በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻም
ፒዮናው ፋሲል ከነማ የቅድመ
ዘመን ዝግጅቱን መቀመጫውን
ባህር ዳር ላይ አድርጎ እየሰራ ይገኛል፤
ፋሲሎች ለዘንድሮ የውድድር ዘመን
ተሳትፎአቸው ጠንካራ ልምምድን በአዲሱ
አሰልጣኛቸው እያከናወኑ ሲሆን ሰሞኑን
ደግሞ በኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ
ጨዋታ ላይ መቐለ 70 እንደርታን
ለሚፋለሙበት ጨዋታ የመለማመጃ ሜዳ
ካገኙ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡና
እንደሚለማመዱ መረጃዎች እየወጡ
ይገኛል፤ ፋሲል ከነማ በፕሪ-ሲዝኑ እያደረገ
ስላለው ዝግጅትና ሌሎች ተያያዥ
ጥያቄዎችን አንስተን ለክለቡ ተጨዋች
አምሳሉ ጥላሁን ጥያቄን ያቀረብንለት
ሲሆን ተጨዋቹም ምላሹን በሚከተለው
መልኩ ሰጥቶናል፡፡
ስለ ፕሪ-ሲዝን ዝግጅታቸው
“ፋሲል ከነማ በባህር ዳር ከተማ
እያከናወነ ያለው የቅድመ ዝግጅት ልምምዱ
በጣም ጥሩ ሲሆን ሁሉንም ነገር ባሟላና
ብቁ በሆነም መልኩ ነው በቀን ሁለት
ጊዜ እየሰራ የሚገኘው፤ ጠዋት ጠዋት
የጂምናዝየም ከሰዓት ከሰዓት ደግሞ
ለመለማመጃ ምቹ በሆነ ሜዳም ላይ ነው
ከኳስ ጋር የተያያዘን ስራ እያከናወንን
የምንገኘው”፡፡
ፋሲል ከነማ ከአምናው አንፃር ዘንድሮ
በምን መልኩ ለመቅረብ እንደተዘጋጀ
- ማሰታውቂያ -
“እኛ ፋሲሎች በእዚህ ዓመት ለውድድር
የምንቀርበው ከአምናው በጣም በተሻለ
መልኩ እና የተሸወድንበትንም ነገሮች
በማረም ነው፤ ያለፈው ዓመት የውድድር
ተሳትፎአችን ላይ ቡድናችን ከተከታዮቹ
ቢያንስ በ10 ነጥብ በልጦ ወደፊት
መጓዝ እና ሊጉንም እየመራ ውድድሩን
በሻምፒዮናነት ማጠናቀቅ ይችል ነበር፤
ያም ሆኖ ግን ክለባችን ዋንጫ ማንሳት
ላይ እንደ ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ልምድ ያለው
ቡድን ባለመሆኑ የልምድ እጦት ሊጎዳን
እና ውጤት ሊያሳጣን ችሏል፤ በእዚህ
ዓመት ግን ያን ችግራችንን በመቅረፍ ነው
በልዩ መልኩ ለውድድሩ የምንቀርበው፤ ከዛ
ውጪም የምንታወቅበትን በኳስ ቁጥጥር
ላይ ያመዘነን አጨዋወትም አሁንም
አጠናክረን ይዘን እንመጣለን”፡፡
ስለ ፋሲል ከነማ የዘንድሮ
የተጨዋቾች ስብስብ
“ፋሲል ከነማ አሁን ላይ የያዘው
የተጨዋቾች ስብስብ በጣም ጥሩ እና
ክለቡንም ለተሻለ ውጤት ሊያበቃው
የሚችል ነው፤ በክረምቱ የተጨዋቾች
ዝውውር መስኮት አንድ ልጅን ከመልቀቃችን
በስተቀር ብዙዎቹ ተጨዋቾች አሁንም ድረስ
አብረውን አሉ፤ ከዛ ውጪም የቡድናችን
ስኳድ ያልፈረሰና ሌሎችም እኛን ሊጠቅሙ
የመጡም ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ስላሉ
የእዚህ ዓመት ስብስባችንን በጣሙን ነው
እየወደድኩት ያለሁት”፡፡
የአዲሱ አሰልጣኛቸው ስዩም ከበደን
የአጨዋወት ፍልስፍና ከቀድሞ
አሰልጣኛቸው ውበቱ አባተ ጋር ሲያነፃጽሩት
“የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብን
ለማሰልጠን ወደ ቡድናችን የመጣው
አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የአጨዋወት
ፍልስፍና ከውበቱ አባተ ጋር ሲነፃፀር በጣም
ተመሳሳይና አንድ አይነት ነው፤ በሁለቱ
መካከል የተለየ ነገርም የለም፤ ሁለቱም
ከኳስ ጋር የተያያዘ ስራን ነው የሚያሰሩት፤
በአጨዋወትም በኳስ ቁጥጥር ተጋጣሚን
የሚበልጥ እንቅስቃሴን ነው የሚጠቀሙትና
ይሄ መሆኑ ለእኛ በጥሩነቱ ነው መታየት
ያለበት”፡፡
ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በቅርቡ
ስለሚኖራቸው የአሸናፊዎች አሸናፊ
ጨዋታ
“ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር የሚኖረን
የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ በሁለታችንም
ክለቦች መካከል በጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን
ይህ ፍልሚያም ከወዲሁ ሌላ ትርጉም
ባይሰጠው በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ እኛና
መቐለዎች የምናካሂደው ጨዋታ እግር
ኳስ የሰላም መሆኑን የምናረጋግጥበት ነው
ሊሆን የሚገባው፤ እግር ኳስ ማስታረቂያ
እንጂ ማጣያ መሆንም የለበትም፤ ሰላማዊ
ጨዋታ ብናደርግም በጣም ደስ ይለኛል”፡፡
ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በሚኖራቸው
ጨዋታ ምን ውጤትን እንደሚያስመዘግቡ
“ፋሲል ከነማ ከመቐለ 70 እንደርታ
ጋር በሚኖረው ፍልሚያ ዞሮ ዞሮ ወደ
ሜዳ የሚገባው ጨዋታውን ለማሸነፍ
ነው፤ ክለባችን በእዚሁም ተጠባቂ ጨዋታ
ዋንጫን አይቶ የሚመለስ ስላልሆነ ባለድል
እንደምንሆን እርግጠኛ ነኝ”፡፡
እንደ ፋሲል ከነማ ተጨዋችነቱ
በእዚህ ዓመት በምን መልኩ ለመቅረብ
እንደተዘጋጀ
“ፋሲል ከነማ በሚያደርጋቸው
ማንኛውም የዘንድሮ የውድድር ዘመን
ጨዋታዎች ፈጣሪ ጤንነቱን ይስጠኝ
እንጂ ከወዲሁ ራሴን በልዩ መልኩ ነው
እያዘጋጀሁት የሚገኘው፤ በተለይ ደግሞ
ዓምና ጥሩ ከነበርኩበት አቋሜ የበለጠ
ተሻሽዬ እቀርባለሁ”፡፡
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጪ
ስለሆነበት መንገድ
“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስኳድ
ከተካተትኩ በኋላ ከዋልያዎቹ የተጨዋቾች
ስብስብ ውጪ የሆንኩት ክለባችን
ከታንዛኒያው አዛም ጋር ተጫውቶ ሲመለስ
ጉዳት አጋጥሞኝ ስለነበር ነው፤ ከዛ ውጪ
ሌላ ምክንያት ፈፅሞ የለም”፡፡
በመጨረሻ….
“ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ አንድ ነገርን
ማለት እፈልጋለሁ፤ በመጀመሪያ የእኛ
ሀገር እግር ኳስ በጣም ማደግ አለበት፤
ኳሱ ሲያድግም አብሮ ሰላምን ይዞ
መምጣት አለበት ብዬ አስባለው፤ ኳሳችን
የሰላም እንጂ የሌሎች ነገሮች ማራመጃም
ሊሆን አይገባውም፤ ኳሳችን ሰላምን ይዞልን
እንዲመጣም ምኞቴን እገልጻለው”፡፡
Photo credit – kebera (KZG)