በካፍ ኮንፌደሬሺን ካኘ ቅድመ ማጣሪያ ፡ወላይታ ዲቻ በሜዳው የ5 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዬንስ ሊግ ሻምፒዬኑን የግብፁን ዛማሌክ 2ለ1 ሲያሸንፍ በአማካኝ ስፍራ ተሰልፎ የተጫዎተው ሀይማኖት ወርቁ ፡ከሀትሪክ ስፓርት ድህረ-ገፅ ጋር ያደረገው ቆይታ፡፡
☞በክረምቱ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ሀዋሳ ከተማን ለቀህ ወላይታ ዲቻን ከተቀላቀልክ በርካታ ወራቶችን አስቆጥረሃል፡በጦና ንቦቹ ያለህ ቆይታ ምን ይመስላል?
“አሁን ባለሁበት ክለቤ በጣም ደስተኛ ነኝ፡ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው፡፡በሊጉ ከነበርንበት ጥሩ መሻሻል እያሳየን ነው፡፡ቢሆንም ግን በሁለተኛው ዙር ከዚህ በበለጠ መሻሻልና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለብን አምናለሁ፡፡እኔም ከክለቤ ጋር ታሪክ እፅፋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡”
- ማሰታውቂያ -
☞በታሪካዊው ድል ዛማሌክን በሜዳችሁ በሀዋሳ ኢንተርናሺናል ስታዲዬም በደጋፊዎቻችሁ ፊት 2ለ1 ስታሸንፉ ምን አይነት ስሜት ተሰማህ ?
“ዛማሌክ በአፍሪካ ትልቅ ስም ካላቸው ጥቂት ክለቦች አንዱ ነው፡፡የዛንዚባሩን ዚማሞቶ አሸንፈን ከዛማሌክ ጋር ስንገናኝ ፡ክለቡ ካለው ስኬትና ስም አንፃር የስፖርት ቤተሰቡ እኛን ያሸንፋሉ ብሎ ከማሰብና ከመገመት ይልቅ ስንት ለስንት ይሸነፋሉ የሚለው ትልቅ መነጋገሪያ እርዕሰ ጉዳይ ነበር፡፡እኛ ግን ቀድሞውንም ዛማሌክን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነበርን ፡፡በቡድናችን ለጨዋታው የነበረን የአሸናፊነት የስነ ልቦ ዝግጂትና እና የቡድኑ መንፈስ ጠንካራ ስለነበር ያልተገመተውን እውን አድርገነው ዛማሌክን አሸንፈን ታሪካዊ ድል ስናስመዘግብ የተፈጠረብኝን ስሜት የምገልፅበት ቃላት የለኝም፡ከቃላትም በላይ ነው፡፡አንድ ነገር ሳላነሳው የማላልፈው ነገር ቢኖር ደጋፊዎቻችን ምርጦች ናቸው፡፡ይሄ ውጤትም የደጋፊዎቻችን ነው፡ይገባቸዋል፡፡”
☞በተጨዋችነት ዘመንህ አንተ በምትጫዎትበት ስፍራ እስካሁን አብረሃቸው ከተጫዎትካቸው ተጨዋቾች የተለየ ክህሎት አለው የምትለው ተጨዋች ?
በተጨዋችነት ከከፍተኛ ሊጉ እስከ ኘሪሚየር ሊጉ አውስኮድ፣ሀዋሳ ከተማ ፣ ጅማ አባጅፋር እንዲሁም አሁን በምጫዎትበት ዲቻ በርካታ የአማካኝ ስፍራ ድንቅ ችሎታ ካላቸው ተጨዋቾች ጋር መጫዎት ችያለው፡፡ከሙሉጌታ ምህረት ጋር በሀዋሳ ከተማ አብሬ ተጫውቻለሁ፡እሱ የተለየ የኳስ ክህሎት ያለው ፡በህይዎቴ ላይ ሁሌም አዲስ ጠቃሚ ነገር የሚጨምርልኝ አመለ ሸጋ የኔም ብቻ ሳይሆን የበርካቶቻቸን ሞዴል ነው፡፡ለሱ የተለየ ክብር አለኝ፡፡
☞በተጨዋችነት ህልምህ እስከ የት ድረስ መጫወት ታስባለህ ?
“ማንኛውም ተጨዋቾች እንደሚያልመው ለብሄራዊ ቡድን ማሊያ በመጫዎት ታሪክ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ከዚህ ባሻገር ከሀገር ውጭ በአፍሪካና አውሮፓ ካሉ ለትልልቅ፡ክለቦች መጫዎት የተጨዋቾችነት ትልቁ ህልሜ ነው፡፡ህልሜ እውን እንዲሆን ጠንክሬ እየሰራሁ ነው፡፡ከሰራሁ ካሰብኩበት ቦታ እንደምደርስ እርግጠኛ ነኝ፡፡በየጊዜው መሻሻል እንዳለብኝም አስባለሁ፡፡እናም ከማለም ባሻገር ወደ ህልሜን ወደ ተግባር ለመቀየር እራሴን በለውጥ ጎዳና ሁሌም እያሻሻልኩ ነው፡፡”
☞ዛማሌክን በሜዳችሁ 2ለ1 ብታሸንፉም ፡ጨዋታው ገና አላለቀም፡፡የመልሱ ጨዋታ ከ10 ቀናት በሇላ ካይሮ ላይ ይደረጋል፡ምን እንጠብቅ ?
ዛማሌክ በሜዳው ቀላል እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ዛማሌክ በአፍሪካ መድረክ ያለው ታሪክ ምንም ይሁን ምን ፡ዋናው ነገር በ90 ደቂቃ ተሽሎ መገኘት ነው፡፡ለዚህም ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ያስመዘገብነውን ውጤት አስጠብቀን ወደ ሌላኛው ምዕራፍ እንሻገራለን፡፡