“እግር ኳሱም ሀገርም ገደል ትግባ፤ ኪሴ ግን ይሙላ የሚሉ በሆዳቸው የሚያስቡ አሰልጣኞች የበዙበት ሀገር ሆናለች”
“ካሳዬ አራጌ በኢት.ቡና በቂ ጊዜ ከተሰጠው የተሻለ ነገር ይሰራል”
“በኔትወርክና በገንዘብ የተጨማለቀው ሲስተም በሙያዬ እንዳላገለግል ገፍቶኛል”
አሰልጣኝ አባይነህ ማሞ (ካናዳ/ቶሮንቶ)
“ካሳዬ አራጌ በኢት.ቡና በቂ ጊዜ ከተሰጠው የተሻለ ነገር ይሰራል”
“በኔትወርክና በገንዘብ የተጨማለቀው ሲስተም በሙያዬ እንዳላገለግል ገፍቶኛል”
አሰልጣኝ አባይነህ ማሞ (ካናዳ/ቶሮንቶ)
በይስሀቅ በላይ
የሚወዳት ሐገሩን ጥሎ የተሻለ የእግር ኳስ ህይወትንና የተሻለ
ኑሮን ፍለጋ በበርካታ ውሀዎች ወደ ተከበበችው በስልጣኔ ጣራ ወደነካችው ካናዳ ኑሮውን ካደረገ ከ24 የበለጡ ወራቶችን አስቆጥሯል፡፡ “ሀገርን ጥሎ መሰደድ” የሚለውን ክፉ ውሳኔ ለመወሰን የማያውቀውን ሌላ የህይወት ፈተና ለመጋፈጥ እንዲሰደድ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ የተሻለ ህይወትን ፍለጋ የሚለው ከፊት ቢቀድምም በሀገሪቱ ውስጥ ያለው በኔትዎርክና በገንዘብ የተጨማለቀው የአሰልጣኞች ቅጥርና ስንብት የሚወዳትን ሀገሩን ጥሎ እንዲሰደድ እስከማስገደድ እንዳደረሰው ይናገራል፡፡ ቀደም ሲል የመድንን ቢ እና ዋናውን ቡድን በማሰልጠን የሚታወቀውና የራሣቸው የጨዋታ ፍልስፍና አላቸው ከሚባሉት ወጣት አሰልጣኞች አንዱ የሆነው አሰልጣኝ አባይነህ ማሞ በቅርቡ ወደ ካናዳ አምርቶ የነበረው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የሚወዳትን ሀገሩን ጥሎ ወደ ካናዳ ያመራውን የቀድሞ የመድን አሰልጣኝ አባይነህ ማሞን ዳውን ታውን Young and Dundas በሚገኘው ፊልም ቤት Food court ላይ ተገናኝተው ለምን ወደ ካናዳ እንደሄደ፣ ስለቀጣዩ ዕቅዱና ስለ ሀገራችን አሠልጣኞች አቀጣጠር ያመነበትን በግልፅ አጫውቶታል፡፡
ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ወጥተህ ኑሮህን
በካናዳ ቶሮንቶ ካደረክ ምን ያህል አመት
አስቆጠርክ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ጊዜው በጣም
አጭር ይመስላል…? አሁን ሁለት አመትን
እንደዋዛ እያሳለፍኩ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ካናዳን እንዴት
አገኘሃት…?…እንዴትስ ተቀበለችህ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ኦው…!…ካናዳ
በጣም ምርጥ ሀገር ናት…፤…ያለምንም
ማጋነን ካናዳ ለእኔ ልክ እንደ ሁለተኛ ሀገሬ
የምቆጥራት በጣም የምትመች ምርጥ ሀገር
ሆና ነው ያገኘኋት፡፡ በተለይ ህዝቡ ያለው
እንግዳ ተቀባይነት…ለሰው ልጅ ያለው
ክብርና ፍቅር ልዩ መገለጫቸው የሆነው
ተባባሪነታቸው ካናዳን የበለጠ እንድትወዳት
ያደርግሃል፡፡ ካናዳዊያን ላይ ያየሁት የተለየ
ነገር የምትጠይቃቸውን ምንም ሳይሰለቹ
ሳይደብቁ ይነግሩሃል፡፡ በካናዳ እንኳን ክቡሩ
የሰው ልጅ እንሰሳቶች እንኳን ፍፁም
የተለየ ቦታና ክብር አላቸው፡፡
ሰው በመሆንህ ብቻ ትልቅ
ክብር አላቸው፤ ከላይ
እንዳልኩህ ከሀገሬ ቀጥላ
ሌላኛዋ ሀገሬ ናት፡፡
ሀትሪክ፡- …ለካናዳ ለባህሏም፣ ለአየሯም ለኑሮውም እንግዳ ነህና በዚህ በኩልስ ካናዳ ተመችታሃለች…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …እውነት ለመናገር መጀመሪያ
ላይ የካናዳ ምድርን እንደረገጥኩ ነገሮች በጣም ከብደውኝ ነበር…፤…የነገሮች ክብደት በካናዳ
የሚጀምረው ደግሞ ከአየር ንብረታቸው ነው፡፡
እንደ አጋጣሚ ወደ ካናዳ የመጣሁት በጃንዋሪ ወር አካባቢ ነበር…ይሄ ወር ደግሞ በካናዳ ከባድ የበረዶ ወቅት ነው፡፡ በረዶን በሀገሬ ባውቅም በዚህ ደረጃ የከበደ በረዶ ይኖራል ብዬ ባለመጠበቄ ለመልመድ በጣም ከብዶኝ ነበር፡፡ ከነገሮች ከባድነት በመነሣት
እንደውም አንዴ…ካናዳ እንደዚህ ናት…?…በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው የምኖረው…?…ብዬ…በጣም ግራ
መጋባት ውስጥ ገብቼ ነበር…፡፡…ግን የምትወዳትን ሀገርህን ጥለህ ወደ ሰው ሀገር የምትሰደደው ለአላማ
በመሆኑ…የሚገጥምህን በሙሉ በፅናትና በጥንካሬ ትቋቋመዋለህ…ደግሞም ታልፈዋለህ…፡፡…እኔም
ያኔ በወቅቱ የማይቻልና በጣም ፈተና የመሰለኝ ወይም የማይገፋ ከባድ ነገር ሆኖ የታየኝን ነገር ዛሬ ተላምጄው ከአየሩ ጋርም ተስማምተን በፍቅርና በደስታ እየኖርኩ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …በኑሮ…ህይወትህ በመለወጡ በኩልስ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …አሁን የማወራህ አጋንኜ አይደለም…፤…አንተም ካናዳን ከሶስት ከአራት ጊዜ
በላይ መጥተህ አይተሃታልና ራስህም ምስክርነቱን ከእኔ
በላይ ልትሰጥ ትችላለህ…(ሳቅ)…ካናዳ ለኑሮ ፍፁም ተስማሚና ምቹ የምትባል ሀገር ናት፡፡ እንደውም አንዳንድ መረጃዎችን ጎግል አድርገህ ብትመለከት ካናዳ
ለኑሮ በጣም ምቹና ሠላማዊ ከሚባሉ ጥቂት
ሀገሮች ተርታ ውስጥ ያለች ሀገር ናት፡፡
ካናዳ ሁሉም በአቅሙ ተደስቶ የሚኖርባት…
የምትፈልገውን የማታጣባት ሀገርም ናት…፡
፡ ሀብታሙም…መካከለኛው ኑሮ ያለው
የሚባለውም በአቅሙ ይኖራል፤ ህይወቱን
ያቆያል፡፡ በካናዳ የሰው ልጅ እኩል ነው፤
በሰው ዘር መካከል ልዩነት ሲደረግ አታይም፡
፡ በአብዛኛው በካናዳ ነዋሪ የሆነው በትውልድ
የሌላ ሀገር ስደተኞች ቢሆኑም በካናዳ ግን
ከዜጋው እኩል የሚኖርባት ሀገር ናት፡፡ እኔ
ወደ ካናዳ ከመጣሁ አጭር ጊዜ ቢሆንም
ራሴን ለመቻል ብዙም ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡
የሞላኝ የተረፈኝ ገንዘብ ላይ የተኛሁ ሰው
ሆኛለሁ ባልልም የተሻለ ህይወትን ማጣጣም
እንደጀመርኩ ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም፡፡
ሀትሪክ፡-መቼም በውጪ የሚኖሩ
ኢትዮጵያዊያንን ሥራህ ምንድነው ብሎ
መጠየቅ የነውር ያህል የሚታይ…መልስ
የማይገኝለት ጥያቄ ነው ቢባልም…ደፍሬ
ስራህ ምንድነው…?…ብዬ ብጠይቅህ
ትመልስልኛለህ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …(በጣም ሳቅ)
…እኔ በዚህ አላምንም…የምሰራውንም
መናገር አይከብደኝም…፤…በካናዳ በሁለት
ነገሮች ላይ ተሳማርቼ ነው ያለሁት…
አንደኛው በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ
ቀን ቀን የተወሰኑ ሰዓቶችን እሠራለሁ…
ከስራ ሰዓቴ በኋላ ያለውን ጊዜዬን ደግሞ
ለስደት ምክንያት በሆነኝ የስልጠና ሙያ ላይ
በመስራት አሰልጥናለሁ…በአጭሩ ከሙያዬ
ሳልርቅ ለመስራት እየሞከርኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ካናዳ ለአሰልጣኞች ምቹ
የምትባል ሀገር ናት…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ብዙ የተመቸ
ነገር አላት…በተለይ ለመማር፣ ለማወቅ፣
በእውቀት ራስህን ይበልጥ ለማሳደግ
ከፈለክ ካናዳ በጣም ምቹ ሀገር ናት…፤…
ከዚህ ውጪም ቴክኖሎጂውን በጣም
በቅርበት ስለምታገኝ ራስን ለማብቃት ጥያቄ
የሚነሳበት ሀገርም አይደለችም፡፡ ካናዳ በዚህ
በኩል የተሻለች ሀገር ብትሆንም እግር ኳስ
በሀገሪቱ ገና በማደግ ላይ በመስፋፋት ላይ
ያለባት ሀገር በመሆንዋ ከአሁን ይልቅ ቀጣይ
አመታት ለሙያው የተሻለች ትሆናለች ብዬ
እገምታለሁ፤ በሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛ
መነቃቃትና መነሳሳት ቢኖርም በህዝቡም
ያለው ተቀባይነት የላቀ ቢሆንም በሚፈለገው
ደረጃ ሰፍቷል ማለት ግን ይቸግረኛል፤ ያም
ቢሆን ጥሩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ካናዳዊያን ለእንደ አንተ
አይነቱ ከአፍሪካ በተለይ ከኢትዮጵያ ለመጣ
አሰልጣኝ ያላቸው እምነትንስ እንዴት
አገኘኸው… ?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በዚህ በኩል
እውነተኛው ምስል ምን መሰለህ…ገና
ከመነሻው ጥቁር አሰልጣኝ ወይም ባለሙያ
ከሆንክ ሙሉ እምነት አይጥሉብህም በአንተ
የማሰልጠን ችሎታ ለማመን አንተን አሰልጣኝ
ብለው ለመቀበል የሆነ ጊዜ ይፈልጋሉ፡፡
ከሀገራችን ወይም ከአፍሪካ የሚሄድ አሰልጣኝ
እምነት እስኪጥሉበት ድረስ በጣም ትዕግስተኛ
መሆን ይጠበቅበታል፤ አንተን ለማመን
አሰልጣኝ ብለው ለመቀበል ደጋግመው
እድሉን ይሰጡሃል…አንተም ረዘም ያለ ጊዜ
በመውሰዱ ሳትበሳጭ ወይም ተስፋ ሳትቆርጥ
እድሉን ከአንድ አንድ መጠቀም አለብህ…
ካናዳ ውስጥ በዚህ በኩል ትዕግስትህን
የሚፈታተን ነገር ቢኖርም ለተስፋ መቁረጥ
እጅ ሳትሰጥ ከተጓዝክና ትዕግስተኛ ሆነህ
በስራህ እነሱን አንዴ ማሳመን ከቻልክ ግን
ከአንተ ውጪ ለእነሱ ሰው አይኖርም፡፡
እምነት እስኪጥሉብህ ግን በጣም ትዕግስተኛና
ጠንካራ ሠራተኛ መሆን ምርጫ ሳይሆን
ግዴታ ነው፤ እንደውም ይሄንን በተመለከተ
አንድ የእኔን ገጠመኝ ላጫውትህ…
ሀትሪክ፡- …ደስ ይለኛል…ቀጥል…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …አንድ ቦታ በሙያዬ
ለመስራት ሄጄ ምን ገጠመኝ መሰለህ…አሁን
ካለሁበት ቶሮንቶ ወጣ ብዬ ለመስራት ጥያቄ
አቀርባለሁ…በሲቪዬ፣በትምህርት ዝግጁነቴና
በስልጠና ልምዴ ደስተኛ ሆነው ለመቀበል
ያስቡና ግን መጀመሪያ እስቲ እንይህ ብለው
እድሉን ይሰጡኛል…በጣም የሚገርምህ
በአካዳሚው ውስጥ ያሉት ሙያተኞች በሙሉ
ነጮች ናቸው…በቦታው ያለሁት ብቸኛው
ጥቁር እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ከላይ እንዳልኩህ
የተሸራረፈ እንጂ ሙሉ እምነት ስለሌላቸው
መጀመሪያ እኔን ስሰራ ማየት የፈለጉት ህፃናት
ላይ ነው…የ12 እና 13 አመታት ህፃናን
እስቲ አሰራ ይሉኛል…በጣም የሚገርምህ
ልጆቹን ሙሉ ትሬይኒንግ (ልምምድ)
እንዳሰራ አልፈቀዱልኝም…የፈቀዱልኝ ነገር
Warming up (ማሟቂያ)እንዳሰራቸው ብቻ
ነው፡፡ እሱን ብቻ አሠርቼ እንድድወጣ ነው
ያደረጉት፡፡ እኔ እሱን አሠርቼ ከወጣሁ በኋላ
ዋናውን ትሬይኒንግ የሚያሠሩት እነሱ ናቸው
፤ይሄ መሆኑ በጣም ቢያበሳጨኝም አቅሜን
እስኪረዱ እስኪያውቁ መታገስ ነበረብኝ፡፡
ባልደስትበትም ታግሼ ያዘዙኝን ስሰራ ቆየሁ፡
፡መጨረሻ ላይ ከመጀመሪያ አመለካከታቸው
ቀስ በቀስ እየተቀየሩ መጡ…በሂደት እምነት
እየጣሉብኝ መምጣት ጀመሩ፡፡ ያጡብኝን
እምነት አገኘሁ…አመኑኝ…ሙሉ በሙሉ
ስልጠናውን እየሰጡኝ የመጡበት ሁኔታ
ነው ያለው…፡፡…ይሄን ያነሳሁልህ ከታገስክ
መጨረሻ ላይ የትዕግስትን ፍሬ እንደምትበላ
ለማሳየት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን…ከመነሻው እምነት
የማጣታቸውን ምክንያት ከምን ጋር ማያያዝ
ይቻላል…ከጥቁርነት…በመነጨ ነው ብሎ
መደምደም ይቻላል…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ከሰው ልጅ
ቀለም ጋር ተያይዞ ነው…የሚል የተሳሳተ
ድምዳሜ የለኝም… ምክንያቱም የሰው ልጅ
በቀለሙ ብቻ የማይዳኝበት…ሁሉም የሰው
ዘር በእኩልነት የሚኖርበት ሀገር መሆኑን
በተግባር ያየሁ ሰው በመሆኔ እኔ ጥሩ
ምስክር ነኝ ብዬ አስባለሁ…
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ውጪ ከሆነ…ታዲያ…
ምንድነው ማለት የሚቻለው…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …እኔ የሚመስለኝ
ከጥቁርነት፣ከዘር ቀለም ይልቅ ሙያው
የሚጠይቀው ትምህርትና ስልጠና አላቸው
ብለው አለማመናቸው…ወይም በተሻለ
አማርኛ ስልጠናው የሚጠይቀው ትምህርትና
ስልጥና ይጎላቸዋል…ከእኛ በተሻለ ለጉዳዩ
ቅርብ አይደሉም ብለው ከማሰብ የመጣ
ይመስለኛል…፤…በተግባርም እንዳየሁት
ከእነሱ የላቀ ሳይሆን በጣም ያነሰ እውቀት
ያለህ አድርገው ማሰባቸው ዋናው ምክንያት
ይመስለኛል፡፡ አመለካከት ላይም በመካከላችን
ትልቅ ልዩነት አለ…፤…ኳስን እኛ በምንረዳበት
መንገድ እነሱ አይረዱትም…መቼም ለምን
በዚህ ደረጃ ተረዱ ወይም አሰቡ ብሎ
መውቀስ ከባድ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ እችላለሁ
በሚል ስሜት ሰርተህ በማሳየት የተዘጋውን
በር ማስከፈት የተዘጋውን አመለካከት ሰብረህ
መውጣት ነው፡፡ ይሄን ካደረክ ከላይም
ብዬሃለሁ አንዴ ከወጣህ ከአንተ ውጪ ሌላ
ሰው ያለ አይመስላቸውም፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተ ከኢትዮጵያ ከመሄድህ
አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳስ እንዳለ
ያውቃሉ? በአጠቃላይስ ኢትዮጵያን እንደ
ሀገር በጥልቀት ያውቋታል?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …አታስዋሸኝና ስለ
ኢትዮጵያ እግር ኳስ አትላንቲክ ውቅያኖስን
የተሻገረ እውቀት አላቸው ወይም በቅርበት
ስለ እግር ኳሱ ያውቃሉ ለማለት ይቸግረኛል፡
ማንኛውም ሀገር ከእግር ኳስ ውጪ
ልትሆን እንደማትችል ጥቅል እውቀት ካልሆነ
በስተቀር ስለሀገራችን እግር ኳስ ጥልቅ የሆነ
ግንዛቤው አላቸው ለማለት ይቸግረኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …ኢትዮጵያን እንደ ሀገርስ…?.
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ይሄን አንተ
ራስህ ብትመልሰው ነበር ደስ የሚለኝ…
(ሣቅ)…ምክንያቱም እኔ ከመምጣቴ በፊትም
በኋላም ሶስት አራት ጊዜ መጥተህ አይተሀል
ታዝበሀል…(አሁንም ሣቅ)…የገጠመህ
ነገርም ይኖራል ብዬ እገምታለሁ…፡፡…
ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በማወቅ በኩል ሁሉም
በትክክል ያውቃታል የሚለው ባያጣላንም…
በጣም ጥቂት የሚባሉት ግን ኢትዮጵያን
የሚያውቋት በሌላ መንገድ ነው…በብዙሃኑ
ብደሰትም እነዚህ ጥቂቶች በተሳሳተ መንገድ
በመረዳታቸው እበሳጫለሁ…
ሀትሪክ፡- …ይሄን…ያህል…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በዚህ ዘመን
ላይ ሆነው…አንዳንድ ያልጠራ አመለካከት
ያላቸው…ከጊዜው ጋር ያልተለወጡ ሰዎች…
ኢትዮጵያ የምትባለውን ታላቅ ሀገር
በተሳሳተ ወይም ባረጀ ባፈጀ ነገር ሲገልጿት
ስታይ ያበሳጭሃል…፤…ኧረ እንደውም
ያምሃል…።…በጣም ጥቂቶች ቢሆኑም
“ኢትዮጵያ” ስትላቸው ዛሬም እዚያ ያረጀ
ያፈጀ ነገር ላይ የቆሙ ያጋጥሙሃል…፤…
ዛሬ ሀገሪቷ ተለውጣ የበርካታ ደማቅ
ታሪኮች ባለቤት ሆና እነሱ ግን የፈረደበት
የ1977ቱ ድርቅ ያመጣው መጥፎ ጠባሳችን
ላይ ቆመው “ኦ…ኢትዮጵያ…?”…ብለው
ፊታቸውን በሀዘን ስሜት አጨማደው
በማንሣት ደምህን ያፈሉታል… (በጣም
ኮስተር ብሎ)…እንዳልኩህ አሮጌ ታሪክ ላይ
ተገትረው መቆማቸው ቢያበሳጭህም…
ደምህን ቢያፈላውም …በትዕግስትና በሰከነ
ስሜት በማስረዳት ከድሮ…ከድንጋይ ዳቦ
ዘመን እንዲወጡ በማስረዳት ብዙዎችን ከዚህ
እንዲወጡ ጥረት አደርጋለሁ…አንዴ ይሄንን
በተመለከተ ምን ገጠመኝ መሰለህ…?
ሀትሪክ፡- …ምን ገጠመህ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ወደ ካናዳ
እንደመጣሁ የቋንቋ ት/ቤት ገብቼ ነበር…፤…
እዛ ት/ቤት የምንማረው ደግሞ እንደ እኔ
ከተለያየ ሀገር የመጡ… የተለያየ ዜግነት
ያላቸው ናቸው፡፡ ከአፍሪካ፣ ከሩሲያ፣
ከቬትናም፣ ከፓክስታንና ከተለያየ ሀገር የመጡ
ናቸው፡፡ ሁሉም ስለመጣበት ሀገር ማንነትና
ታሪክ እንዲናገር በማድረግ የየትውልድ
ሀገሩን የማስተዋወቅ ሠራ ይሰራል፡፡ ሁሉም
የየራሱ ሀገርን ታሪክ በኩራት ይዘረዝራል…
ፓኪስታኑም፣ሩሲያውም ቬትናሙም
አፍሪካዊውም ሁሉም አለኝ ያለውን ዘርዝሮ
ሲጨርስ ተራው እኔ ጋ ይደርሳል፡፡ ኮራ
ቅብርር ብዬ እኔ ከኢትዮጵያ ነው የመጣሁት
አልኳቸ…(ሣቅ)…ይሄንን ስናገር አንዳንዶቹ
ፊት ላይ ብዥታ…አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ
የሀዘኔታ ስሜት በግልፅ ይነበብባቸው
ስለበር…በውስጤ ይሄንን አመለካከት
መሰባበር አለብኝ ብዬ ቃል በመግባት ከሌሎች
በተለየ ሀገሬን ማስተዋወቅን ተያያዝኩት፡፡
በቅኝ ገዥዎች ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት
ሀገር፣ የሁሉም የሰው ዘር እናት የሆነችው
“ሉሲ” የተገኘችባት ሀገር፣ሁሉም አፍሪካዊያን
በቅኝ ስለተገዙ የራሣቸው ቋንቋ የላቸውም…
ግማሾቹ ፖርቺጊዝ፣ግማሾቹ ፈረንሣይኛ
ቀሪዎቹ ደግሞ እንግሊዝኛ ሲናገሩ ኢትዮጵያ
ግን የራስዋ ቋንቋና ፊደል ያላት ብቸኛ ሀገር
ናት…፤…መች ይሄ ብቻ አለምን በሩጫ
የሚያንቀጠቅጡ የታላላቅ አትሌቶች መገኛ
እንዲሁም የእስልምናና የክርስትና ወይም
ሌሎች ሀይማኖቶች በእኩልነት የሚኖሩባት
ምርጥ ሀገር ናት ብዬ ስተነትነው…(ሣቅ)…
ሁሉም ማለት እችላለሁ…“ዋው…በጣም
ይገርማል…”…ምርጥና ታሪካዊ ሀገር
ናት ያላችሁ…”…በማለት ሀዘኔታቸውን
በአድናቆት ቀየሩት…፤…በጣም የሚገርምህ
ተማሪዎቹ ብቻ ሣይሆኑ አስተማሪያችንም
በጣም በግርምትና በአድናቆት ተቀብላኝ ምን
እንዳለች ታውቃለህ…
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- …ምን አለች…በጣም
ያጓጓል…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …እሷም
በግርምት…“…ዋው የዚህ ሁሉ ታሪክ
ባለቤት ሀገር ናት ያላችሁ…?…እኔ ይሄንን
ሁሉ አላውቅም ነበር…፡፡…እኔ በጣም
የሚገርመኝና አንድ የማውቀው ነገር ምን
እንደሆነ ታውቃለህ…? መጽሐፉ ቅዱስ
ሳነብ (ኢትዮጵያ) የምትባለው ሀገር ብዙ ቦታ
መጠቀስዋን ነው” ብላ ሌላ ሀገራችንን የተለየች
የሚያደርጋትን ማጠናከሪያ አታቀርብም…
(ሣቅ)…እኔም ልክ ነሽ “ኢትዮጵያ የሚለው
ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 50 ቦታ
አካባቢ ተጠቅሷል አልኳት…፡፡…እውነት
ነው የምልህ ቁጭት በውስጤ ተፈጥሮ
ስለነበር… በሰዓቱ ሳብራራ የስፖርት ስው
ሣይሆን ፖለቲከኛ አሊያም ቱሪዝም ውስጥ
አገሩን የማስተዋወቅ ስራን የሚሠራ ሰው
ነበር የምመስለው፡፡ ከዚያች ቀን ማብራሪያ
በኋላ ሁሉም አመለካከቱን ቀየረ…ከበሬታም
መስጠት ጀመሩ፡፡ እኔም በጣም ተደሰትኩ…
ደስታዬ የመጣው ግን በከበሬታቸው ሣይሆን
ያንን የ1977ቱን አሮጌ የድርቅ ታሪክ
ከአዕምሮአቸው ውስጥ ጠራርገው እንዲያወጡ
በማድረጌ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተ በእግር ኳሱ ወጣት
በሚል ከሚጠሩ አሰልጣኞች አንዱ ነህ…
ከቀድሙት…ከአንተ በፊት ከነበሩት
አሰልጣኞች ምን ያተረፍከው…ወይም
የተማርከው ነገር አለ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ጥቂት ቢሆንም
የተሻለ ነገር ለመስራት የሞከሩ አሰልጣኞች
እንዳሉ አልክድም በዚህ መልሴ ብዙዎች
ይከፋሉ ግን እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ካለፉት
አሰልጣኞች አገኘሁት ወይም ተማርኩት
የምለው ምንም ነገር የለም ነው መልሴ፡፡
ሀትሪክ፡- …ማለት በፊት ከነበሩት
አሰልጣኞች ለዛሬው የስልጠና ህይወትህ
የሚረዳ ምንም ትምህርት አላገኘሁም…
አተረፍኩ የምለውም ነገር የለም እያልክ
…ነው…እንደዚህ አይነት አስተሳሰብህስ…
የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ አይጥልህም…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በመጀመሪያ
ደረጃ ለአሰልጣኞች ትልቅ ክብር አለኝ…
ምንም በሌለበት የሚችሉትን ሰርተዋል…
ደክመዋል…፤…ይቅርታ አድርግልኝና
መጀመሪያ የሰጠውህን መልስ አልቀይ
ረውም… እደግመዋለሁ…ምንም ያገኘሁት
ትርፍም…ትምህርም የለም…፡፡…እኔ
እንደውም በዚህ አጋጣሚ አንድ እውነት
ልንገርህ…ስልጠናውን በፊትም በጣም
እቃወም ነበር…፤…ይሄንን የምለው ዛሬ
ከሀገር ቤት ከወጣሁ በኋላ አይደለም…፡፡…
እዚያም እያለሁ በድፍረት እናገር ነበር…፡፡
…ሰፈሬ አሮጌ ቄራ የሚባለው አካባቢ ነው…
ልጆች ሆነን ከሠፈር ቦሌ ድረስ በሩጫ እንሄድ
ነበር…ከዚያ መጥተን ደግሞ የፖሊስ ጋራዥ
አለ ሸራተን ፊት ለፊት አንድ ዳገት አለ
እሱን ደግሞ ሮጠን መጥተን እንወጣው ነበር፡
፡ ምንድነው እንደዚህ አይነት ነገር እያልኩ
ያኔም በልጅነቴ እቃወም ነበር፡፡ ምክንያቱም
የምንሠራው ግራ ያጋባኛል ብቻ ሣይሆን
ጥቅሙን የሚነግረኝም ፈልጌ አላገኝም ነበር፡
፡ ካደኩኝ በኋላም ከአዲስ አበባ ሱሉልታ…
ከሱሉልታ ይሄ ዲሽ እስከተተከለበት እስከ
ሳተላይት ጣቢያው ድረስ እንሮጥ ነበር፡፡ በቃ
አፈር ድሜ በልተን ነበር የምንሰራው፡፡ እኔ
በወቱም አሁንም ትልቁ ፀቤ ለምን ጠንከር
ያለ ሥራ ተሠራ አይደለም ጥቅሙ ምንድነው
የሚለው ነበር፡፡ እና ከዚህ የተነሣ አብረውኝ
ላሉት ተጨዋቾች እናገር እቃወም ነበር፡፡ ይሄ
ነገር ምንድነው እውነት ለእግር ኳስ ነው
የምንሰራው እያልኩ እጠይቅም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- …ለእግር ኳሱማ ነው…ይሄ
እንዴት ይጠፋሀል…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …አልገባህም…
(ፈገግ እያለ)…ለእግር ኳስ እንደሆነማ
አልጠፋኝም…ግን ሲሰራ የነበረው ለዛ
ስለማይመስል ነው፡፡ ከእግር ኳሱ ከቴክኒክና
ታክቲክ ይልቅ ለአትሌቲክሱ ጠቃሚ የሆነ
ሥራን እንሠራ ስለነበር ያንን ጥያቄ በውስጤ
ፈጥሮብኛል፡፡ ጠንከር ያለ ትሬይኒንግ
የኢንዱራንስ ስራ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ
ባውቅም መጠኑ ላይ እንዲሁም ኢንዱራንስ
ትሬይኒንግ አሰጣጡ ላይ ጥያቄዎች ነበሩኝ፡፡
ለአትሌቶች በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው
መጠኑ በዝቶ ሲሰጠን የነበረው፡፡ እንደውም
በዚህ አጋጣሚ አባባሌ ምን ያህል ትክክል
እንደሆነ እንድ ማሳያ ላንሳህ…?
ሀትሪክ፡- …ምን አይነት ማሳያ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ኤፍሬም ችቦ
የሚባልን ተጨዋች ታውቃለህ…?…ጥሩ
የአግር ኳስ ጥበብ ያለው ምርጥ የሚባል
ተጨዋች ነበር…፤… እግር ኳስ ሲያቆም
ወደ አትሌቲክስ ወደ ማራቶን ገብቶ ስኬታማ
ሆኗል፡፡ ለምን ስኬታማ ሆነ…?…ብለህ
ስትጠይቅ ኤፍሬም የዚያ ስልጠና ውጤት
ስለሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ሲሰጥ የነበረው
ስልጠና ለአትሌቶች የሚጠቅም ኢንዱራንስ
የበዛበት ትሬይኒንግ ነበር ፡ ፡እንደውም
የኤፍሬምን ወደ ማራቶን ገብቶ ስኬታማ
ሆኖ እየነው እንጂ ሌሎች ተጨዋቾች ወደ
ማራቶን ቢገቡ ኖሮ ብዙ ማራቶንን የሚያሸንፉ
ተጨዋቾች ሊኖሩን እንደሚችሉ ነው ዛሬ
ላይ ሆኜ የምናገረው፤ እንዳልኩህ ብዙዎቹ
በኢንዱራንስ ውስጥ ስላለፉ ሊሳካላቸው
የሚችልበት እድል ሊኖር ይችል ነበር፡፡ ይሄን
ስልጠና ግን ሁሉም ባልልም በጣም ጥቂቶች
ለቴክኒክና ታክቲክ ስራ የተፈጠሩ… እዚያ
ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ አሉ፤
ፍልጠው ቁረጠው… አባረህ በለው አይነት
ስልጠና የሚሰጡ ነበሩ…፤… ከዚህ በመነሣት
ስልጠናውን ስቃወም ነው የኖርኩት፡፡ እኔ
ፀቤ ከስልጠናው እንጂ ከአሰልጣኞቹ ስላልሆነ
ለነበሩት አሠልጣኞች ክብር አለኝ…፤…
የሚያውቁትን ነበር ሲያሰሩን የነበረው…፡፡
ሀትሪክ፡- … የነበረውን ስልጠና
በጣም አጣጥለህ ነው የምታወራው…
፤…ግን አንተ ምን አይነት የስልጠና
ፍልስፍና ነው ያለህ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በጣም
የተለየና የራሴ የምለው የእግር
ኳስ ፍልስፍና የለኝም…፤… ግን
የምከተለው የጨዋታ ፍልስፍና
ፖሴሽን ፉትቦል በጣም እወዳለሁ፡
፡ ጥሩ የእግር ኳስ ፍሰት ያለው
አጨዋወት ምርጫዬ ብቻ
ሣይሆን ግዴታዬም ነው ብዬ
ነው የማምነው፡፡ በዚህ በኩል
በቃ ታውቃለህ የእነ ዮኸን ክራይፍ፣
የእነ ማርሴሎ ቢዬልሳ፣ የእነ ሩኒ
ሚሼል፣ የእነ ቴሌ ሣንታና አይነት
አጨዋወትና የቡድን ግንባታ ቀልቤን
ይሠርቀዋል፡፡ በዚህ የተነሣ የእነዚህ
የፖሴሽን ፉትቦል ባለቤቶች
መፅሐፎችን፣ ቪዲዮዎችን ታሪካቸውን የልጠና
ፍልስፍናቸውን አድኜ ነውየምከታተለውና
የማነበው፡፡ ብዙ ነገራቸውን ከእነሱ ወስጄ
ወደ ራሴ በማምጣት ለእኛ ሀገር ለመጠቀም ነው
የምሞክረው፡፡
ሀትሪክ፡- …የስልጠና ሮል ሞዴሎችህ እነዚህ በስም የጠራ ኋቸው ናቸው ማለት ነው…?…ሮል ሞዴሌ የምትለው ማንን ነው…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ስለ
እነ ዮኸን ክራይፍ፣ ማርሴሎ
ቤይልሳን ከማወቄ በፊት አሰልጣኝ
ስዩም አባተን (ነፍሱን ይማረውና) እያየሁ
እያደነኩ ነው ያደኩት፤ ለእኔ በአሰልጣኝነቱ
የማደንቀው እንደ ጥሩ ሮል ሞዴል
(ተምሣሌት) የማየው ይሄን የተከበረ ታላቅ
አሰልጣኝ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በስዩም
አባተ ሞት ከልብ አዝኛለሁ፤ ህልፈቱ ከልብ
ነው ያስደነገጠኝ…።… ስዩም በጣም የተለየ
አሰልጣኝ በመሆኑ ለእሱ የተለየ ክብር
አለኝ…፤…በዚያ ዘመን እሱ ከኢትዮጵያዊያን
አሰልጣኞች የቀደመ አዕምሮ የነበረው ሰው
ነው፡፡ በዚያን ወቅት ሌሎች አሰልጣኞች
ተራራ ሲያስሮጡ እሱ ከኳስ ጋር ነበር
የሚያሰራው…፤… የኢትዮጵያዊያን
ተጨዋቾችን አቅም ቀድሞ የተረዳ ነበር፡፡
ኳስ የሚጫወት ተመልካችን የሚያረካ ቡድን
በመገንባትም ነበር የሚታወቀው፡፡ መድንን
ካየህ በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ብዙ ርቀት
የሄደ ቡድን ነበር፤ ቡናንም ብትወስድ ኳስ
የሚጫወት ተመልካችን የሚያረካ ቡድን
ገንብቶ ይሄ ሁሉ ደጋፊ እንዲመጣ ምክንያት
የሆነም የማትረሣው አሰልጣኝ ነው፡፡
ተጨዋች በማሳደግም ማንም አይደርስበትም፤
ምንም የማይታወቅን ተጨዋች ከመሬት
አንስቶ ታዋቂ ትልቅ ተጨዋች የሚያደርግ
ልዩ አይን ያለው አሰልጣኝ ነው፡፡ በእነዚህ
መሰረታዊ ምክንያቶች ለእሱ የተለየ
አድናቆትና ክብርም አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከአሁኑም ይሁን ከቀ
ድሞ ተጨዋቾች በጣም የምታደንቀው
ተጨዋችስ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በፊት ከነበሩት
ጥራ ካልከኝ ካሳዬ አራጌን በአንደኛነት ነው
የማነሣው…፤…ካሳዬ አራጌ ልዩ ተጨዋች
ነው፡፡ ከእሱ ሌላ ጥላሁን መንገሻ (ጥልዬ)
የኳስ ጠቢብ የሆነ ተጨዋች ነው…
አብዱራዛቅ (ናይጄሪያ)፣ አብርሃም ብስራትና
አብዲ ሠይድ ለእኔ ልዩዎች ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- …ለካሳዬ አራጌ ያለህን
አድናቆት ገልፀሃልና ስለ እሱ ካነሣህ አይቀር
በዚህ አጋጣሚ እሱ በአሰልጣኝነት ወደ
ኢትዮጵያ ቡና መምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ
እየተነገረ ነው…፤…የእሱን ወደ ኢትዮጵያ
ቡና አሰልጣኝነት መምጣትን እንዴት ነው
የምታየው…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ካሳዬ አራጌን
በተጨዋችነትም በአሰልጣኝነትም ደማቅ
ታሪክ ወዳፃፈበት ወደ ቤቱ መምጣቱን
እንደመልካም ነገር ከሚያዩ ሰዎች አንዱ
ነኝ…፤…ግን ካሳዬ ኢትዮጵያ ቡናን
የሚረከበው እንዴት ነው…? የሚለው
ነው በደንብ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባው፡
፡ ምክንያቱም ካሳዬ ወደ ቡና የሚመጣው
በሆይ ሆይታና በግርግር ዋንጫ
እንዲያመጣ…?…ወይስ የነገውን አስተማማኝ
መሠረት ያለው ቡናን እንዲገነባ…?…
የሚለው በደንብ መታየት አለበት…፡፡…
በእኔ የግል አስተያየት ካሳዬ አራጌ ወደ
ኢትዮጵያ ቡና የሚመጣው እንደባለፈው
አይነት ሱሪ በአንገት ለማለት ከሆነ የመምጣቱ ጥቅም አይታየኝም፤ ምክንያቱም ካሳዬ የተሻለ ነገር እንዲሠራ ከተፈለገ በቂ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም
ካሳዬ ይመጣል የተባለበት ወይም ቡድኑን የሚረከብበት
ወቅት ነገሮች የተበላሹ በሚመስሉበት ጊዜ በመሆኑ የተሻለ እንዲሠራ ከተፈለገ በቂ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል፡፡
የካሳዬ መምጣት ላይ ሣይሆን በቂ ጊዜ ይሰጠዋል…?… አይሰጠውም…?… የሚለው
ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …በሌላ ወገን የተሰለፉት ደግሞ ካሳዬ ከፕርምዬር ሊጉም ከወቅቱ አጨዋወትም ርቋል፤ ከኢትዮጵያ ውጪ በመኖሩ አሁን ያለውን ትውልድና አጨዋወትንም አያውቀውም… ስለዚህ በቡና አሰልጣኝነቱ ሊቸገር ይችላል ብለው የሚሠጉ
አሉ… አንተስ ይሄን ስጋታቸውን ትጋራለህ…
ወይስ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …ምን ሆነህ ነው…?…የኢትዮጵያ
ፕርምዬር ሊግ ይሄንን ያህል ውስብስብና ከባድ…
በቴክኒክና ታክቲክ የታጠረ ሆኖ ነው… ካሳዬ የሚቸገረው…?…የኢትዮጵያ እግር ኳስWalking football (ዘገምተኛ) አይደለም እንዴ? በዚህ በኩል
እኔ ስጋቱ አይታየኝም…፤…ካሳዬም በዚህ ይቸገረራል
ብዬም አላስብም…፡፡…ደግሞም እኮ ፕሪሚየር ሊጉን ለማወቅ የተለየ ጥናት ወይም ሀገር ውስጥ ውሎ ማደርን
አይጠይቅም…፤…ማልያውን ለብሶ የተጫወተበትን ማንም ያልሠራውን ታሪክ በክለቡ የሠራው ካሳዬን ተወውና የሀገሪቱን ቋንቋ፣ ባህልና አጨዋወት የሚያውቁ አሰልጣኞች ከውጭ መጥተው ክለቦችን ያሰለጥኑ የለም እንዴ…?…ምንአልባት እንዳልከው የሚፈጠር ክፍተት ካለ ያንን ለመሙላት ቪዲዮዎችን ማየት
ያግዛል ባይ ነኝ…፤…ከዚያ ውጪም ኮቺንግ ስታፉ የሚዋቀረው እዚሁ ሀገር
ቤት ካሉ አሰልጣኞች በመሆኑ በዚህ በኩል
የሚፈጠርበትን ክፍተት ይሞሉለታል የሚል
እምነት ነው ያለኝ፡፡ በዚህ በኩል ብዙም
አልሠጋም የሚያሰጋኝ ነገር ካለ በቂ ጊዜ
ይሰጠዋል…?…አይሰጠውም…? የሚለው
ነው ለእኔ…፡፡
ሀትሪክ፡- በሀገር ቤት ያሰለጠንከው የመጨረሻ ክለብህ መድን ነው…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡-… አዎን… !
ሀትሪክ፡- መድንን ካሰለጠንክ በኋላ
በሌላ ክለብ ስትጠበቅ አንተ ግን ሀገር ጥለህ
ወጥተሃል፤ እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰህ
ምንድነው….?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …አንድ ሰው
ከሀገር ሲወጣ የራሱ ምክንያት አለው፤ እኔም
ከሀገሬ ስወጣ ሁሉም ሰው እንደሚያሰበው
የተሻለ ነገር ፈልጌ ወይም ተመኝቼ እንጂ
ሀገሬን ጠልቼ አይደለም፡፡ ግን ይሄንን ውሳኔ
እንድወስን የገፋኝ ሌላ ምክንያት የለም
እያልኩህ አይደለም፡፡ ግን አንድ እውነት
ልንገርህ ሀገር ቤት ያለው የስልጠና ሲስተም
ብዙም አይመቸኝም፤ በተለይ ለእንደ እኔ
አይነቱ ወጣ ያለ ባህሪ ላለው አሰልጣኝ ፍፁም
ምቹ አይደለም፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው
ስልጠና ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ አለ ይሄንን
ገንዘብ ለመቀራመት ብዙዎች አሰፍስፈው
ሲጠብቁ በቡድን ተደራጅተው ሲስተም
ዘርግተው ሲንቀሳቀሱ ታያለሁ፤ አንተ የዚያ
ሲስተም አካል ካልሆንክ በስተቀር ያንን አጥር
አልፈህ በሙያህ ለመስራት ነገሮች ሁሉ
ፈተናዎች ናቸው፡፡ ይሄ ነገር እኔም በሙያዬ
ሀገሬ እንዳላገለግል ገፋፍቶኛል፤ የስልጠና
አቅም እውቀትህ ሳይሆን ገንዘብ አፍ አውጥቶ
የሚያወራበት ቦታ በመሆኑ ነገሮችን ለእኔ
ትንሽ ከባድ አድርጎብኛል፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን አንተ ውጪ ነው
ያለኸው የምታጣው ወይም የምትፈራው ነገር
ይኖራል ብዬ ስለማላስብ አሰልጣኞች ገንዘብ
ይቀበላሉ…ብዬ ብጠይቅህ ትመልስልኛለህ?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በጣም ቀላል
ጥያቄ ነው የጠየከኝ…፤…ሀገር ቤትም ብሆን
የምፈራው ነገር የለም። በፊትም አሁንም
እናገራለሁ፡፡ አሰልጣኞች ገንዘብ ይቀበላሉ
ወይ? ነው ያልከኝ ግጥም አድርገው ነዋ
ነው መልሴ፡፡ ሁሉም ብዬ ለክብራቸው
ለሙያቸው የሚጨነቁትን አሰልጣኞች
በደፈናው መውቀስ ባልፈልግም እግር
ኳሱም ሀገርም ገደል ትግባ ኪሴ ግን ይሙላ
የሚሉ በሆዳቸው የሚያስቡ አሰልጣኞች
ያሉባት ሀገር ናት፡፡ አሁንም እነማን ገንዘብ
እንደሚበሉ እነማን እንደማይባሉ በግልፅ
ይታወቃል፡፡ በቅርብ ጊዜ እኮ ገንዘብ የሚበሉ
አሰልጣኞች ተብሎ ስም ዝርዝራቸው በየፌስ
ቡክ ተበትኖ ነበር፡፡ ክለብ አውርደህ ወይም
ላለመውረድ ስትጫወት ቆይተህ ስትባረር
ሌላው ክለብ ደግሞ ከፍተኛ የፊርማ ገንዘብና
ደሞዝ አቅርቦ ሲያስፈርም ታያለህ፡፡ ይህ
ሁኔታ ግጥም አድርገው የሚበሉ አሰልጣኞች
አሉ የማለቴ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተን ከስልጠና ያራቅህ
አንደኛው ምክንያት ይሄ ነው ማለት ነው…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …እንደዚህ አይነት
የተጨማለቀ በገንዘብ ቅብብሎሽ የተዘረጋ
ሲስተም ውስጥ እንዴት ገብተህ ትሠራለህ?
እሰራለሁ ካልክ በልተህ ማብላት ከደላላ ጋር
በተዘረጋው ሲስተም ውስጥ ማለፉ አለብህ፤
ከኮሚቴ ጋር ካልተሞዳሞድክ ማሰልጠንን
አታስበውም። በዚህ ሲስተም ውስጥ ካላለፍክ
ደግሞ በሙያህ ሀገርህን ማገልገል አትችልም፡፡ እኔም የዚህ ችግር ሰለባ የሆንኩት በዚህ
ነው፡፡ በሙያዬ ሀገሬን ማገልገል አልቻልኩም፡፡ በሚሰራው ሥራ ከልቤ ነው የማዝነው፡፡
በዚህ የተጨማለቀ ነገር ውስጥ ከምገባ በቃ
ለምን ሀገሬን ጥዬ አልሄድም…?… ለምንስ
ወጥቼ አልሠራም…?ለምንስ አልማርም…
?እውቀቴን አላሳድግም ብዬ ነው የወጣሁት፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ ሁኔታ የተማረርክበትን
የሀገርህን እግር ኳስ አንድ ቀን ተመልሰህ
የምታገለግል ይመስልሃል…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በጣም እንጂ…
!ከሀገርህ በላይ ደግሞ ምን አለ…?ዛሬ
በዘረጉት ኔትወርክ እግር ኳሱ ላይ አዛዥ
ሆነው የሚገለባበጡ ሁሉ ጊዜ ፍርዱን
ይሰጣቸዋል፡፡ አንድ ቀን የተዘረጋው የዝርፊያ
ኔትወርክ ፍርስርሱ ይወጣል፡፡ በሀቀኝነት
በነፃነት ለሀገራቸው ለማለፉ ለሚደክሙ
ለተገፉ አሰልጣኞች ፀሐይ ትወጣለች፤ የዚያን
ጊዜ እውነት ሲኖር ፍትህ ሲኖር እኔም ወደ
ሀገሬ ተመልሼ አገለግላለሁ፡፡ ወደ ስደት
የሄድኩት ገና ሥልጠናን ጀምሬ ነው እንጂ
አልጨረስኩም፤ ስለዚህ ተመልሼ የምወዳት
ሀገሬን አገለግላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …እስቲ ከውጪ በአሰልጣኝነት
የምታደንቀውንአሰልጣኝ ጥራልኝ ብልህ
ማንን ታስቀድማለህ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …በተናጠል መጥራት
ይቸግረኛል…፤…ከላይ እንደገለፅኩልህ
ጥሩ የኳስ ፍሰት (ፓሴሽን) ያለው ቡድን
በመገንባት የሚታወቁ አሰልጣኞችን አደንቃ
ለሁ…፡፡ …ዮኸን ክራይፍ፣ ማርሴሎ ቢዬልሳ
ከቀድሙት ትልቁን ቦታ ሲይዙ አሁን
ካሉት አርሴን ቬንገር፣ ፔፕ ጋርዲዮላ፣
የርገን ክሎፕም ይመቹኛል። የእነ ማርሴሎ
ቢዬልሳና ዮኸን ክራይፍ መፅሐፎችና
ቪዲዮዎች በብዛት አሉኝ፡፡ አንድም ወደፊት
ላሳካው ከምፈልጋቸውና እንደ ትልቅ እቅድ
ከያዝኩት ውስጥ ሆላንድ ሄጄ የክራይፍ
ኢንስቲቲዩትን መጎብኘት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከውጪ ተጨዋቾችስ…?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …የባርሴሎናዎቹ
ዣቪና… ኢንዬስታ ለእኔ በድንቅ ጥበባቸው
ለነፍሴ እርካታ ሰጪዎች ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከውጪ ክለቦችስ… ?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- ከባርስሎና
ከአያክስ በፊት የማስቀድመው የለም፡፡
ሀትሪክ፡- …ስለ ግል ህይወትህ
ብጠይቅህስ…እንደ ካናዳዊያን አነጋገር
Single ነህ…?… ወይስ Married…?…
(አግብተሃል…?… አላገባህም….?)…
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …(ሳቅ)…
አግብቻለሁ…፤…ባለቤቴ ወደ ካናዳ እስክ
ትመጣልኝና ቀጣይ የትዳር ህይወቴን
ጣፋጭ እስክታደርግልኝ እየጠበኩ ነው…
(ሳቅ)…፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ… ሳልናገር ማለፍ
አልፈልግም የምትለው ካለ?
አሰልጣኝ አባይነህ፡- …የሚቀረኝ
ምስጋና ብቻ ነው፤ በዋናነነት የሀትሪክ
ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን አንተን ኤክስኪዩቲቭ
ኤዲተሩን እዚህ ያለሁበት ካናዳ ድረስ
መጥተህ አፈላልገህ እንግዳ ስላረከኝ ከልብ
አመሰግናለሁ፡፡ በተረፈ ከጎኔ የሁኑትን ሁሉ
ሳላመሰግን አላልፍም፤ ሌላው ባህሪዬን
በተመለከተ አብሮኝ የኖረ ነው፤ ወደፊትም
አብሮኝ ይኖራል፤ ቀጥተኛ ነኝ፡፡ ስታውቀኝ
ብቻ ነው የምታውቀኝ፡፡ ከዚህ ውጪ ሰው
ጋር አልደርስም… በጋፕ ነው የምኖረው፡
፡ ሰዎች ከሩቅ ጉረኛ እንደሆንኩ… ሰው
እንደምንቅ አድርገው ያስባሉ…እኔ ግን ከዚህ
በተቃራኒው መሆኔን ነው የማውቀው፤
ለሰዎች ትልቅ ክብር ያለኝ በሙያዬ የተሻለ
ደረጃ ለመድረስ የማለፋ መሆኔን ነው
መግለፅ የምወደው፡፡