በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ጊዮርጊስ
በፎርፌ ወደቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡
፡ የደቡብ ሱዳኑ ዋኡ አልሰላም ፎርፌ
በመስጠት የገንዘብና የእገዳ ቅጣት ከካፍ
እንደሚተላለፍበት ይጠበቃል፡፡ ያም ሆኖ
ጊዮርጊሶች ከጨዋታው ሊያገኙ የሚገባቸውን
ወደ 1.3 ሚሊየን ብር አካበቢ ሳያገኙ
መቅረቱ አበሳጭቷቸዋል፡፡ ቡድኑም ያሰበውን
የዝግጅትና ወቅታዊ አቋም ማየት አለመቻሉን
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ለሀትሪክ ተናግሯል፡፡
ዮሴፍ ከፈለኝ ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር
ባደረገው ቆይታ ስለፎርፌው፣ ስለፈረሙት
አዳዲስ የውጪ ተጨዋቾች፣ ከደጋፊዎች
ጋር ስላለው ልዩነት፣ ወልዋሎዎች
ስላቀረቡለት የአሰልጥነን ጥያቄና ሌሎች
ጉዳዮች ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ከዝግጅቱ እንጀምርና…
የልፋታችሁን ውጤት እንዳታዩ ማድረጉን
እንዴት አየኸው?
ፋሲል፡- ከድሬደዋ ጋር ካደረግነው
ጨዋታ በኋላ ሙሉ ትኩረት ሰጥተን ለዚህ
ጨዋታ ተዘጋጅተናል፡፡ ነገር ግን ጨዋታው
መቅረቱ በተለይ ለሻምፒዮንስ ሊግ
ያስፈረምናቸው ተጨዋቾች የማየት እድል
አሳጥቶናል፡፡ ቡድኑ በመቅረቱ አቋማችንን
ማየት ባንችልም ወደቀጣዩ ዙር የማለፍ
ፍላጎታችን ግን አሳክተናል፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን የፈረሙት ተጨዋቾች
በርግጥ በትክክለኛው የመመልመያ መስፈርት
ያለፉና የተሻሉ ተጨዋቾች ናቸው ማለት
ይቻላል?
ፋሲል፡- ብዙ የምናስፈርመው
ተጨዋቾች በምንሰጣቸው የሙከራ ጊዜ
ክለባችንን በመቀላቀል በሚያሳዩን አሳማኝ
አቋም ተንተርሰን ነው፡፡ በትክክለኛው
የጨዋታ ሂደት አይተን የማስፈረም እድላችን
ግን ጠባብ ነው፡፡ በመሆኑም የአንዳንዶቹ ሊሳካ
የሌሎቹ ላይሳካ ይችል ይሆናል፡፡ የአሁኖቹን
በተመለከተም መገመት ይከብዳል ነገር ግን
በልምምድ አይተናቸው ተቀብለናቸዋል ዋናው
ግጥሚያ ላይ ምን ያህል ስኬታማ ይሆናሉ
የሚለውን ግን ከጨዋታው በኋላ የምንናገረው
ነው የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፎርፌው ይበልጥ ጠቀመ ወይስ
ጎዳ?
ፋሲል፡- ተጫውቶ በማሸነፍና በፎርፌ
ወደቀጣዩ ዙር ማለፍ ይለያያል፡፡ በራስ
መተማመን ፈጥሮ ደካማ ጎንን ለማረም
ጠንካራ ጎንን የበለጠ ለማጠናከር ጨዋታውን
ቢካሄድ ይጠቅመን ነበር፡፡ በተለይ የሙሉ
ተጨዋቾቻችንን የሻምፒዮንስ ሊጉ የአዕምሮ
ዝግጅት ለማየት አልታደልንም፤ በርግጥ
በፎርፌ ማለፍ ከላይ ባልኩት ምክንያቶች
ጥሩም መጥፎም ገጠመኞች ይኖረዋል፡፡
ሀትሪክ፡- በተጨዋችነህ ዘመንህ ይህ
ክስተት ገጥሞህ ያውቃል?
ፋሲል፡- አዎ 1992 ይመስለኛል፡
፡ ከቪታሎ ጋር ተገናኘንና ከትራንስፖርት
ጋር በተያያዘ መምጣት ባለመቻላቸው እሁድ
መካሄድ የነበረበት ጨዋታ ወደ ሰኞ ተዛወረ፡
፡ ለኛ ጥሩ መስሎን ነበር፡፡ ሰኞ መሆኑ ግን
ትኩረታችንን እንድናጣ አድርጎናል፡፡ 1ለ0
እየመራን ከነርሱ አንድ ተጨዋች በቀይ
ካርድ ወጥቶ ጨዋታው ሲያልቅ ግን 2ለ1
ተሸንፈናል፡፡ ትኩረት ሰብስቦ ያለመምጣት
ችግር ዛሬም አስፈርቶኝ ነበር፡፡ የተጨዋች
ትኩረት ካልተሰበሰበ ጨዋታው ሊከብድ
ይችል ነበር ብዬም ሰግቼ ነበር፡፡ እንኳን
ለነርሱ ለኛም አስቸጋሪ ይሆንብን ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ይህ ክስተት ስለምስራቅ አፍሪካ
የሚነግረን ነገር አለ?
ፋሲል፡- ከምዕራብም ሆነ ከሰሜኖች ጋር
ለመፎካከር በፋይናንስም ሆነ በአደረጃጀት
ብዙ መስራት የሚጠበቅበት ዞን መሆኑ
ያመለክታል፡፡
ሀትሪክ፡- ከሻምፒዮንስ ሊጉ ወይም
ከፕሪምየር ሊጉ የጊዮርጊስ ማህበረሰብ ፍላጎት
የቱ ይመስልሃል?
ፋሲል፡- የሻምፒዮንስ ሊጉ ጣራ ላይ
መድረስ የሁላችንም ህልም ነው፡፡ እግር ኳስን
የሚወድ ሰው በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ላይ
መገኘትን ይወዳል፡፡ ነገር ግን የሻምፒዮንስ
ሊጉ ዋንጫን ዘንድሮ አንስቶ በቀጣዩ አመት
በውድድሩ መካፈል ካልተቻለ ከክብርም አንፃር
ልክ አይደለም፡፡ ከሻምፒዮንስ ሊጉ አንፃር ብቻ
አይደለም እንደ ኢትዮጵያ ሊጉ ክብራችን
ነው፡፡ የሊጉም ሻምፒዮን መሆን ክብራችን
ነው ሊጉን እኛ ከፍ አድርገን ካላጎላነው ማን
ሊያከብረው ይችላል ለዚህም ነው ከሁለት
አንዱን መምረጥ ያቅተኛል የምለው፡፡
ሀትሪክ፡- ካሉት ተጨዋቾች አንፃር
ጊዮርጊስን በሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ
ወይም ለፍፃሜ መጠበቅ ይቻላል?
ፋሲል፡- ቀጣዩን ጨዋታ ካለፍን 16ቱ
ውስጥ እንገባለን፡፡ 16ቱ ውስጥ ደግሞ እነማን
እንደሚገጥሙን አይታወቅምና ለመገመት
አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለፈው አመት ከባድ ምድብ
ውስጥ ነበርን፡፡ የገጠምነው በፋይናንስ፣
በተጨዋቾች ጥራትና በአደረጃጀት ከኛ የተሻሉ
ቡድኖች ነው፡፡ ችለንና እግዚአብሄር ፈቅዶልን
ድልድል ውሰጥ ከገባን እነማን ይገጥሙናል
አናውቅም፡፡ ተጨዋቾቻችን በዚህ ውድድር
ላይ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ተነሳሽነታቸው
ላቅ ያለ ነው፡፡ መገመት ባይቻልም አንድ ቦታ
ለመድረስ ትሰራለህ፡፡ እኛም ትላልቅ ቡድኖችን
ነው የምንገጠመው በሚል ፍርሃት ማሳካት
የምንፈልገውን ህልም አንተውም ዛሬም
ነገም እንሞክራለን፡፡ ስለሞከርን 16 ውስጥ
ገብተናል ስንሞክር ደግሞ 8ቱ ውስጥ ልንገባእንችላለና ዘንድሮ ለተሻለ ውጤት እንተጋለን
ብለን ተዘጋጅተናል፡፡
ሀትሪክ፡- ዛሬ ሜዳ ውስጥ በፎርፌ ማለፋችሁ
ከታወቀ በኋላ ልምምድ ስትሰሩ አንድ ደጋፊ
ዘሎ ወደሜዳ ገብቶ ያወራህ ጉዳይ ምንድነው?
(ቃለ-ምልልሱ የተደረገው እሁድ ምሽት ነው)
ፋሲል፡- ሊያቅፈን ነው የገባው፡፡ እኔንም
ዘርዬንም ነው ያቀፈን ስሜታዊ ሆኖ እያለቀሰ
ነው ያወራን፡፡ በጣም እወዳችኋለሁ ለኔ ክብሬ
ናችሁ እያለ ነው ያቀፈን፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲልና ዘሪሁን ቡድኑን እያሳመፁ
ስለሆነ ነው ጥሩ ሆነን የማንቀርበው የሚሉ አሉ
በተቃራኒው ደግሞ የሚወዷችሁም ደጋፊዎች
አሉ እዚህ ላይ ምንድነው የምትለው?
ፋሲል፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን የመሰለ
ትልቅ ቡድን እየመራህ ጥሩ ውጤት ወይም
ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲጠፋ ደጋፊው
መቃወሙ የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን
ስሜት የሚነካ ጉዳይ ይገጥምሃል አንዳንዶች
በደንብ አያውቁንም ማለት ነው እኔና ዘርዬ
በዚህ አይነት ባህሪ ውስጥ የለንበትም፡
፡ ተጨዋቾችም ቢሆኑ ትላልቆች ናቸው፡
፡ ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ ምን እንደሚያገኙ
ይረዳሉ፣ ጊዮርጊስ ቤት ውስጥ የሚቆዩት
በማሸነፍ ብቻ እንደሆነ የሚረዱ ናቸውና
ውጤት እንዳያመጡ መምከር አይቻልም፡
፡ ጊዮርጊስ ቤት ውስጥ ያለ አሰራር ግልፅ
ያለና ሁሉም ሰው የሚያውቀው በመሆኑ
ሊጭበረበር የሚችል ነገር የለም፡፡ ጊዮርገስ
ጥሩ እንዳይጫወት ለማድረግና ለማሳመፅ
የሁለታችንም ፐርሰናሊቲ አይፈቅድም ይሄን
ሁሉም ቢያውቁ ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ተጨዋቾች እየጠጣን ነው
የምንጫወተው ማለታቸው የአሰልጣኞችን
ደካማ የቁጥጥር ስርአት ያሳያል የሚሉ ወገኖች
አሉና ምላሽህ ምንድነው?
ፋሲል፡- መጀመሪያውኑ መታወቅ ያለበት
የኛ ሃላነፊነት የም/ል አሰልጣኝነት ነው፡፡
ሃላፊነቱ ደግሞ ዋናውን አሰልጣኝ መርዳትና
ተጨዋቾች አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ ማገዝ
ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ተጨዋቾችን እየተከታተልን
የምንጠብቅ አይደለንም፡፡ የዲሲፕሊን ስህተት
ስናይ በክለቡ ህግ መሰረት ይዳኛሉ እንጂ
እየተከታተልን ልንጠብቅ አንችልም፡፡ ይሄ
የሙያ ስነ-ምግባራችንም አይፈቅድም ቦታው
ላይ ያለነውም ለዚህ ስራ አይደለም፡፡ ጥፋት
ሰርተው ከተገኙ ሪፖርት አድርጎ ማስቀጣት
የዋናው አሰልጣኝ በሪፖርቱ መሰረት
ደግሞ መቅጣት የቦርዱ ሃላፊነት ይሆናል፡
፡ ተጨዋቾች ከጨዋታ ቀን በፊት አንድ ቀን
ቀድመው ካምፕ ገብተው የማደር ሃላፊነት
አለባቸው፡፡ እንደ አሰልጣኝ ደግሞ ይሄንን
እንከታተላለን፡፡ ከዚያ ውጪ በየመዝናኛ
ስፍራ ሄደን ልንከታተላቸው አንችልም፡፡ ነገር
ግን መናገር የምፈልገው እኔም ሆንኩ ዘርዬ
የቡድኑን ስሜት የሚነካ ወይም የሚጎዳ ነገር
አይተን ዝም እንላለን ማለት ለእኔ የሚያስቅ
ድርጊት ይሆንብኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ሽንፈት ሲመጣ ብቻ በተለየ
መንገድ ስማችሁ እየተጠራ ለመሰደባችሁ ያንተ
ምላሽ ምን ይሆን?
ፋሲል፡- ሁሉም ሰው የየራሱ ሃላፊነት
አለው፡፡ ነገር ግን እኔና ዘርዬ ቡድኑ በተሸነፈ
ቁጥር በተለየ ምክንያት የምንጠየቅበት
ሁኔታ ተገቢ አይደለም፡፡ ቡድኑ ሲያሸንፍ
የምንሞገሰውም ሆነ ሲሸነፍ የምንተቸው
በደረጃችን መሆን አለበት፡፡ ሰዎች ሲተቹም
ሆነ ጥያቄ ሲያቀርቡ ምክንያታዊ ቢሆኑ
በጣም ደስ ይለኛል፡፡ የምንለፋውና
የምንታገለው ሁሉም ደጋፊ የሚደሰትበትን
ውጤታማውን ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ለማሳየት
ነው ለዚህ ደግሞ አንድና አንድ መፍትሔ
ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው፡፡ ጠንክረን
እንሰራለን፡፡ ደጋፊዎቻችን ሁልጊዜም
ከሜዳ የሚወጡት ተደስተው ቢሆን ደስ
ይለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የምንችለውን ሁሉ
እናደርጋለን፡፡
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ጥያቄ… ከወልዋሎ
ጋር ስምህ እየተያያዘ ነውና ምን ላይ
ደረሳችሁ?
ፋሲል፡- (ሳቅ) የወልዋሎ አመራሮች
እኔን በዋና አሰልጣኝነት ሊቀጥሩኝ
እንደሚፈልጉ ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን
በተለያዩ ምክንያቶች ጥያቄውን ሳልቀበል
ቀርቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከጊዮርጊስ ምክትል የወልዋሎ
ዋና አሰልጣኝ መሆን አይሻልም? ላንተስ ሲቪ
የተሻለው የወልዋሎ ሹመት አይደለም? ወይስ
ከጊዮርጊስ ጋር ያለህን የጠበቀ ግንኙነት
ላለማጣት ነው?
ፋሲል፡- ሁሉም ሰው የየራሱ
አስተያየት አለው፡፡ ጊዮርጊስ ለእኔ የቤቴ
ያህል ነው፡፡ አድጌበታለሁ ለትልቅ ደረጃም
ደርሼበታለሁ፡፡ ምንም ጥያቄ የሌለው ነገር
ግንኙነታችን ቤተሰባዊ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ
የራሴ የሆነ ህልም አለኝ፡፡ በርግጠኝነት
መናገር የምፈልገው የአገሪቱ ትልቅ
አሰልጣኝ የመሆን ህልም ቢኖረኝም ለጊዜው
ግን በተለያዩ ምክንያቶች የወልዋሎን ጥያቄ
አልተቀበልኩም፡፡ አንድ ቀን ይህን ህልሜን
እንደማሳካ ርግጠኛ ነኝ፡፡
“አቋማችንን ማየት ባንችልም ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ፍላጎታችንን አሳክተናል”አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ (ቅ/ጊዮርጊስ)
Hatricksport team