በ2019 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሴራሊዮን አቻውን በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በጋና አቻው ከደረሰበት የ5-0 አስደንጋጭ ሽንፈት ያገገመበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኳስ ቁጥጥር እና በሙከራ ረገድ ከተጋጣሚው ከሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን እጅግ ተሽሎ የቀረበ መሆን ችሎ ነበር። ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ዋልያዎች የመጀመሪያውን ሙከራ ለማድረግ የፈጀባቸው የ 3ደቂቃዎች እድሜ ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ ዑመድ ኡኩሪ በሳጥኑ ቀኝ በኩል ወደ ግብ የመታው ኳስ የውጪኛውን መረብ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከ3 ደቂቃዎች በኋላ በ6ኛው ደቂቃ ዑመድ ኡኩሪ በቀኝ መስመር በኩል በድጋሚ ጥሩ ግብ የማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ወደኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል።
36ኛው ደቂቃ ላይ የዋሊያዎቹ ተከላካይ አህመድ ረሺድ በረጅም የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ብቃት ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ይዞት ሲገባ የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ሜዶ ካማራ ጥፋት በመስራቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት የብሔራዊ ቡድኑ አምበሉ ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር ዋልያዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የመጀመርያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ዋልያዎቹ ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ይህ ነው የማይባል ፈታኝ እና አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የበላይነት የታየበት ሲሆን የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድንም የአቻነት ግብ ለማግኘት አልፎ አልፎ ጥረት ሲያሳዩ ተስተውለዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከርቀት የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ዑመድ ዑኩሪን ቀይሮ የገባው አቤል ያለው ፍጥነቱን በመጠቀም ከመስመር እየተነሳ ወደ ውስጥ በመግባት አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ ነበር። 78ኛው ደቂቃ የሴራሊዮን ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ጋቶች ፓኖም ያገኘውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ከግብ ጠባቂው ጋር 1-1 ተገናኝቶ በቀጥታ ወደ ጎል የሞከረው ኳስ የግራ ቋሚውን ለትሞ የተመለሰበት ኳስ በዋልያዎቹ በኩል እጅግ የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች።
- ማሰታውቂያ -
እንግዶቹ ሴራሊዮኖች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የአቻነት ጎል ለማግኘት መጠነኛ ጫና ከመፍጠራቸው ውጪ እምብዛም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈተና የሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። ከዚህ በኋላም ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት ጨዋታው በዋልያዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከዚህ ጨዋታ አንድ ቀን በፊት በምድቡ የሚገኙት ኬንያና ጋና ባደረጉት ጨዋታ ኬንያ ሳትታሰብ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች። ውጤቱንም ተከትሎ በምድቡ የሚገኙት አራቱም ቡድኖች እኩል ሶስት ነጥቦች በመያዝ የምድቡን ቀጣይ ጨዋታዎች ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል።
የምድቡ ቀጣይ ጨዋታዎች መስከረም 30/2011 እና ጥቅምት 4/2011 የሚደረጉ ሲሆን ዋልያዎቹ መስከረም 30 ባህርዳር ስታዲየም ላይ እንዲሁም ከ4 ቀናት በኋላ ጥቅምት 4 ወደ ናይሮቢ በማቅናት ከኬንያ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል።