የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ አንድ ጨዋታ ዛሬ ተደርጓል። በጨዋታውም ኢትዮጵያ ቡና ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ ያለግብ አቻ ሊለያይ ችሏል።
እንደ ቀድሞ በደጋፊዎች መሙላት ሳይችል የተከናወነው ይህ ጨዋታ ግቦች ሳይታዩበት 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። አዲሱ የዋጋ ጭማሪ ከሜዳ ብዙ ደጋፊዎችን እያሸሸ እንደሆነ የዛሬው እና የትናንቱ የሸገር ክለቦችጨዋታ ማሳያ መሆን ይችላል። በተለምዶ ዳፍ ትራክ እና ካታንጋ ተብለው የሚታወቁት ቦታዎች ባዶ ሆነው ታይተዋል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለቱም ቡድኖች የውድድር አመቱን የመጀመሪያ 3ነጥብ ለማግኘት ያደረጉት ጨዋታ እንደመሆኑ ማራኪ ጨዋታ ይታይበታል ተብሎ በደጋፊው ቢጠበቅም ጨዋታው ግን አልፎ አልፎ ከሚታዩ ሙከራዎች በስተቀር ይህ ነው የሚባል ጨዋታ አልነበረም። ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ በአጥቂው አቡበከር ናስር የሞከሩት ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። በተደጋጋሚ ኳስ መነጣጠቅ የታየበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ኳስ ይዞ ለመጫወት ጅማ አባጅፋር ደግሞ ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ሲጥሩ ተስተውለዋል። 22ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ኤርሚያስ ጥሩ ኳስ አግኝቶ ቢሞክርም ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። 33ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አስራት ቱንጆ መሬት ለመሬት የሞከረው ኳስ ለጎል የቀረበ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላም አማኑኤል ዮሐንስ የሞከረው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ኢትዮጵያ ቡና በተደጋጋሚ ወደ ጅማ አባጅፋር የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይም ኢትዮጵያ ቡና ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲሞክር ጅማ አባጅፋር በአንፃሩ ወደኋላ በማፈግፈግ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክሩም የተገኙትን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም። በሁለተኛው አጋማሽ ደጋፊውን የሚያዝናና እና ይህ ነው የሚባል ምንም አይነት ሙከራ ሳይደረግበት መጠናቀቅ ችሏል። ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና የውድድር አመቱን የመጀመሪያ ነጥብ ሲያገኝ ጅማ አባጅፋር ደግሞ ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ አቻ ወጥቷል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ቡና በ1ነጥብ እና በ1 የግብ እዳ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ጅማ አባጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና በ1ነጥብ ከፍ ብሎ በ2ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ሊጉን ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለውና በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው ወልዋሎ አ.ዩ. በ6 ነጥብ እና በ3 ንጹሕ ግብ መሪነቱን ሲይዝ ፋሲል ከነማ፣ ሐዋሳ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ቅ/ጊዮርጊስ በእኩል 4ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ2ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ወልቂጤ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለምንም ነጥብ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም እና የወልዋሎ አ.ዩ. ሰመረ ሐፍተይ በእኩል 3ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሲመሩ ሽመክት ጉግሳ፣ ካርሎስ ዳምጠው፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ አዲስ ግደይ እና ዲዲየር ሊብሬ በእኩል 2ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።