በ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የሰባተኛ ቀን ውሎ የግማሽ ፍፃሜ 1 ጨዋታ የተከናወነ ሲሆን ቅ/ጊዮርጊስ እና ተጋባዡ ጅማ አባጅፋር ተገናኝተው ሙሉ የጨዋታ ጊዜውን 0 – 0 በማጠናቀቃቸው በተሰጡት መለያ ምቶች ቅ/ጊዮርጊስ አሸናፊ በመሆን ፍፃሜውን መቀላቀሉን አረጋግጧል።
11:00 ይጀምራል ተብሎ 11:15 ላይ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንደተለመደው በድንቅ የደጋፊዎች ዝማሬና ጭፈራ የታጀበ ሲሆን እስከ 29ኛው ደቂቃ ድረስ ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሳይታይበት ቆይቷል። 29ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ከቀኝ በኩል ያሻገረውን ቅጣት ምት ሙሉዓለም መስፍን(ዴኮ) በግሩም ሁኔታ በግንባሩ የገጨውን ኳስ የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል ኢጄ በቀላሉ ይዞታል። 41ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ እንዳለ ደባልቄ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። የመጀመሪያው ግማሽ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት ዮናስ ገረመው በድንቅ ሁኔታ የመታውን ኳስ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ለዓለም ብርሀኑ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበት የመጀመሪያው ግማሽ መጠናቀቂያ ሆኗል።
ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረገው ተጋባዡ ጅማ አባጅፋር 62ኛው ደቂቃ ላይ በሄኖክ አዱኛ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ በኩል ወጥቷል። 65ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አማካይ በኀይሉ አሰፋ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አዳነ ግርማ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
78ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ከቀኝ በኩል ያሻገረውን ቅጣት ምት አዳነ ግርማ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ የገጨው ኳስ በግቡ ቋሚ በኩል ወጥቷል።
በጨዋታው 82ኛ ደቂቃ ላይ የአ/አ ስታዲየም መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ጨዋታው ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ከ 22 ደቂቃዎች ቆይታ በኀላ በድጋሚ ተጀምሯል።
ጨዋታው ያለምንም ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት አምርቶ በቅ/ጊዮርጊስ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በቅ/ጊዮርጊስ በኩል አዳነ ግርማ፣ አበባው ቡጣቆ፣ ሰለሀዲን በርጌቾ እና አብዱልከሪም ዞኮ የመቷቸውን 4 ፍፁም ቅጣት ምቶች ማስቆጠር ሲችሉ በጅማ አባጅፋር በኩል ሄኖክ ኢሳያስ እና በድሩ ኑርሀሰን ማስቆጠር ቢቺሉም ሳምሶን ቆልቻ እና ኤልያስ ኢታሮ የሳቷቸው ኳሶች ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎት ወደ ፍፃሜው ማለፍ ተስኖታል።
በጨዋታው ጥሩ ብቃት ያሳየው የጅማ አባጅፋሩ አማካይ ዮናስ ገረመው የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
መርሃ ግብሩ ነገ(ሐሙስ) ሲቀጥል 11:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የሚገናኙ ይሆናል። የሁለቱ ቡደኖች አሸናፊ እሁድ ቅ/ጊዮርጊስን የሚገጥም ሲሆን ተሸናፊው ቡድን ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ጅማ አባጅፋርን የሚገጥም ይሆናል።
የኮከብ ተጫዋቹ ፎቶ ምንጭ የአ/አ ሲቲ ካፕ ፔጅ