በይስሐቅ በላይ
“የምጠላውም የተለየ ጥቅም ማግኘት አለበት ብዬ የማስበው አንድም ቡድን የለም” “94 ሚሊዮን ብር ከተገዛው ሕንፃ ገንዘብ ተበልቷል የሚባለው ማስረጃ ያልቀረበበት ተራ አሉባልታ ነው፤ ያልተጨበጠ ወሬ በቅንነት የሚሰራን አካል ይጎዳል”
በዳኝነት ላይ ፍትሀዊ አሠራር እንዳይኖር በማድረግ ክለቦችን ለመጉዳት ኃይማኖቴም፣
አስተዳደጌም፣ ስብዕናዬም አይፈቀድልኝም፡፡ የምትሰራው አድሎአዊነት ያለው ሥራ
የአንተን ስብዕና የሚወስን የሚመዝን ነው፤ እንደዚህ አይነቱን ድርጊት ለማድረግ
አይደለም ማሰብ በራሱ ኢትዮጵያዊነትን፣ ማንነትን ኃይማኖትን የመካድ ያህል አድርጌ
እወስደዋለሁ፡፡ ሁሉም ክለቦች ለእኔ እኩል ናቸው፤ አንዱን ጠቅሜ ሌላውን የምጎዳበት
ምንም ምክንያት የለኝም፡፡ ምናልባት ቃሉ የሚጎረብጥ ቢሆንም እንደዚህ አይነት ስራን
መስራት ማለት ለእኔ ሰው በራሱ ላይ አይፀዳዳም አይደል? ይህን ማድረግ ለእኔ በራስ ላይ
የመፀዳዳት ያህል ፀያፍ ነው፡፡” ይህንን ከላይ ያለው ጠንከር ያለ አስተያየት በተለይ
ለሀትሪክ የገለፀው ወጣቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና
የአርቢትር ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ነው፡፡
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ረዘም ላሉ አመታት በፕሬዚዳንትነት የኢትዮጵያ እግር
ኳስ ፌዴሬሽንን ከአምስት አመታት ያህል በላይ በስራ አስፈፃሚነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች
በማገልገል ላይ የሚገኘው የተዋጣለት የቢዝነስ ሰው የሆነው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እሱ
በሰብሳቢነት ስለሚመራው የአርቢትር ኮሚቴና በዳኝነቱ ዙሪያ፣ ፌዴሬሽኑ በ94 ሚሊዮን
ብር ስለገዛው ሕንፃ፣ እንዲሁም በክለብ ደጋፊነት ተፈርጆ በገለልተኛነቱ ላይ ስለተነሳበት
ጥያቄ፣ ከኤራ ወደ አምብሮ ስለተደረገው የትጥቅ ስፖንሰር ሽግግር ዙሪያ የሀትሪክ ጋዜጣ
ኤክሲክዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በድፍረት ጥያቄ አቅርቦለት ድፍረት
የተሞላበት ምላሽ ሰጥቶታል፤ አብሮነታችሁን አውሱን፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስጠናውን ጥናት በሰብሳቢነት በመምራትህ
ለአንተም ለአጥኚው ቡድን አባላትም 30ሺ ብር ፌዴሬሽኑ በስጦታ መልክ ሲያበረክት
አልቀበልም ብለሀል፤ ያልተቀበልከው ብሩ አንሶ… ወይስ ሌላ የተለየ ምክንያት አለህ… ?
ዮሴፍ፡-…አንድ አባባል ሲነገር አልሰማህም…?…የስጦታ ፈረስ… ጥርሱ
አይታይም…” የሚል… ስጦታ ምንም ይሁን ምን… የስጦታ ትንሽ የለውም… የሰጠን
አካል አመስግነህ መቀበል ነው ያለብህ…
ሀትሪክ፡-…በዚህ የምታምን ከሆነ ታዲያ… ለምን አልቀበልም አልክ..?
ዮሴፍ፡-…እኔ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጣሁት ገንዘብ ለመቀበል
አይደለም…፤…በወቅቱ የአጥኚው ቡድን አባላት በሠሩት ሥራ ፌዴሬሽኑ ተደስቶ
እንደማበረታቻ ይሆናል በሚል ሰላሳ ሰላሳ ሺህ ብር በስጦታ መልክ ሲያበረክት ለእኔም
በሰብሳቢነቴ በተመሳሳይ የ30 ሺ ብር የገንዘብ ስጦታ ተዘጋጅቶልኝ ነበር፤ ሊሰጠኝ ስል
በፍፁም አልቀበልም አልኩኝ፤ እንዲህ ያልኩበት ምክንያቴ ደግሞ ወደ ፌዴሬሽኑ
የመጣሁት ገንዘብ ለመቀበል ሣይሆን ሁሉ ነገሬን ለመስጠት በመሆኑ ሳልቀበል ቀረሁ፡፡
ሰዎች ችግር እንደሌለው ቢያግባቡኝም ከመነሻው አቋሜ ስለነበር ባለመቀበሌ ፀናሁ፡፡
ፌዴሬሹኑ ግን በአቋሜ መፅናቴን በማየቱ እንዲሁም በሰብሳቢነት መርቼ አመርቂ
የሚባል ስራን ስለሰራን የመጀመሪያ ሃሳባቸውን ለውጠው በፌደሬሽኑ ስም ለማስታወሻ
ይሆናል ብለው የወርቅ ስጦታ አበርክተውልኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በቅርቡ ለዳኞች ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተህ የትጥቅ ስጦታ ያበረከተው ከዚህ
አቋምህ በመነሳት ነው ብሎ መገመት ይቻላል…?
ዮሴፍ፡-…ለዳኞች በራሴና በድርጅቴ ጆሳምቢን ስፖርት ስም የሰጠሁት ስጦታን ከዚህ
ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ምክንያቱም ለዳኞች ስጦታ ለማበርከት ቃል የገባሁት
መስከረም ላይ ነውና፡፡ እኔ ፌዴሬሽኑን ለመጥቀም እንጂ በፍፁም በፌዴሬሽኑ
ለመጠቀም አልመጣሁም፡፡የኢትዮጵያን እግር ኳስ አገለግላለሁ ብለህ ስትመጣ ጊዜህን፣
ጉልበትህን፣ እውቀትህን ከቻልክ ደግሞ ገንዘብህን ጨምረህ በመስጠት ማገልገል
አለብህ፡፡ ፌዴሬሽኑን ለመጥቀም እንጂ በፍፁም በፌዴሬሽኑ ለመጠቀም መምጣት
የለብህም፡፡ የዳኞች የትጥቅ ስጦታውን በተመለከተ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኜም
ከውጪም የትጥቅ ችግር በጣም እንዳለ እሰማ ነበር፡፡ የዳኞት ትጥቅ በውጪ በጣም
ውድ ነው፤ ያሉን ጥቂት ኢንተርናሽናል ዳኞች ትጥቅ እያመጡ ቀዳዳውን ለመድፈን
እየሞከሩ እንጂ ችግሮች አሉ፡፡ ይሄንን ሲሰማ እንደ አንድ የስፖርቱ አመራር እንደ አንድ
የአርቢትር ኮሚቴው ሰብሳቢ ምን ማድረግ አለብኝ? አልኩና ወደ 400 ለሚጠጉ ዳኞች
በሁለተኛው ዙር የትጥቅ ስጦታ አበርክታለሁ ብዬ ቃል ገባሁ፤ቃል በገባሁበት መሠረትም
ቃሌን ጠብቄ ለ400 ዳኞች ከ400 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ በራሴና በድርጅቴ
ስም በስጦታ አበርክቻለሁ፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቅርቡ በ94 ሚሊዮን ብር ህንፃ መግዛቱ
አነጋግሯል፤ በዚህች ደሃ ሀገር በዚህ ሁሉ ሚሊዮን ብር ህንፃ መግዛቱን እንዴት
ታየዋለህ…?
ዮሴፍ፡- …በዚህ ሕንፃ ዙሪያ ለመነጋገር በመጀመሪያ ህንፃው በምን መልኩ
ተገዛ…?…ህንፃውስ የተጠቀሰውን ያህል ብር ያወጣል ወይ…? የሚለው በደንብ
መታየት ያለበት ይመስለኛል፤… የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህንፃውን በ94 ሚሊዮን
ብር ከመግዛቱ በፊት ትክክለኛውን የጨረታና የግዢ ስርዓት ተከትሏል፡፡ የህንፃ ግዢ
ኮሚቴው ከፌዴሬሽን ሶስት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከፌዴራል ወጣቶች ስፖርት
ኮሚሽን የኮንስትራክሽን ባለሙያ አካቶ የግዢ ማንዋል አውጥቶ በዛ የግዢ ሥርዓት
መሰረት ሕጋዊ ጨረታ አውጥቶ ህጋዊው ጨረታውን ደግሞ በአግባቡ ገምግሞ እንደሰራ
ነው የማውቀው፤ የወጣው ግልፅ ጨረታ ነው፤ በግልፅ ጨረታው ደግሞ ማንኛውም
አካል የእኔ ሕንፃ 10 ወይም 20 ብር ያወጣል ብሎ በሥም በታሸገ ኤንቬሎፕ ጨረታውን
ያስገባል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር አንደኛው ዋጋው ቢታይ ሁለተኛው ደግሞ ቦታው፣
ሕንፃው ነገ የተሻለ ነገር ማምጣት ይቻላል ወይ? የዋጋው ግምት እያደገ ይሄዳል ወይ?
የሚለው ሁሉ ይታያል፡፡ ኮሚቴው በመስፈርቱ መሠረት ይሄንን ሁሉ አጣርቶ ከተወዳዳሩት
ሕንፃዎች የተሻለ ሆኖ ያገኘውን ገዝቷል፤ በቃ ይሄው ነው ታሪኩ፡፡
ሀትሪክ፡- ለአንድ ሕንፃ 94 ሚሊዮን ብር ያውም ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ? በጣም
በዝቷል ለሚሉ ምን መልስ አለህ…?
ዮሴፍ፡- …እንግዲህ ገና ለገና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዚህን ያክል ብር ሕንፃ
ሲገዛ ሀሜታዎች አሉ ብለን ፊፋ የሰጠንን እድል አምክነን ባዶ እጃችን መቀመጥ አለብን
ብዬ አላስብም፡፡ ብሩ በጣም በዝቷል ተጋኗል ከተባለም ከላይ እንዳልኩህ ሁሉም ነገር
የግዢ ስርዓትን ተከትሎ በዝግ ጨረታ የተከናወነ ነው፤ አንድ ነጋዴ ንብረቱ 94 ሚለየን
ብር አይደለም ከዚያም በላይ ሊያወጣ ይችላል ብሎ ሊያስብ ሊያምን ይችላል፡፡ ስለዚህ
በዶክመንት ያቀረበው እስከሆነ ድረስ የጨረታ ኮሚቴው ያንን አጣርቶ መመዘኛውን
ያሟላ ነው ብሎ ያመነበትን ለውሳኔ አቅርቦ አስፀድቋል። ምናልባት እንደ ግለሰብ ስናወራ
ብዙ ነው ልንል እንችላለን ፤እንደ አስተዳደር እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስናወራ
ፌዴሬሽኑ ምንም የሌለው ነበር፤ አሁን ደግሞ ወደ መኖር ሲመጣ የምንፈልገውን ብቻ
ቀንጨብ አድርገን ከማራገብ የተሰራውን ሥራ ማበረታት ማድነቅ ያስፈልጋል ብዬ
አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ችግሩ ፌዴሬሽኑ የሕንፃ ባለቤት መሆኑ ላይ አይደለም፤እንደውም እዚህ ጋ
ይሄንን ሕንፃ በተመለከተ ድፍረት ያለው ጥያቄ ልጠይቅህ…በዚህ ሕንፃ ግዢ ገንዘብ
ተበልቶበታል በሚል እንደምትታሙ ታውቃለህ…? …ጉዳዩ የአደባባይ ወሬ በመሆኑ ምን
ትላለህ…?
ዮሴፍ፡- …እንደዚህ አይነት አመራር ቦታ ስትቀመጥ ሰዎች በራሣቸው ወይም
በተሰማቸው አሊያም ይሆናል ብለው ባሰቡት መንገድ የራሳቸውን መላ ምት
ያስቀምጣሉ፤ ገንዘብ ተበልቶበታል በሚል ሲወራ ሰምቻለሁ፤ ሰዎችም ይሄን ጥያቄ
ጠይቀውኛል፤ ገንዘብ ተበልቶበታልና እንዴት ዝም ትላላችሁ? ብለው የጠየቁኝ ጥቂቶች
አይደሉም፤ ነገር ግን እስከአሁን ድረስ ከንግግሮች ከአሉባልታ ባለፈ አንድም መበላቱን
የሚያሳይ ማስረጃ ያቀረበ አካል የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእኔም የሥራ አስፈፃሚውም
አቋም ከወሬ ባለፈ በዚህ ዙሪያ ማረጋጋጫ ያለው አካል ማስረጃውን ይዞ ቀርቦ በሕግ
ቋንቋ መነጋገር ይችላል፡፡ እኛ ጋር ብቻ ሣይሆን የሚመለከታቸው አካል ጋርም ማቅረብ
ይቻላል። ለእኔ ግን እስከአሁን ድረስ ከመላ ምት የዘለለ ያለፈ አንዳችም ተጨባጭ ነገር
ይዞ ያመጣ አላየሁም፡፡ በነገራችን ላይ ገንዘቡ ውድ ነው፣ በጣም በዝቷል የሚለውን
ማንም ሊያወራ ይችላል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ብር ተበልቷል፤ የኮሚቴው አካል ሄዶ
ተሞዳምዷል በሚል የሚወራው ነገር ብዙም አይመቸኝም፡፡ በእኔ በኩል በማስረጃ
ተደግፎ እስካልቀረበ ድረስ አልስማማም፡፡
ሀትሪክ፡-…በሕንፃ ግዢውም ገንዘብ ተበልቷል… በሚል የሚናፈሰው ወሬ ተራ
አሉባልታ ነው… እያልከኝ ነው…?
ዮሴፍ፡- …አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ፤ ይሄ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት
ህዝብ የመረጠው፣ጠቅላላ ጉባኤ አደራ ሰጥቶ የመረጠው ኮሚቴ ነው፤ ጠቅላላ
ጉባኤው የሀገርን እግር ኳስ ለመምራት ታላቅ ኃላፊነት ሲመርጠን እግር ኳሱን፣ ህዝቤን
አገልግል ገንዘቤንም ጠብቀህ አስተዳድርልኝ ብሎ ነው፤ መተዳዳደሪያ ደንቡም ይሄንን ነው
የሚለው፡፡ ነገር ግን እምነቱን፣ ታማኝነቱንና ብሎም አደራውን ጥሶ በዚህ ተራ ነገር
ውሰጥ የሚገኝ ሥራ አስፈፃሚ ይኖሯል የሚል እምነት በፍፁም የለኝም፡፡ እንደዚህ
ማስረጃ በሌላው ባልተጨበጠ የሚወራ ነገር በቅንነት ሀገርን ለማገልገል የመጣን አካል
ስሜት የሚጎዳ በጣምም የሚያሳንስ በመሆኑ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ሀትሪክ፡-…ከዚህ ከሕንፃ ጋር በተያያዘ ሌላው የሚሰነዘረው አስተያየትና ለሀሜት በር
የከፈተው ጉዳይ ፌዴሬሽኑ 94 ሚሊዮን ብር አውጥቶ ሕንፃ ከሚገዛ ለምን መሬት
ከመንግሥት በነፃ ጠይቆ በጣም አነስተኛ በሆነ ብር ገንብቶ ገንዘብ
አያተርፍም…?…በሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ…በዚህ ላይስ ምን ትላለህ…?
ዮሴፍ፡-…ልክ እንደ አስተያየቱ ሁሉ እኔም እንደ አንድ የቢዝነስ ሰው ምረጥ ብትለኝ
መሬት ገዝተን ብንሰራ ብዬ አስባለሁ፤ ምክንያቱም መሬት ገዝተን ስንሰራ የምንሰራው
ሕንፃ እንዲሆን በምንፈልገው፣ ዋጋው በጣም በሚቀንስበት መሠረት ሊሆን ይችላል
ብለህ ታስባለህ፤ ግን ችግሩ ይሄ አይደለም፡፡ ፊፋ ድጋፍ የሚያደርግልን ገንዘብ የጊዜ ገደብ
አለው፤ የጊዜ ገደብ በተቀመጠበት ሁኔታ መሬት ከመንግሥት ጠይቀን ወይም ገዝተን
ግንባታ ገንብተን ለመጨረስ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ፊፋ
ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ደግሞ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፤እንደውም ፊፋ ያቀረበልን
አማራጭ ወደ ግዢ ብትገቡ ነው የምመርጠው ብሎናል፡፡ ምክንያም ቀደም ሲል በእነ
አቶ ጁነዲን ጊዜ የተጀመረው እንቅስቃሴና የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ኤክስፓየር አድርጎ
(ተቃጥሎ) ነበር፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ጉዳዩን ለማስቀጠል
በሞከሩበት ጊዜ በፊፋ በኩል “ልንረዳችሁ የምንችለው በዚህች ባላቸው በጣም
በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ህንፃ ገዝታችሁ መሄድ የምትችሉበት እድል ካለ ይሄ ፈንድ
ሣይቃጠል ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ፤አለበለዚያ ግን ይሄ ከተቃጠለ ሌላ ፈንድ ነው
የምትጠይቁት” አሉን፡፡ ሌላ ፈንድ እንደ አዲስ መጠየቅ ደግሞ የማይታሰብ ነው፤
ምክንያቱም እንደ አዲስ ልጠይቅ ብትል ቀርቦ እስኪፀድቅ በትንሽ ከአመት ከሁለት
አመት በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ያለን ብቸኛ አማራጭ ፈንዱ ከሚቃጠል
በቀጥ ታ ወደ ግዢው ሥርዓት ብንሄድ ይሻላል ብለን ነው የወሰነው፡፡
ሀትሪክ፡-አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የእግር ኳሱ ችግር የቢሮ ችግር አለመኖሩ እንደሆነ
እየታወቀ ፌዴሬሽኑ ለሕንፃ 94 ሚሊዮን ብር ከሚያወጣ ገንዘቡን እግር ኳሱን
ለማሳደግ በሚረዳ ተግባር ላይ ቢያውለው ይመረጥ ነበር ብለው የሚሞግቱ አሉ…ይሄንን
ሃሳብስ እንዴት ነው የምታስተናግደው… ?
ዮሴፍ፡- …የሰዎች አስተያየት ይከበራል…፤ ሃሳብ በመስጠቱም ቅሬታ የለኝም፡፡ ግን
እንደዚህ አይነቱ አስተያየት የሚሰጠው ምናልባት የፊፋን አሠራር በደንብ ካለመረዳት
በመነጨ ነው ብዬ በግሌ አስባለሁ፡፡ ፊፋ ለአባል ፌዴሬሽኖች የሚሰጣቸው የተለያዩ
የፈንድ አይነች አሉ፤የልማት፣ የግዢ፣ የብ/ቡድን፣ የስልጠናና የተለያዩ ፈንድ
የሚደረግባቸው መንገድ አሉ፡፡ አሁን ለፌዴሬሽናችን የተለቀቀው የሕንፃ ግዢ ፈንድ
ከተዘረዘሩት ፈንዶች ውስጥ አንደኛው ነው፡፡ የሕንፃ ግዢ ፈንድ የፊፋው ፕሬዚዳንት
ኢንፋንቲኖ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ አባል ሀገራትን ተጠቃሚ ለማድረግ
የመጣ አዲስ ፈንድ ነው፡፡ በአለም ላይ ያሉት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች በተለይ በተለይ
በአፍሪካ ደረጀ በቂ የሆነ ቢሮ እንኳን ስለሌላቸው ከሌሎች ፈንዶች በተጨማሪ የዋና
መ/ቤት (Head quarter) ግዢና ግንባታ የሚል ፈንድ ብናካተት በሚል የተካተተ
ነው፡፡ ይሄንን የግዢ ፈንድ ማዋል የሚቻለው ፊፋም እንዲውል የሚፈልገው ለዚህ አለማ
ብቻ ነው፡፡ የሀገሪቱ እግር ኳስ ችግር ሌላ ነው ወይም የባሰ ነገር አለ ብለን የግዢ ፈንዱን
ወደ ሌላ ማዞር የሚፈቀድ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ለተፈቀደለት አላማ ብቻ
እንዲውል መደረጉ ለሁሉም ግልፅ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ፌዴሬሽኑ በ73 አመት የምስረታ ታሪኩ የራሱ የሆነ የ94 ሚሊዮን ብር
ሕንፃ ባለቤት በመሆኑ ክሬዲቱ የማነው…?… የአሁኑ… ወይስ… ያለፈው ፌዴሬሽን…?
ዮሴፍ፡- …ሁለቱም ፌዴሬሽኖች የየራሣቸው ድርሻ ቆርሰው ይወስዳሉ፤…የቀድሞው
አመራር ሁለት ሶስት ጊዜ ጨረታ አውጥቶ ቦታና ሕንፃ መረጣ አድርጎ ነበር በተለያየ
ምክንያት ሳይሳካ ቀረ እንጂ፡፡ በወቅቱ የነበረው ፌዴሬሽን ሣያሳካ የቀረበት የተለያየ
ምክንያት ማንሣት ይችላል፡፡ በተለይ የፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ምርጫ ስለነበር ነገሮች
እንዳይሳኩ እንቅፋት ፈጥሯል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ የተነሣ በወቅቱ የተወሰነው ውሳኔ
ምንድነው አዲስ የሚመጣው ፌዴሬሽን (አመራር) ይሄን ሥራ ቢሰራው ይሻላል የሚል
ውሳኔ የተወሰነበት ሁኔታ ነበር፤ከዚህ አንፃር የነበረው ፌዴሬሽን የተወሰነ ጥረት አድርጓል
ባልኩት ሁኔታ ባይሳካም፤ አሁን ያለው ፌዴሬሽን ደግሞ በጣም በፍጥነት፣ ጠንካራ በሆነ
አቋም ፊንዱ እንዳይቃጠል የማሳመን ሥራ በመስራት ሊቃጠል (ኤክስፓየርድ) ያደረገን
ነገር ነፍስ በመዝራት ሥራ አስፈፃሚው ተፈፃሚ እንዲሆን በማድረግ ፌዴሬሽኑን በታሪክ
የራሱ ትልቅ ሕንፃ ባለቤት አድርጎታል፡፡ በዚህ በኩል በተለይ ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ
ዙሪክ ድረስ በመሄድ ትልቅ ጥረት አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ እንዳልኩት ሁለቱም
የራሣቸው ሚዛን የሚደፋ ሥራ ሠርተዋል፡፡
ሀትሪክ፡-እስቲ አሁን ደግሞ ቀደም ሲል የብ/ቡድኑ የትጥቅ አቅራቢ ስፖንሰር
ከሆነው ኤራ ወደ አምብሮ ስለተደረገው ድንገተኛ ሽግግር እናውራ፤ ከኤራ ጋር የነበረውን
ኮንትራት አቋርጣችሁ ውል እያላችሁ ወደ አምብሮ መሄዳችሁ ፌዴሬሽኑን ለ100 ሺህ
ዩሮ ቅጣት አሳልፎ ሰጥቶታል የሚል ነገር አለ.. ይሄ ምን ያህል እውነት ነው…?
ዮሴፍ፡- …እውነት ነው… ይሄንን አምነንበት ነው የገባነው…
ሀትሪክ፡- …አምነንበት ነው የገባነው ስትል… ምን ማለት ነው…?… ግልፅ
አድርገው እስቲ…?
ዮሴፍ፡- …ቀደም ሲል በዚህ ዙሪያ በሰጠነው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በግልፅ
ተናግረናል፤ከኤራ ጋር የነበረውን ውል በማቋረጣችን እንድንከፍል የምንጠየቀውን 100
ሺህ ዩሮ እንከፍላለን፡፡ ምክንያቱም ከኤራ ጋር ሁለት አመት ብንቆይ በአመት 50ሺ
በሁለት አመት 100 ሺ ዩሮ መክፈላችን አይቀርም፡፡ ግን አሁን አምብሮ ከተባለው
የትጥቅ አምራች ድርጅት በስፖንሰርነት በነፃ የምናገኘወ ጥቅም በገንዘብ ሲሰላ ከ100
ሺህ ዩሮ በላይ ነው፤ያውም በአንድ አመት፡፡ ከዚህ አንፃር የኤራን ውል በማፍረሳችን
የምንከፍለው 100 ሺህ ዩሮ መክፈል ከአምብሮ ከምናገኘው ትልቅ ጥቅም አንፃር
የተሻለ ነው ብለን በማመናችን ይሄን መርጠናል፤ ስለዚህ 100 ሺህ ዩሮ ትከፍላለችሁ
ወይ? ላልከው አዎን ደስ ብሎን እንከፍላለን፡፡
ሀትሪክ፡- …ግልፅ ለማድረግ ያህል በዚህ ደረጃ ዋጋ እስከመክፈል ያደረሰችሁን ከኤራ
ወደ አምብሮ የተደረገው ሽግግር የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በዝርዝር አሣየኝ…?
ዮሴፍ፡- …ጠቀሜታው (Benefit) ብዙ ነው፤ አንደኛው ትርፉ ማለት ከላይ
እንዳልኩት ኤራ በግማሽ ነው ስፖንሰር የሚያደርገን በአመት 50 ሺህ ዩሮ እንከፍላለን፡፡
አሁን ግን ገንዘብ ሳንከፍል ነው አምብሮ ስፖንሰር የሚያደርገን፡፡ እንደ ሀገር ስታስበው
50 ሺህ ዩሮ ማዳን ቀላል የሚባል አይደለም፤እንደ ፌዴሬሽን ስታስበው 50 ሺህ ዩሮ ብዙ
ሥራ ይሠራልናል፡፡ ሁለተኛው በፊት ስናገኛችው ከነበሩት ውስጥ ቦርሳ፣ካሶተኒ፣
የመጫወቻና የልምምድ ማልያ፣ ፎጣን የመሳሰሉት ለስፖርተኛው የሚያስፈልጉ ትጥቆች
ቁጥራቸው ከበፊቱ በጣም የበዙ ናቸው፤ መብዛታቸው ወደ ገንዘብ ሲለወጥ ልዩነቱ
በግልፅ ይታያል፡፡ ለምሣሌ የተጫዋቾች ወደ 320 የሚጠጋ ትጥቅ ፣ የአሰልጣኞች 80
ኖርማል ቁምጣ ረዥም፣ ካልሲ፣ ቦርሳ፣ ኮፍያ፣ ጫማ (ስኒከር)፣ነጠላ ጫማ፣
የልምምድ ሰደርያዎች፣ የልምምድ ቁምጣ፣ የልምምድ እቃ መያዥያ፣ የኳስ መንፊያ፣
የሃይት ቦርድ መፃፊያ ማርከር፣ ከሜዳ ውጪ ማልያና ቁምጣ፣ ሶስተኛ የተጨዋችና
የግብ ጠባቂ ማልያና መጋጫና የአምበል አርም ባንድ በአጠቃላይ አንድ ቡድን እንደ
ቡድን ሊኖረው የሚገቡ ነገሮች እንዲኖሩት የሚያደርግ በመሆኑ ካለፈው ስምምነት በብዙ
መልኩ የላቀ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ዝርዝር ሲታይ ሚናውን ከትጥቅ ያልዘለለ አድርጎ ማሰብ
ስህተት ነው፤ ምክንያቱም ጥቅሙ ከዚህ ላቅ ያለ ነውና፡፡ አንድ ስፖርተኛ ሊያገኘው
የሚገባውን ወይም ሊሟላለት የሚገባው ነገር ባለመሟላቱ የተነሣ የሚፈለገውን
ውጤታማነት እንዳያመጣ ተፅዕኖ ይፈጥርበታል፤ ተነሳሽነቱም ይቀንስበታል፡፡ በተቃራኒው
ሁሉም ነገር የሚሟላለት ከሆነ ነፃ የውጤታማነት አዕምሮ እንዲኖረው ለተሻለ ነገር
እነዲነሳሳ ከሜዳ ላይ ዝግጅቱ በተጨማሪ የራሱን እገዛ ያደርግለታል።
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ከአምብሮ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ትልቁን ሚና
የተጫወተው ዮሴፍ… የአምብሮ ኤጀንት በመሆኑ ነው በሚል ትታማለህ… ለዚህ መልስ
አለህ…?
ዮሴፍ፡- …ይሄ በጣም ትልቅ ውሰት ነው…፤… እውነት ለመናገር አምብሮ ወደ
ኢትዮጵያ እንዲመጣ በከፍተኛ ሁኔታ የሠሩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ
ናቸው፡፡ከካምፓኒው ጋር በጥልቀት (ዲፕሊ) ገብተው ጨርሰው ያመጡበት ሁኔታ ነው
ያለው እንጂ እኔ ማንኛውንም የትጥቅ ስፖንሰር ካምፓኒ ወደ ሀገር ቤት አለመጣሁም።
እንደው ቢሆን ቢሆን የእኔ ካምፓኒ ስፖንሰር አድርጎ ቢሰራ ነው የምመርጠው እንጂ
እውነት ለመገር አምብሮን እኔ አለመጣሁትም፤ ፕሬዚዳንቱ ናቸው፡፡ አምብሮ በዚህ ደረጃ
ለምን እንደተነሣ ባይገባኝም እንደተባለው እኔ አምጥቼውም ቢሆን ለሀገር እስከጠቀመ
ድረስ መልካም ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ፌዴሬሽኑ እንዲጠቀም እንኳን እኛ አመራሮች
ማንኛውም የስፖርት ቤተሰብ ቢያመጣው ጥሩ አጋጣሚ ከሆነ መቀበሉ ክፋት አለው አልልም፡፡
ሀትሪክ፡-የአንተ ስም ከአምብሮ መምጣት ጋር ተያይዞ እንዲነሣ ምክንያት የሆነው
የአምብሮ ኤጀንት መሆንህን ተከትሎ ይመስለኛል…?
ዮሴፍ፡- …የሚገርምህ ነገር አምብሮዎችን እንኳን እኔ ላመጣችው ስፖንሰር
መሆናቸውን እንኳን አላውቅም ነበር፤ ከድርጅቴ ጆሳምቢን ስፖርት የአምብሮ ኤጀንትነት
ጉዳይ ጋር ካምፓኒው ከፌዴሬሽኑ ጋር ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ፌዴሬሽኑን እነማን
ናቸው ትላለቅ ካምፓኒዎች? ብሎ ጠይቆ አጥንቶ ነው የመጣው፤ በዚህ መሠረት
ፌዴሬሽኑን ካነጋገረ በኋላ እኔንም እንደ ካምፓኒ ጠርተውኝ አነጋግረውኛል፡፡
“ከድርጅታችሁ ጋር አብረን መስራት እንችላለን ወይ?”ብለውኝ በዚህ አግባብ ነው
የተነጋገርነው፤ ፕሬዝዳንታችን በወቅቱ ለማናችንም ቀደመው ስላልነገሩን ላውቅ
አልቻልኩም፤ የሚገርምህ ስብሰባ ላይ የአምብሮ ካምፓኒ ፕሬዝዳንት ጋር ስንገናኝ
ደንግጬያለሁ፤ ስለዚህ የተባለው ነገር ከእኔ ጋር አይገናኝም፤ ፍፁም ውሸት ነው
በሚለው ቢወሰድ ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን ከአምብሮ ጋር ያለው ስምምነት ተጠናቋል፣ መቼ ነው ወደ ተግባር
የምትገቡት…?
ዮሴፍ፡-…እንዳልከው…ከካምፓኒው ጋር ተፈርመናል…፤…ካምፓኒውም በፍላጎታችን
መሠረት ምርቱን እያመረተ ነው… በአጭር ጊዜ ውስጥ… ስምምነታችን ወደ ተግባር
ይለወጣል… ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- በአሁን ሰዓት ለእግር ኳሱ የማጣፈቻ ቅመም ያህል የሚቆጠረውን ቁልፉን
ዳኝነትን በሰብሳቢነት እየመራህ ነው…ጫናውን እንዴት አገኘኸው… ?
ዮሴፍ፡- …ለእኔ ከፍተኛ ጫና አለው ብዬ አላስብም…፤…ከፍተኛ ጫና የለውም ስል
ምን ለማለት ነው… በትክክለኛውና በሀቅ የሚሰራ ባለሙያ ካለ፣ የኢትዮጵያን እግር ኳስ
አለአግባብ ካልተጠቀምኩበት የሚል ባለሙያ እስከሌለ፣ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ሌላው
አላዋቂ ነው ብሎ የሚመፃደቅ ባለሙያ እስከሌለ፣ የግሩፕ ስራን ለመስራት፣
ለመጠላለፍ የሚተጋ ባለሙያ እስከሌለ ድረስ ስራው በምንም አይነት ተዓምር ጫና
አይኖረውም፤ ከባድም አይሆንም፡፡ ሥራውን ለመስራት አጥብቆ የሚጠይቀው
ታማኝነትን፣ ንፁህ መሆንን ብቻ ነው ።እነዚህ ካሉ ጫናም የለውም ከባድም
አይሆንም፤ እንደተባለው ሥራው የሙያ ሥራ ነው፤ የሙያ ሥራ እንደመሆኑ ሙያውን
ቀርቦ ለመረዳት፣ ለማዳመጥ፣ ለመማር ከሞከርክ የዳኝነት፣ የኮሚሽነርነት ሥራ
በአግባቡ ይመራል የሚል እምነቱ አለኝ፡፡ ለዚህ ማሳያ ባለፉት ስድስት ወራት
የሄድኩባቸው ርቀቶች፣ የተከተልኳቸው መንገዶች አነሰም በዛም ያሳዩኝ ውጤቶች አሉ፡፡
እርግጥ ነው ከ400 በላይ ዳኞች ከ100 በላይ ኮሚሽነሮችን ነው የምትመራው…ከዚህ
አንፃር ከባድ ነው፤የእነዚህን ሁሉ ፍላጎት ማሟላት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በዚያው ልክ
ደግሞ ውጤታማ እንዳይሆን የሚፈልግ አካል አለ፤ ይሄንንም ፈተና መቋቋም
ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ስገባ እንደተናገርኩት ይሄ ነገር እንደማይከብደኝና
ከእግዚአብሔር ጋር ውጤታማ ሆኜ እንደምሠራው እምነቱ አለኝ፡፡ ምንም እንኳን
እንደተባለው ቦታው ብዙ ልፋትን ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ነው፤ እንደምታውቀው ይሄ
ሁሉ ምደባ… ይሄ ሁሉ ሥልጠና የሚሰጠው በአንድ ባለሙያ ነው…በእኛ ዲፓርትመንት
ውስጥ ባለ፤ ምናልባት በቅርቡ የዳኝነት ዲፓርትመንትም አንደኛው የሪፎርሙ አካል
በመሆኑ የሚሰሩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡
ሀትሪክ፡-አንተ የአርቢትር ኮሚቴውን በሰብሳቢነት እየመራህ ነው፤ በሙያው ካላለፈ
ይልቅ በሙያው ያለፈ፣ የሙያውን ቋንቋ አቀላጥፎ መናገር በሚችል ቢመራ የተሻለ
ነው የሚል አስተያየት ያላቸው አሉ…ይሄ ሃሣብ ይሰማማሃል… ?
ዮሴፍ፡- … እ… ሰዎች ይሄን አይነት አስተያየት የሰጡት ከምንድነው?… የሚለውን
ስናይ… በፊፋ ህግ መሠረት በተለይ በተለይ የዳኝነት ቦታ በኢንተርናሽናል ዳኝነት ባገለገሉ፣
በዳኝነት ህይወት ውስጥ ባለፉ አካላት ቢመራ መልካም ነው ይላል…ምክንያቱም እነሱ
በቀላሉ ሊመሩት ይችላሉ ከሚል እሳቤ ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን ከሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ
ውስጥም ሆነ በሌላ ባለሙያ ሊመራ ይችላል፡፡ ያው እንደምታውቀው አሁን ባለው ሥራ
አስፈፃሚ ውስጥ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዳኝነት ሙያ ያለፈ ሰው የለም፤ እኔ ይሄንን ቦታ
በሰብሳቢነት እንድመራ ስመደብ በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነት፣
በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከአምስት ዓመት በላይ በማገልገሌ እንዲሁም በዳኝነትና በሴቶች
ሥራ ላይ ብዙ መስራቴና ማገልግሌ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚትው ያንን ግንዛቤ ውስጥ
በመክተት በተሻለ በስብሳቢነት ሊመራው ይችላል ብለው እድሉን ሰጥተውኛል፡፡
እስከአሁን በሰብሳቢነት በቆየሁባቸው ጊዜያት የገጠመኝ ችግር የለም፤ ምክንያቱም እኔ
አብዛኛውን ሥራ የምሰጠው ለባለሙያ ነው፤የያዝኳቸው ባለሙያዎችና ሌሎች
ሙያተኞች ሥራውን በአግባቡ እየሠሩ በመሆኑ ያን ያህል ገጠመኝ የምለው ችግር የለም፡፡
ሀትሪክ፡- ከዳኝነት ምደባ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጨዋታ እንዲመሩ የተወሰኑ
ዳኞችን መመደብ እንዲሁም የሚጠበቁና ትላልቅ የሚባሉ ጨዋታዎች ላይ ለጨዋታው
የማይመጥኑ ዳኞችን የመመደብ ችግር ይታያል… በሚል ወቀሳ ይቀርብብሃል…ወቀሳውን
ትቀበለዋለሁ…?
ዮሴፍ፡- …እኔ በግሌ ብቃት የሌላቸው ዳኞች አሉ ብዬ አለምንም፤ ምናልባት
ብቃታቸው ሊለያይ የሚችሉ ዳኞች እንዳሉ ግን አምናለሁ፡፡ ምናልባት ኢንተርናሽናል ናቸው
የምንላቸው ዳኞች በሀገር ውስጥ ውድድር ሲያበላሹ ልናይ እንችላለን፤ ፌዴራል ናቸው
ያልናቸው ዳኞች ደግሞ በሀገር ውስጥ ውጤታማ ሆነው ልናገኛቸው አንችል ይሆናል፡፡ ይሄ
ዳኝነት ነው፤ በመቅስፈት ውሳኔዎች የሚወሰኑበት እንደመሆኑ ሊከብድ ወይም
ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ከዚህ በተረፈ ምደባን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃን ነው በጥያቄህ
ይዘህ የመጣኸው፤ ምክንያቱም በተደጋጋሚ የጨዋታ ምድባ በተለይ ያገኘ ዳኛ የለምና፡፡
ምናልባት ካለብን የዳኛ እጥረት ደግመን አንድ ክለብ ላይ ዳኛ የምንመደበው ያ ክለብ
አሸንዴ ከሆነ ያንን ዳኛ ከችግር አንፃር ደግመን ልንመድበው እንችላለን፤ ከዚህ ውጪ
በጣም ተጠንቅቀን በዳታ ነው ዳኞችን የምንመደበው፡፡ ምናልባት ያልተመደቡ ሰዎች
ይሄን ጥያቄ አንስተው ከሆነ አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን አንድ ጥያቄ በድፍረት ልጠይቅህ ነው ፤ዮሴፍ የአንድ ትልቅ ክለብ
ደጋፊ ነው ብለው በአርቢትር ኮሚቴ ሰብሳቢነትህ ላይ ጥያቄ በማንሳት የአንተን
ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱና የሚያነሱ አሉ… ከዚህ አንፃር ዮሴፍ ምን ያህል
ገለልተኛ ነው?
ዮሴፍ፡- ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠቴ በፊት አንድ ነገር ላስቀምጥ፤
በዚህ በእግር ኳሱ ምህዳር ውስጥ ያለን ማህበረሰብ ብትመለከት ወደ እግር ኳሱ
የመጣው አንድም በመጫወት፣ በመደገፍ፣ በማሰልጠን፤ በመዳኘት፣ እግር ኳስን፣
ክለብን አልያም ተጨዋችን ወዶ ነው፡፡ በዚህ አይነት ያልተቃኘ አንድም ሰው ወደ እግር
ኳሱ መንደር አይመጣም፤የእኔም የሁሉም አመጣጥ ይሄው ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ
ህይወት ውስጥ በማለፍህ ሰዎች አንተን ከአንድ ክለብ ጋር አገናኝተውህ ይሆናል ብለው
የሚያስቡትን ነገር ይለጥፉብሃል፡፡ እኔ ወደ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የመጣሁት አንዱን ክለብ
ጠልቼ ሌላውን ልወድ አሊያም አንደኛው ጠቅሜ ሌላውን ልጎዳ አይደለም፡፡ ሁሉንም
ክለቦች በእኩልነት ለማገልገል ነው የመጣሁት፡፡ በዚህ አጋጣሚ የማስተላልፈው
መልዕክት አንድን ክለብ ጠቅሞ ሌላውን የመጉዳት ነገር በፍፁም እንደማይታሰብ ነው
መናገር የምፈልገው፤ አሁንም ደግሜ እነግርሃለሁ ክለቦች በዚህ በኩል ለሰከንድም
ቢሆን እንዳያስቡ ነው፤ እንደውም ክለቦቻችን በዚህ አይነቱ ምናባዊ አስተሳሰብ
ከሚሰቃዩ ክለቦቻቸውን አጠናክረው እንዲሠሩ ነው፡፡ በዘንድሮው አመት አንደኛው ግቤ
ይሄን ሥራ የሚሠራ አመራር፣ ዳኛ፣ ኮሚሽነር ወይም ባለሙያ አሣዶ መያዝ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-አንተ እንደዚህ ብትልም በቅርቡ አንድ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ የአንተን
ተአማኒነት ወይም ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት መገለጫ ኃላፊነትህን ጠቅሶ
እስከማውጣት ሁሉ ደርሷል… ይሄ ነገር አንተ ከምትለው ጋር አይጋጭም፤.. ?
ዮሴፍ፡- በዚህ ዙሪያ ምላሽ ባልሰጥህ ደስ ይለኝ ነበር፤ ነገር ግን እውነታውን
ለማሳውቅ ያህል በጉዳዩ ዙሪያ እናገርለሁ፡፡ ምናልባት ደብዳቤውን አይተኸው ከሆነ
አፃፃፉ ራሱ ተገቢነት የለውም፤ አንድ ሰው በዚህ ደረጃ ጥፋተኛ ነው ብለን ደምዳሜ ላይ
ስንደርስ ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡እርግጥ ነው አንዳንድ ጊዜ ማረጋገጫ የማይገኝላቸው
ስውር ስራዎች ሊሠሩ ይችላሉ…፤… አንተ እንደ አንድ የክለብ ኃላፊ በዚያ ላይ የትልቅ
ክለብ አመራር ከመሆን አኳያ ስጋትህን ማስቀመጥ መብትህ ነው፤ ሥጋት አለኝ ፌዴሬሽኑ
ይሄንን ጉዳይ ሊያይልኝ ይገባል ማለትም መብትህ ነው፡፡ ነገር ግን የደብዳቤው ርዕስ
የግለሰብን ማንነት የሚነካ የኮሚቴዎችን ሞራል የሚጋፋም ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎም
የፌዴሬሽኑን ታማኝነት የበለጠ የሚጎዳም ነው፡፡ በጣም የታዘብኩት ብዙዎቻችን በበፊቱ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ በመመራት አስተሳሰብ ውስጥ ነን፤አሁን ከዚያ ልንወጣ ይገባል፡፡
ልንተማመን ልንነጋገር ግድ ይላል፡፡ ስም ከማጥፋት በፊት ማንኛውም አካል ከእኔ ጋር
ቁጭ ብሎ መነጋጋር ይችላል፤ በተረፈ ግን የእኔንም ሆነ የሌላው አመራር ስም ማጥፋት፣
ስብዕናውን መንካት ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፤ ደግሞም አይጠቅመንም፡፡
ሀትሪክ፡- ከላይ እንዳልኩት ይሄ ታላቅ ክለብ ስምህን ጠቅሶ መግለጫ አውጥቶብህ
በጉዳዩ ዙሪያ ዝም ማለትህ አምነህ የተቀበልክ ያህል የቆጠሩ ጥቂቶች አይደሉም በጉዳዩ
ዙሪያ በወቅቱ ለምን ምላሽ አልሰጠህም…?
ዮሴፍ፡- …ዝም አላልኩም…፤… በነገራችን ላይ እኔ በግሌ ሣይሆን እንደ ፌዴሬሽንም
ክለቡ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃውን እንዲያመጣ በተደጋጋሚ ተጠይቆ ማቅረብ አልቻለም፤
ዝም ብሎ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ እኔ መረጃ ቢቀርብ በጣም ነው የምደሰተው፤
በዚህ ስነ ምግባር ውስጥ ተገኝቼ ብያዝ አልደነግጥም፤ በጣም ነው የምደሰተው፡፡
ምክንያቱም የኢትዮጵያ እግር ኳስ መንፃት ስላለበት። እንዳልኩህ መረጃ ተጠይቋል
እስካሁን ከስም ማጥፋት የዘለለ የቀረበ ነገር የለም፡፡
ሀትሪክ፡-በዚህ ደረጃ ስምህ መነሳቱና ገለልተኝነትህን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነገር
መነሣቱ በመስራት ፍላጎትህ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ አለ…?
ዮሴፍ፡- እንደዚህ አይነት የስም ማጥፋት ዘመቻዎች የስራው አንደኛው ቻሌንጅች
(ፈተናዎች) እንደሆኑ እገምት ነበር፤ምክንያቱም ሁልጊዜ ክለቦችን ከስራ አስፈፃሚ
ኮሚቴዎች ውስጥ አንደኛውን አካል ከአንዱ ጋር መድበው ይሄን አይነቱን ወሬ
እንደሚያነሱ የተለመደ በመሆኑ ብዙም አልገረመኝም፡፡ እውነቱን ለመናገር ደብዳቤው
በዚህ ደረጃ ይሆናል የማልግምት ግን አልነበረኝም፡፡ ሌላው ደግሞ 16 ክለቦች አሉ… 16
ክለቦች ምንድነው የተጎድት? የተጠቀሙትስ? የሚለው ላይ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሁልጊዜ አንድን ክለብ ከሌሎች ለይተህ የምትጎዳበት ፣የምትጠቅምበት ምንም የተለየ
ምክንያት የለም፤ እኔ ጠላትነት ከማንም ጋር የለኝም፡፡ በስራም፣
በዝምድናም፣በእውቀትም የተጎዳዳነው ነገር የለም፤ሁሉም ለእኔ እኩል ናችው፤እኔ
በዚህ አጋጣሚ ደግሜ የምናገረው ምናልባት ቃሉ የሚጎረብጥ ቢሆንም እንደዚህ አይነት
ስራን መስራት ማለት ለእኔ ሰው በራሱ ላይ አይፀዳዳም አይደል? ለአኔ ይሄን ማድረግ
ማለት በራስ ላይ የመፀዳዳት ያህል ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኝነት ውስጥ አሁን
ጥርጣሬ ያለው አካል ያለው ሥራ ከተሰራ ወይም ከሰራሁኝ እደግመዋለሁ ለእኔ በራስ ላይ
የመፀዳዳት ያህል ነው፡፡
በዳኝነት ላይ ፍትሀዊ አሠራር እንዳይኖር በማድረግ ክለቦችን ለመጉዳት ኃይማኖቴም፣
አስተዳዳጌም፣ ስብዕናዬም አይፈቅድልኝም፡፡ አንተ የምትሠራው አድሎአዊነት ያለው ሥራ
የአንተን ስብዕና የሚወስን የሚመዝን ነው፤ እንደዚህ አይነቱን ድርጊት ለማድረግ
አይደለም ማሰብ በራሱ ኢትዮጵያዊነትን፣ ማንነትን፣ ኃይማኖትን የመካድ ያህል አድርጌ ነው የምወስደው፡፡
ሀትሪክ፡- ዳኞች የእግር ኳሱ ቁልፍ ከመሆናቸው አንፃር እየሰጡ ያለው አገልግሎትና
ክፍያው ተመጣጣኝ ነው ብሎ መናገር ይቻላል?
ዮሴፍ፡- ክፍያውን በተመለከተ በጣም በፊት ለዳኞች ሊከፈል ከነበረው ጋር ካወዳደር
ነው በጣም ጥሩ ነው ፤አሁን ካለው ከጊዜው፣ ገንዘብ ካለው የመግዛት አቅም ጋር
ካየነው ግን አነስተኛ ነው፤በቂ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አሁን ጥረት እያደረግን ያለው ካለው
ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ለማስተካከል ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ወደ ስልጣን ከመጣህ በኋላ እየዘገየ ያስቸገረውን የዳኝነት ክፍያን
በተመለከተ “ከዚህ በኋላ አትቸገሩመ ወደ አካውንታችሁ ወዲያውኑ ነው የምናስገባው”
ብትልም አሁንም ይሄ ችግር ሊቀረፍ አልቻለም….?
ዮሴፍ፡- ዳኝነት አንደኛው የሪፎርም አካል ነው፤ ነገር ግን ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ
ስንሞክር ብዙ ፈታኝ ነገሮች ገጥመውናል፡፡ ከነበረው ልማዳዊ አሠራር አውጥተህ ወደ
አዲስ አሠራር ስትወስድ መንገጫገጭ ይኖራል፤ አሮጌው አሠራር እስኪቀየር አዲሱ
እስኪለመድ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡ አሁን መቶ በመቶ ትክክል ነው የምንልበት ደረጃ
ላይ ባንደርስም የተስተካከለ ነገር መፍጠራችን ግን አይቀሬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገር ስም የሚያስጠሩ ሁለት ኢንተርናሽናል ዳኞች
አሉን፤ኢተርናሽናል አርቢትር ሊዲየ ታፈሰና በአምላክ ተሰማ። አለም የሰጣቸውን ክብር
ያህል በሀገር ቤት፣ በፌዴሬሽን ተሰጥቶአቸዋል ማለት ይቻላል…?
ዮሴፍ፡- ሊዲየ ታፈሰና በአምላክ ተሰማ በአለም አቀፍ ደረጃ በጣም ርቀው ስለሄዱ
እንጂ እነሱ ብቻ ሣይሆኑ ሌሎች ኢንተርናሽናል ዳኞችም አሉን፡፡ በዘንድሮው አመት ከዚህ
ቀደም ባልታየ መልኩ ካፍም ሆነ ፊፋ ለዳኞቻችን ትኩረት ሰጥቷል፤ ለሁለቱ ታላላቅ
ዳኞቻችንክብር መስጠትን በተመለከተ በእኛ በኩል በተለይ በዳኛ ኮሚቴ ከእነሱ ጋር
በጣም ቁልፍ ሆነነ እየሠራን ነው፡፡ ሀገራችንን የሚያስጠሩ ሙያተኞች በመሆናቸው፣
ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ዳኞች በመሆናቸው ለሥራቸውም ለስኬታቸውም ትልቅ ክብር
አለን፡፡ ያሰብናቸው ብዙ ነገሮች አሉ ፤በጊዜ ሂደት የምናየው ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- ውድ የሥራ ጊዜህን ተሻምተህ ለሰጠኸኝ ቃለ-ምልልስ አመሰግኜህ
ከመለያየታችን በፊት በመጨረሻ የምትለው ካለ እድሉን ልስጥህ….?
ዮሴፍ፡- በሁለት መልኩ ነው መልዕክቴን ማጠቃለል የምፈልገው፤ አንደኛው የዳኝነት
ጉዳይን በተመለከተ ነው፡፡ አሁንም ደግሜ የምናገረው ሁሌም በፕሪሚየር ሊጉ፣
በብሔራዊ ሊግም ሆነ ከፍተኛ ሊግ ያሉት ክለቦች በልበ ሙሉነት በነፃነት እግር ኳሳቸውን
እንዲመሩ እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ ዳኝነትን በተመለከተ ለሰከንድም ቢሆን አድሎአዊ አሠራር
ይኖራል ብለው እንዳያስቡ እመክራለሁ፡፡ መቶ ፐርሰንት ደግሜ የማረጋግጥልህ በዚህ
አይነት አስተሳሰብ ውስጥ የሚኖር አካል የለም፡፡ በእኔ በኩልም ማንነቴም፣
አስተዳደጌም፣ ስብዕናዬም፣ እምነቴም ይሄን ስለማይፈቅድልኝ ሁሉም ሰው ይሄን
እንዲገነዘብልኝ እፈልጋለሁኝ። ከዚህ በተረፈ ዳኞች ሰው እንደመሆናቸው መጠን ሊሳሳቱ
ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዳኞችም ኮሚሽነሮችም የእኔ አይነት ተመሳሳይ አቋም
ይኖራቸዋል የሚል እምነቱ ነው ያለኝ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንድ አንድ ዳኞች ስህተት ሊሠሩ
ይችላሉ፤ያንን ስህተት ብቻ በመምዘዝ ያልነው ተፈፀመ በማለት በአሉባልታ ባንኖር
መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ክለቦች እግር ኳሳቸውን ብቻ ይሰሩ እኛ ዳኝነታችንን
እንሠራለን፡፡ በ2011 ዳኝነትን በነፃነት፣ በታማኝነት ሠርተን የዳኞቻችንን እውቀት ከፍ
አድርገን በ2012 ደግሞ ከዚህ የበለጠ ለመስራት ዝግጁ ነን ብዬ እናገራለሁ፡፡ ሌላው
እንደ ፌዴሬሽን መልዕክት ሳስተላልፍ ሥራ አስፈፃሚው ትልልቅ ሥራዎችን እየሠራ ያለበት
ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሁሉም ከጎናችን መቆም አለበት፣ የጠቅላላ ጉባኤውም አባላት
ክለቦች፣ ሙያተኞች ከአሮጌ አስተሳሰብ ወጥተው ወደ ተሻለ እግር ኳስ ለመሄድ በፍፁም
ታማኝነት ቅንነት ልናገለግል ይገባል፡፡ በእርግጠኝነት ትንሽ ጠብ ብናደርግ ብዙ ውጤታማ
ነገሮችን እናመጣለን የሚል እምነቱ አለኝ፤ የሌሎች ሀገሮች እግር ኳስ ተለውጦ የእኛ
የማይለወጥበት ምንም ምክንያ የለም፡፡