በሽቶ ሚድያ ፕሮዳክሽንና በትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኣዘጋጅነት ለኣንድ ሳምንት የተካሄደው ትግራይ ዋንጫ ዛሬ በመቐለ 70 እንደርታና በድሬዳዋ ከተማ መካከል በተካሄደ የፍፃሜ ጨዋታ ተጠናቋል።
ምዓም ኣንበሳዎቹ(መቐለ 70 እንደርታ) ደደቢትን ከገጠመው ቡድን ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ ድሬዎች ሚክያስን በዘነበ ከበደ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ 4-2-3-1 ኣሰላለፍ የተጠቀሙ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታዎች መሃል ሜዳ ላይ በላይ ሆነው ታይተዋል።በተለይ የመጀመርያ 20 ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት መቐለዎች በሃይደር ሸረፋ ኣማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል።የዚህም ውጤት በ19ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻማው ኳስ ሳይጠበቅ ድሬዳዋ መረብ ላይ ኣርፏል።
ከግቡ መቆጠር በተመሳሳይ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ምዓም ኣምበሳዎቹ ጨዋታው ላይ ብዙ ሙከራዎችን ያረገው ሃይደር ሸረፋ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ያሾለከለትን ኳስ ከበረኛው ኣናት ቢልካትም ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ከመስመር ኣድኖበታል።37ኛው ደቂቃ ላይ ቅያሪ ማድረግ የጀመሩት ድሬ ሲላ ኣብዱላሂን በሃይሌ እሸቱ፣ወሰኑ ማዜን በሃብታሙ ወልዴ በመቀየር የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፤የዚህም ውጤት ኢታሞና ኮሚኔ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ፍቃዱ ደነቀ ኣስቆጥሮ ኣቻ መሆን ችለዋል።የመጀመርያ 45 መጨረሻ ላይ መቐለዎች በጋብርኤል መሃመድ ድሬዎች በሃብታሙ ወልዴ ኣማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ኣድርገዋል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለተኛው ኣጋማሽ መቐለዎች ኳሱን ይዘው ሲጫወቱ ድሬዎች በመልሶ ማጥቃት ሲያጠቁ ነበር።በግራ መስመር በተሰለፈው ኣማኑኤል ላይ ትኩረት ያደረገው የመቐለ ማጥቃት እንቅስቃሴ የድሬን የተከላካይ ክፍል ሲፈትን ነበር።በ57ኛው
ደቂቃ ከግራ መስመር ኣማኑኤል ያሻማውን ኳስ ጋብርኤል መሃመድ በደረቱ ገጭቶ መቐለ 70 እንደርታን መሪ ቢያደርግም ከሁለት ደቂቃ በኃላ ከማእዘን ምት ዘነበ ያሻማው ኳስ ሶፈንያስ ቢመልሰውም ቅርብ የነበረው ሃብታሙ ወልዴ ኣስቆጥሮት ድሬን በድጋሚ ኣቻ ኣድርግዋል።
በግራ መስመር ሚደረገው የመቐለ ማጥቃት እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን ኣማኑኤል ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ራሱ ኣማኑኤል ኣሻምቶት ኣንተነህ ገ/ ክርስቶስ ኣስቆጥሮ መቐለን በጨዋታው ለሦስተኛ ጊዜ መሪ ማድረግ ችሏል።የዮውሃንስ ሳህለ ቡድን ድሬ የኣቻነትን ግብ ለማግባት ተጨዋቾችን በመቀየር ውጤቱን ለመቀየር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።መደበኛ ጨዋታ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ተቀይሮ በገባው ኦሰይ ማውሊ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ጨዋታው ላይ ጥሩ
ሲንቀሳቀስ የነበረው ኣማኑኤል ኣስቆጥሮ የመቐለ 70 እንደርታ መሪነትን ወደ 4ለ2 ከፍ በማድረግ ጨዋታው በምዓም ኣንበሳዎቹ ኣሸናፊነት ተጠናቋል።ለደረጃ በተካሄደው ጨዋታ ደደቢት ሽሬ እንዳስላሴን በፍፁም ቅጣት ምት 4ለ3 በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ኣጠናቀዋል።
ውድድሩ ላይ የተሰጡት የኮከብ ሽልማቶች :-
ኮከብ ኣሰልጣኝ፡ ገ/መድህን ሃይሌ (መቐለ ከተማ)
ኮከብ ተጨዋች፡ ሃይደር ሽረፋ (መቐለ ከተማ)
ኮከብ ግብ ጠባቂ፡ ረሺድ ማታውሲ (ደደቢት)
ኮከብ ተከላካይ፡ ፍቃዱ ደነቀ (ድሬደዋ ከተማ)
ኮከብ የመሃል አማካይ ተጨዋች፡ ጋብርኤል መሃመድ (መቐለ ከተማ)
ኮከብ ኣጥቂ፡ ራምኬል ሎክ (ድሬደዋ ከተማ)
የህወሓት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳ የመቐለ 70 እንደርታ ቡድንን ሲደግፉ!