ያሉት፡፡
እነዚሁ የወሬ ምንጮቻችን ጨምረው
እንደሚገልፁት የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ፌዴሬሽን ለፊታችን ሐሙስ ለጠራው
አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተያዘው
ብቸኛ አጀንዳ ማለትም አስመራጭ
ኮሚቴ ምርጫ ላይ እነማንን በምርጫው
ውስጥ ቢካተቱ ከስልጣናችን ያገናኙናል?
በሚልና ይሄን ምኞታችን የሚያሳኩ
አስመራጮችንስ እንዴት ማሰመረጥ
ይቻላል? በሚለው ዙሪያ ከሆቴል ሆቴል
እየቀያየሩ እየመከሩ እንደሆነ ነው ጉዳዩን
የታዘቡ ምንጮች እየገለፁ ያሉት፡፡ ከዚህ
በመነሣት የፊታችን ሐሙስ በሚካሄደው
የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ ላይ ከፍተኛ
ውዝግብና አለመግባባት ሊፈጠር ይቻላል
በሚል ከወዲሁ ሥጋት እንዲያድርባቸው
አድርጓል፡፡
ባለፈው ጥቅምት 30 እና ኅዳር
1 ቀን በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ
በቡድንተኝነትና የግለሰብ አጀንዳን
ለማስፈፅም ከታየው ግብግብና ትንቅንቅ
አንፃር ለፕሬዝዳንታዊውም ሆነ ለሥራ
አስፈፃሚ ኮሚቴነት ምርጫ ወሳኝ ቦታ
ባለው የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ
በቀላሉና በሠላማዊ መንገድ የአስመራጭ
ኮሚቴው ምርጫ ይጠናቀቃል ብሎ
መጠበቅ ከባድ እንደሆነ ነው እነዚህ
አሰተያየት ሰጪዎች እየገለፁ ያሉት፡፡
የፊፋ የምርጫ ኮድ በግልፅ
እንደሚያስቀምጠው በአስመራጭ ኮሚቴ
ውስጥ የሚገቡ አባላት በእጩነት
ያልቀረቡ፣ ከተመራጮች ጋር የጋብቻም
ሆነ የሥጋ ዝምድናና የተለየ ቀረቤታ
የሌላቸው መሆን እንዳለባቸው በግልፅ
የሚደነግግ በመሆኑ የጠቅላላ ጉባኤው
አባላት በዚህ በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄ
ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቀጣዩን
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
ትክክለኛውን ፕሬዚዳንትና ሥራ
አስፈፃሚ በምርጫ መስፈርቱ መሠረት
ለይቶ ለመምረጥ ከባድ ኃላፊነት
እንዳለበት የተጠቆመው አስመራጭ
ኮሚቴው ከምርጫው በኃላ በሚኖራቸው
የሥራ ጊዜ የፊፋን የምርጫ ህግ
ማስከበር እንዳለባቸው ነው እየተነገረ
ያለው፡፡
በፊፋ የምርጫ ሕግ (Election
Code) መሰረት አስመራጭ ኮሚቴው
ዝቅተኛው ሰባት ከፍተኛው ዘጠኝ አባላት
ይኖሩታል ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ
ጠቅላላ ጉባኤው የአስመራጭ ኮሚቴ
አባላትን ቁጥር በዚህ መሠረት መወሰን
ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም
በሐሙሱ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ
ላይ የሚመረጠው አስመራጭ ኮሚቴ
የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ (General
Secretary) ጋር አብረው እንዲሰሩና
ዋና ፀሐፊው የአስመራጭ ኮሚቴው
ፀሐፊ ሆነው የሚሠሩበት ሁኔታ እንዳለ
የሚያስቀምጥ በመሆኑ የፌዴሬሽኑ የጽ/
ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ወንድምኩን
አላዩ ከትናንት ሰኞ ጀምሮ ከኃላፊነት
ራሣቸውን በማግለላቸው ማን ከአስመራጭ
ኮሚቴው ጋር አብሮ ይሠራል? የሚለው
በጥያቄ ውስጥ ያለ ሲሆን ምን አልባት ወ/ት
መስከረም አቶ ወንድምኩን አላዩን ተክታ
ልትሠራ እንደምትችል እየተነገረ ነው፡
፡ እንደ ፊፋ የምርጫ ሕግ ከሆነ የጽ/ቤት
ኃላፊ ከአስመራጭ ኮሚቴው ጋር በኃላፊነት
አብሮ የሚሠራ ሲሆን ምናልባት መስከረም
በቦታው ከተሾመች አስመራጭ ኮሚቴውን
ከማማከር በዘለለ በአስተዳደርና ለምርጫ
ጠቃሚ በሆኑ ሎጀስቲክስ (የዕቃ አቅርቦት)
ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ
ይጠበቃል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ነገ ሐሙስ
ፍፁም ገለልተኛ እና ከማንም ወገንና ቡድን
ነፃ ሆኖ ከተመረጠ በኋላ የፌዴሬሽኑ
ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን ከፊፋ፣ ከካፍና
ከፌዴሬሽኑ ሕጎች ጋር የምርጫ ሂደቱ
የሚጋጭ አለመሆኑን ማጣራት፣ የምርጫ
ሕጉ ሙሉ በሙሉ ስለመከበሩ፣ ምርጫውን
አስመልክቶ ለዋና ፀሐፊው ለህዝቡና ለሚዲያ
መረጃ በየዕለቱ መስጠጠቱን፣ አስፈላጊ በሆነ
ጊዜ ምርጫውን አስመልክቶ ከመንግሥት
ኃላፊዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ ለህዝቡ
የተመራጮችን ማንነትና ስለ እነሱ መረጃ
መሰራጨቱን ማስተዋወቅ፣ እጩዎች
መረጃዎቻቸውን ለፌዴሬሽኑ ሕጋዊ ደረሰኝና
መረጃ ባለው መልዕክት መላኪያ ከ30 ቀናት
በፊት መላካቸውን ማረጋገጥና ከዚህ በኋላ
እጩዎችን በሕጉና በደንቡ በተለይም የፊፋ
ሕግ በሚያዘው መሠረት መወከላቸውን
ማረጋገጥና ከሕጉ ጋር የሚጋጩ ሆነው
የተገኙ እጩዎችን ከምርጫ ውጪ
የማድረግና ተጠባባቂዎችን ወዲያውኑ
የመተካት ትልቅ ኃላፊነት እንደወደቀቸው
አውቀው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከዚህ ከምርጫ ዜና ሳንወጣ የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ለራሣቸው
በሚመች መልኩ እያንዳንዱ የክልል
ፌዴሬሽን አንዳንድ እጩዎችን ብቻ ይላክ
የሚለው ገደብ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ባለፈው ቅዳሜ ባደረገው ስብሰባ ላይ ያነሣ
ሲሆን ማንኛውም ክልል ያለ ገደብ የፈለገውን
እጩ እንዲልክ ቀደም ሲል የተጣሰው ሕግ
እንዲታረም ተደርጓል፡፡
ፌዴሬሽኑ ባለፈው ያደረገው አመታዊ
ጠቅላላ ጉባኤ ዋልያ ቢራ (ሄይኒከን) በሰጠው
ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተከናወነ
ሲሆን አሁን ግን ፌዴሬሽኑ ገንዘብ የለኝም
በሚል ሁሉም የጉባኤው አባል ወጪውን
ራሱ ሸፍኖ እንዲመጣ መታዘዙ የጉባኤው
አባላትን ቁጥር እንዳያመናምነው ተሰግቷል፡፡