የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ለድሬዳዋ ስፖርት ዕድገት አሰተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት የምስክር ወረቀት ዕውቅናና ሽልማት አበርክቷል፡፡
የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከድር ጁሃር የድሬዳዋ ስፖርት እንዲያድግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሽልማት በሰጡበት ወቅት የስፖርት ኮሚሽኑ ያበረከተው የገንዘብ፡የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ዕውቅናና ሽልማት በሕይወት ላሉና ለስፖርት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተው በህይወት ለሌሉትም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን ዕውቅናና ሽልማቱን በሰጠበት ወቅት ለስፖርቱ ዕድገት ከ1968 ዓ/ም እስካሁን ድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አሰልጣኞች፡ተጨዋቾች ዳኞችና አመራሮች እንዲሁም ለሌሎች ባለድርሻ አካላት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
- ማሰታውቂያ -
የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን ከድሬዳዋ ስፖርት ዕድገት ባሻገር ለሀገራችን ስፖርት ባለውለታ ናቸው በሚል እውቅናና ሽልማት ካበረከተላቸው መካከል ለቅዱስ ጊዬርጊስና ለምድር ባቡር እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ፍስሃ በጋሻው፡ለምድር ባቡር የተጫወተው ዘካሪያስ አሊ፡አሁን በህይወት የሌለው አሰግድ ተስፋየ እና የቀድሞ የከተማዋ ከንቲባ የነበሩት አቶ አበበ እሸቴ ይገኙበታል፡፡
በድንገተኛ ሞት የስፖርት ቤተሰቡን መሪር ሀዘን ውስጥ ከቶ ያለፈውን የቀድሞ የድሬዳዋ ኮካኮላ፡የቅዱስ ጊዬርጊስ፡የመድንና የቀድሞው ቡና ገበያ፡ያሁኑ ኢትዮጵያ ቡና በአጠቃላይ ለ4 ክለቦች ለ16 ዓመታት የተጫዎተው የ”አሰጌ ስፖርት አካዳሚ” መስራች የነበረውንና ሁሌም በኢትዮጵያውያን ልብ የማይዘነጋው አሰግድ ተስፈዬ በህይወት ባይኖርም ለስራዎቹ ስፖርት ኮሚሽኑ ዕውቅና መስጠቱ የሚያስመሰግን ነው፡፡
የስፖርት ኮሚሽኑ ለሽልማቱ ከ240 ሺ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ዕውቅናና ሽልማት ሲሰጥ ለድሬዳዋ የስፖርት ዝናና ታዋቂነት የደከሙ አካላት ዛሬ ዕውቅና ሽልማት የተበረከተላቸው ብቻ ባለመሆናቸው በቀጣይ ሌሎችንም ዕውቅናና ሽልማት ለመስጠት ኮሚሽኑ እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆን ዛሬ የተሰጠው ዕውቅናና ሽልማት ለቀጣኝ ጊዜያት ትልቅ ተነሳሽነትን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተነግሯል፡፡
በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ሽልማቱን የሰጡት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ የዛሬው ዕውቅናና ሽልማቱ የቀድሞ የድሬዳዋን ገናና የስፖርት ስም ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እንደሚያግዝ ሲገልፁ የከተማ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው ለተሸላሚዎች ዛሬ ሽልማቱን ያገኙት አካላት ለድሬዳዋ ስፖርት ትንሳኤ ያላቸውን ልምድ እንዲያካፍሉ ጥሪ መልዕክትም ጥሪም አስተላልፈዋል፡፡