በውድድሩ የሀገር ኩራት መሆንም እንፈልጋለን”
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ
- ማሰታውቂያ -
ወላይታ ድቻ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ሻምፒዮና ከፍተኛ ልምድ ያለውን፤
በውድድሩ ታሪክም ከእዚህ ቀደም
ሀገራችንን በተደጋጋሚ በመወከል በአፍሪካ
ኮንፌዴሬሽን ካፕ የተሳተፈውን መከላከያን
በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገሪቱን
የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሊያነሳ ችሏል፤
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው
የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ከመከላከያ
ጋር ባደረገው የእዚሁ የጥሎ ማለፍ
የፍፃሜ ጨዋታ ተጋጣሚውን ለመርታት
የቻለው መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ
1-1 ካጠናቀቀ በኋላ በተሰጠው አምስት
አምስት የፍፁም ቅጣት ምት በማሸነፍ
ሲሆን ቡድኑ ይህንን ዋንጫ ለማግኘት
የቻለው ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች
ሳይዝና በወጣት ተጨዋቾች በመገንባቱም
በመሆኑ ያገኘው ስኬት ከፍተኛ አድናቆት
ሊያሰጠውም ችሏል፡፡
የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ
መከላከያን በመርታት ይህንን ዋንጫ
ካነሳ በኋላ ወደ ክልሉ ሲገባ በዝዋይ፣
በሻሸመኔ፣ በሐዋሳ እና መቀመጫውን
ባደረገበት የወላይታ ሶዶ ከተማ ከፍተኛ
እና ደማቅ የሆነ አቀባበል ሊደረግለት
ችሏል፤ የቡድኑን ድል ተንተርሶም
በወላይታ ሶዶ ስቴድየም ላይም በርካታ
የክለቡ ደጋፊዎች ተገኝተውም ደስታቸውን
በከፍተኛ የፈንጠዝያ ስሜት ሲገልፁም
ታይተዋል፡፡
ወላይታ ድቻ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ዋንጫን በ1989 ዓ.ም ኒያላን አሸንፎ
ካነሳው ወላይታ ቱሳ እና በ1990 ዎቹ
መጨረሻ ላይም ይህንን ዋንጫ ካነሳው
የሐዋሳ ከተማ ክለብ በኋላም ይህንን ስኬት
የተጎናፀፈ ሌላው የደቡብ ክልል ቡድን
ሲሆን ክለቡ በዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ
የውድድር ተሳትፎው ላይ ወደ ታችኛው
ሊግ ለጥቂት ሳይወርድ ቀርቶ ይህንን
የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሊያገኝ መቻሉ ከፍተኛ
አድናቆት እንዲያሰጠው አድርጎታል፡፡
የወላይታ ድቻ ክለብ የኢትዮጵያ
ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ለማግኘት በመቻሉ
የመጪው ዓመት ላይ ሀገራችንን ወክሎ
በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ
የሚሳተፍ ሲሆን ቡድኑ ከእዚያ ግጥሚያው
ባሸገር ከሊጉ ሻምፒዮና ቅዱስ ጊዮርጊስም
ጋር በአዲሱ የውድድር ዘመን መክፈቻ ላይ
ለአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ተጠባቂውን
ፍልሚያም የሚያደርግ ይሆናል፡፡
የወላይታ ድቻ ክለብ የኢትዮጵያ ጥሎ
ማለፍ ዋንጫን ካነሳ በኋላ ቡድኑ ስላገኘው
ድል፣ በድሉ ስለተፈጠረባቸው የደስታ
ስሜት፣ በመጪው ዓመት ሀገራችንን
ወክለው ስለሚወዳደሩበት የኮንፌዴሬሽን
ካፕ ተሳትፎ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች
ለአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አቅርበንለት
ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቶናል፡፡
ሀትሪክ፡- ወላይታ ድቻ የኢትዮጵያ
ጥሎ ማለፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፤
እንኳን ደስ ያለህ?
አሰልጣኝ መሳይ፡- አመሰግናለሁ፤
የፈጣሪ እርዳታ ነው ለእዚሁ ክብሩ
ያበቃን ስለ ዚህም አምላኬን በጣም ነው
የማመሰግነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ዋንጫን ካነሳችሁ በኋላ ያለው የደስታ
ስሜት ምን ይመስላል?
አሰልጣኝ መሳይ፡– ወላይታ
ድቻ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ዋንጫን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ
በማንሳቱ፣ ከደቡብ ክልል ክለቦች
መካከልም በ1980ዎቹ እና
በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ ይህንን
ዋንጫ ያነሱትን የወላይታ ቱሳ እና
የሐዋሳ ከተማ ክለቦችን ወደ ኋላ
ተመልሰን እንድናስታውሳቸው
እና የእነሱንም ታሪክ እንድንጋራ
ያደረገን በመሆኑ እንደዚሁም
ደግሞ በውጤታማነቱና
በጥንካሬው ይታወቅ የነበረውን
መከላከያን ረተን በአፍሪካ
ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ
ሀገራችንን ወክለን ለምንጫወትበት
የውድድሩ ተሳትፎ በመብቃታችን
በውስጣችን የተፈጠረብን
የደስታ ስሜት ከፍ ያለ ነው፤
ደስታው አሁንም ድረስ ያልበረደ
ነው፤ ይህንን ደስታም ፈጣሪ
የልፋታችሁ ነው በሚል ዋጋም
ስለሰጠንም ለእሱ ልዩ ክብር
እና ምስጋናም ነው ማቅረብ
የምንፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ዋንጫ ባለቤት ለመሆን እቅድን ነድፋችሁ
ነበር?
አሰልጣኝ መሳይ፡- በፍፁም፤
የኢት ዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የሚያወዳድራቸው ውድድሮች ላይ እንደ
አሰልጣኝ ቡድንህን በኃላፊነት ስትመራ
የራስህ የሆነ እቅድ ይኖርሃል፤ ዋንጫ
አነሳለሁ፣ የደረጃ ፉክክር ውስጥ እገባለሁ፣
የመሃል ስፍራው ላይ ሆኜ አጠናቅቃለሁ፣
የሌሎች ውድድሮች ላይ ማለትም በጥሎ
ማለፉ ላይ ስኬታማ እሆናለሁ እና
ወደ ታችኛው ሊግ ሳልወርድ ቡድኑን
በሊጉ ላይ አቆየዋለሁ የሚሉ ነገሮችን
ታስቀምጣለህ፤ እኔ ግን እንደወላይታ ድቻ
ቡድን አሰልጣኝነቴ የጥሎ ማለፉ ውድድር
ከመጀመሩ በፊት ክለባችንን የጥሎ ማለፉን
ዋንጫ ያነሳል ብዬ የጠበቅኩበትም ሆነ
ያቀድኩበት አንዳችም እቅዱም ግምቱም
አልነበረኝም፡፡ የእዚያን ጊዜ ውስጥ የእኛ
ዋነኛ አላማ የነበረው ከሶስት ሳምንት በፊት
ወላይታ ድቻ የወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኝ
ስለነበር ክለቡን ውጤታማ በማድረግ
ወደታችኛው ሊግ እንዳይወርድ የማዳን
ስራ ነበር ስንሰራ የነበረው፤ ከእዚያ በኋላ
ግን በሊጉ መትረፋችንን ካረጋገጥን በኋላ
ይህንን ዋንጫ ስለማግኘት ከኤሌክትሪክ
ጨዋታ ጀምሮ ማሰብ ጀመርን፤ እነሱንም
በፍፁም ቅጣት ምት አሸነፍን የአሸናፊነት
ፍላጎታችን ከፍ እያለ ሲመጣ ደግሞ
ይህንን ዋንጫ ማግኘት አለብን ብለን
ማሰብ ጀመርንና ጅማ አባቡናን በግማሽ
ፍፃሜው መከላከያን ደግሞ በፍፃሜው
ረተን የውድድሩ አሸናፊ ልንሆን ችለናል፡፡
ሀትሪክ፡- በፍፃሜው ቀን ከመከላከያ
ጋር የነበራችሁ ጨዋታ ምን መልክ
ነበረው..? ለአሸናፊነት እንድትበቁስ
ያደረጋችሁ ዋናው ምክንያትስ ምን ነበር?
አሰልጣኝ መሳይ፡- ወላይታ ድቻ
እና መከላከያዎች ያደረጉት የሐሙስ ዕለቱ
የፍፃሜ ጨዋታ በሁለቱም ክለቦች መካከል
ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር ተደርጎበታል፤
በጨዋታውም ቡድናችን ከተጋጣሚ
አንፃርም በስነ-ልቦናው በኩልም ጥሩ ሆኖ
ታይቷል፤ በዕለቱ የመረጥነው አጨዋወት
ለእኛም ጠቅሞናል በእዚያ እንቅስቃሴ
ውስጥ ሆነንም ነው ግጥሚያውን በአቻ
ውጤት ካጠናቀቅን በኋላ በመለያ ምትም
ለማሸነፍ የቻልነው፤ ይህንን የስኬት ድል
ካገኘን በኋላም እኔን ትዝ ያለኝ የታዋቂው
አሰልጣኝ ዲዲየ ዴሻምፕም ንግግርም ነው
እሱ በአንድ ወቅት እግር ኳስ ሳይንስም ነው
እድልም ነው ብሎ የተናገረበት አጋጣሚም
አለና የእኛን ድል በጣም አቅደንበት ሳይሆን
በፈጣሪ ፈቃድ ያገኘነው መሆኑን በእዚሁ
አጋጣሚ ለመናገር እፈልጋለውኝ፡፡
የወላይታ ድቻ ቡድን የዕለቱን ግጥሚያ
በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ እንዲችል
የሜዳው ጭቃማነትም ከእኛ ይልቅ ለእነሱ
አጨዋወት የፈቀደላቸው እና የጎላ ነገር
አለመኖሩ ከእዚያ ውጪም የእኛ ክለብም
የተጋጣሚውን ቡድን ኳስ ይዞ የመንቀሳቀስ
አጨዋወት ያውቅ ስለነበርና በመከላከሉም
ላይ ጥብቅ እና ታይት ሆኖ በመቅረቡ፣
በአጨዋወታችን ላይም የአጥቂ ስፍራ
ተጨዋቻችንን አላህዛርን በእንቅስቃሴ ወደ
መሀል በማምጣት እና ከሪምንም ወደፊት
ሄዶ እንዲጫወትና የመሀል ክፍሉ ላይም
የሰው ቁጥርን በማብዛት በመልሶ ማጥቃት
አጨዋወት ለመጫወት በመሞከራችንም
ጨዋታውን በአቻ ውጤት እንድናጠናቅቅና
በመለያ ምትም እንድናሸንፍ አድርጎናል፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ዋንጫን ወላይታ ድቻ ለማንሳት በመቻሉ
ለአንተ እና ለቡድንህ ተጨዋቾች
የፈጠረላችሁ የተለየ ነገር አለ?
አሰልጣኝ መሳይ፡- አዎን፤ በጣም
እንጂ እንደ አሰልጣኝነቴ ይህ ውጤት
ለእኔ ወደ ሙያው ከገባሁበት ጊዜ
አንስቶ ትልቁ እና ከምንም ነገር በላይም
የማስበልጠው እና አቻም የማላገኝለት
ነው፤ የአሰልጣኝነት ሙያው ላይ ስትቆይ
ታሪክ ሳይኖርህ ገንዘብ ብቻ ማግኘት በቂ
አይደለም፤ ያን ስል ገንዘብ አያስፈልግም
ማለቴ አይደለም፤ ሙያው ላይ ስትሰራ
ለአንተ ዋናው እና ትልቁ ቁም ነገር
የምታስመዘግበው ታሪክ ነው፤ ታሪኩም
ሁሌ የሚነገርልህና የሚወራልህም
ስለሆነ ለአንተ ያ በአስደሳችነቱም ወደር
የማታገኝለትም ነው የሚሆንልህ፤
ወደፊት ስትጓዝ ከቤተሰብ፣ ከልጆችህ፣
ከሚዲያው እና ከሌሎች ሙያተኞችም
ጭምር ምን ሰርተህ አልፈሃል ተብለህ
ስትጠየቅ ውጤቱን በመጥቀስ እንዲህ
ሰርቼያለሁ እንድትል ስለሚያደርግህ
እንደዚሁም ደግሞ ወላይታ ድቻን ወደ
ውጪ ሀገር ይዤም ለጨዋታ ስለምሄድም
ያ በኢንተርናሽናል ደረጃ ያለኝን የስልጠና
ልምዴንም ይበልጥ ስለሚያሳድግልኝ፤
ከሊጉ ቀጥሎ ይህ ዋንጫም ትልቅ የሚባል
በመሆኑም ለእኔ የተለየ ነገርን ፈጥሮልኛል፡
፡ ለቡድኔ ተጨዋቾችም ምን አልባት ከግብ
ጠባቂያችን ወንደወሰን ገረመው በስተቀር
ለአብዛኛዎቹ በተጨዋችነት ዘመናቸው
ያገኙት አበረታች እና ትልቅ የሚባል
ውጤትም ያገኙበት ስለሆነ ለእነሱም ለሌላ
ስኬት የሚያበረታታቸው ያህል ሆኖ ነው
ያገኘሁት፡፡
ሀትሪክ፡- ወላይታ ድቻ በአዲሱ ዓመት
ሀገራችንን በመወከል በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን
ካፕ ውድድር ላይ ይካፈላል፤ ለእዚህ
ተሳትፎው በምን መልኩ ይቀርባል..
ክለባችሁ ምን ውጤትስ ለማምጣት
ከወዲሁ ይዘጋጃል?
አሰልጣኝ መሳይ፡- የወላይታ
ድቻ እግር ኳስ ክለብ ሀገራችንን ወክሎ
ለሚሳተፍበት የኢንተርናሽናል ከፍ
ያለው ውድድሩ ከወዲሁ ነው እቅዱን
ነድፎ ጠንካራውን ስራ ሊሰራ የሚገባው፤
ለእዚያም ውድድር የአሁን ሰዓት ላይ
ቡድናችን ብዙ ነገርንም እያሰበ ይገኛል፤
የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎ ውድድራችንም
ቀላል ስለማይሆንልን በምናስቀራቸው
ወጣት ተጨዋቾች ላይ ጥሩ ዲሲፕሊን
ያላቸውንና ልምድ ያላቸውን ጠቃሚ
ተጨዋቾችንም ከተለያዩ ክለቦች ጥሩ
ገንዘብ በማውጣት ልናስመጣም አስበናል፤
በውድድሩ ተሳትፎአችንም ጠንካራ ቡድን
ሰርተን እንደምንመጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ስለምታመጡት ውጤትስ
ምላሽ አልሰጠህንም?
አሰልጣኝ መሳይ፡- የአፍሪካ ኮንፌ
ዴሬሽን ካፕ የሚኖረን ተሳትፎ ላይ እኛ
ወደ ውድድሩ የገባነው በመጀመሪያው
ዙር ለመባረር አይደለም፤ ጥሩ ጉዞ
እንዲኖረንም እንፈልጋለን፤ በመጀመሪያ
ለእዚህ የሚረዳን ፈጣሪ ከእኛ ጋር አብሮን
አለ በመቀጠል ደግሞ የምናደርጋቸው
ጨዋታዋች ላይ ውጤታማ የሚያደርገን
የራሳችን የሆነ የኳስ አጠቃቀም ይኖረናልና
ያ ለውጤት ያበቃናል፤ የወላይታ ድቻ
ቡድን የመከላከል ጨዋታው ላይ በንፅፅር
ብዙ ጎል የማይቆጠርበት ቡድን ነው፤
መከላከሉ ላይ በጣም ጠንካራም ቡድን
ነው ያ እንዳለ ሆኖ አጥቅቶም ለመጫወት
የሚያስብ ቡድንም ስለሆነ በተለይ በሜዳው
የሚያደርገው ጨዋታ ላይ የሜዳውን እድል
በመጠቀምና ተጋጣሚውንም በመርታት
ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፍ ቡድንን ነው
የምናዘጋጀው፡፡ በውድድሩ ለኮንፌዴሬሽን
ካፕ ማለፍ ብቻ ሳይሆን በውድድሩ የሀገር
ኩራት መሆንም እንፈልጋለን፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ዋንጫን ተጨዋች ሆነህ አላነሳህም፤ አሁን
ግን በአሰልጣኝነት ህይወትህ ዋንጫውን
አነሳህ ስሜቱ ምን ይመስላል?
አሰልጣኝ መሳይ፡- አዎን፤
የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች እያለሁ ይህን
ስኬት በመከላከያ ክለብ ተሸንፈን ለጥቂት
አጥቼዋለሁ፤ ያኔም ቅርም ተሰኝቻለው፤
አሁን ግን ከበርካታ ዓመታት በኋላ
በአሰልጣኝነት ህይወቴ ይህንን ዋንጫ
ከወላይታ ድቻ ጋር የፈጣሪ እርዳታ
ታክሎበት ስላገኘሁት ልዩ ስሜት ነው
በውስጤ እየተፈጠረብኝ ያለው፡፡
ሀትሪክ፡- በአዲሱ ዓመት ከቅዱስ
ጊዮርጊስ ጋርም ለአሸናፊዎች አሸናፊ
ዋንጫ ትጫወታላችሁ?
አሰልጣኝ መሳይ፡- አዎን፤ ከቅ
ዱስ ጊዮርጊስ ጋር የአዲሱ አመት ላይ
የሚኖረን የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ
ጨዋታ ለሁለታችንም ግጥሚያው
እጅግ አስፈላጊያችን ነው፤ የቡድናችንን
የአዲሱ ዓመት አቋም ምን እንደሚመስል
የምንለካበትም ነው፤ ጨዋታው ጥሩ
ፉክክር ይደረግበታል ብዬም ነው ተስፋ
የማደርገው፤ አሁን ትልቅ የሚባል
ዋንጫን እኛ ስላገኘን የቀጣዩ ዓመት ላይም
ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ሌላ ትልቅ
ዋንጫን ማንሳት እንፈልጋለንና ለእዚያም
የተጠናከረ ዝግጅትን እንሰራለን፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ
ዋንጫን አግኝታችሁ ወደ ክልላችሁ ስትገቡ
የነበረው አቀባበል ምን ይመስል ነበር?
አሰልጣኝ መሳይ፡- የወላይታ ድቻ
ክለብ በታሪክ ትልቅ የሚባለውን ዋንጫ
ይዞ ወደ ክልሉ ሲገባ የተደረገለት አቀባበል
ጥሩ የሚባልና ደማቅም ነበር፤ ከዝዋይ
ከሻሸመኔና ሐዋሳ ድረስ በመምጣትም
ነው ሊቀበሉን የቻሉት፤ በሶዶ ስቴድየምም
በደጋፊዎቻችን ጥሩ አቀባበልም
ተደርጎልናል፡፡ አቀባበሉ ወደፕሪምየር ሊጉ
ስንገባ ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ስለነበር
ያ በጣሙን ሊያስደስተንም ችሏል፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…
አሰልጣኝ መሳይ፡- የወላይታ
ድቻን ላለፉት ስምንት ዓመታት ሳሰለጥንና
ክለቡንም በኃላፊነት ስመራ እስካሁን
ላመጣነው ውጤትም ሆነ የአሁን ሰዓት
ላይም ላገኘነው ከፍተኛ ድል እንድንበቃ
የመጀመሪያው ትልቁን ድርሻ የሚወስደው
አካል ቢኖር ፈጣሪ ነው፤ በመቀጠል
የክለቡ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አልታዬ
አየለ ለእኔ ትልቅ ኃላፊነትን እና ሰፋ ያለ
ጊዜን በመስጠት ከቡድኑ ጋር እንድቆይና
እንድሰራ ስላደረጉኝ ለቡድኑ ውጤት
ማምጣት አስተዋፅኦን አድርገዋል፤ ሌላው
ሳይሰለቹ እና ሳይደክሙ እኛን በየክልሉ
በመጓዝ ያበረታቱን የነበሩት ደጋፊዎቻችን
እና ለምንም ነገር ታዛዥ በመሆን ስራቸውን
በትጋት ይሰሩ የነበሩት ተጨዋቾቻችንም
ሌላው ለውጤት መምጣቱ ተጠቃሽ ስለነበሩ
ለሁሉም አካላቶች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡