በአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው የአለማችን ታላላቅ ውድድሮች ብቸኛ የሆነው የኦታዋ የ10 ኪ.ሜ ዓመታዊ የሩጫ ውድድር ትናንት ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፃታዎች ተቀናቃኞቻቸው የሆኑት ኬንያውያንና የሌላ ሀገር አትሌቶችን አስከትለው በመግባት እሸነፋ።
በሴቶች በተካሄደው የ10 ኪ.ሜ ሩጫ ሰባት ኪ.ሜትር ሲቀር ብቻዋን አፈትልካ የወጣችው ነፃነት ጉደታ 31:35 በሆነ ሰዓት በመግባት ነው ያሸነፈችው።በውድድሩ ከፍተኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት ኬንያውያን አትሌቶች ፓስካላ ቺፕኮሪዬርና ሞኒካ ኒጄ 32:08 እና 32:46 በመግባት እንደየቅደምተከላቸው ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ሲያጠናቅቁ ሌላዋ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣት አማኒ ጎበና 33:09:45 በመግባት አራተኛ ሆና ውድድራን አጠናቃለች።
የኦታዋ ማራቶን የ2017 የ10ኪ.ሜትር የሴቶች ውድድር አሸናፊ በመሆን ስምዋን በታሪክ መዝገብ ላይ ያሰፈረችው አትሌት ነፃነት ጉደታ ከውድድሩ በኃላ ለሚዲያ ሰዎች እንደተናገረችው ውድድሩን እንደጠበቀችው እንዳሸነፈች ገልፃ አየሩም የመወዳደሪያ ቦታው ምቹ መሆንና በቂ ዝግጅት ማድረግዋ ለድል እንዳበቃት ተናግራለች።
“ሁሌም በሩጫ ላይ እያለሁ ወደ ኃላ በመመልከት የተፎካካሪዎቼን ሁኔታ የመከታተልና የመቆጣጠር ልምዱ አለኝ ይህ ደግሞ ለውጤታማነቴና ለሰዓቴ ትልቅ ጥቅም ይሰጠኛል”ያለችው ነፃነት ውጤቱ ከፊትዋ ለሚጠብቅዋት ታላላቅ ውድድሮች ላይ የሀገርዋን ስም ከፍ አድርጋ ለማስጠራት ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ጉልበት እንደሚሆናት በአስተያየትዋ መጨረሻ ገልፃለች።
የ26 ዓመትዋ የ2015ቱ የIAAF ክሮስ ካንትሪ ብሮንዝ ሜዳሊያን ለግልዋ ሀገርዋ በቡድን የወርቅ ተሸላሚ እንድትሆን ያደረገችው ነፃነት የኦታዋ ማራቶን የ10k አሸናፊ በመሆንዋ የ10ሺ የካናዳ ዶላር ተሸላሚም ሆናለች።