በሀገር ዉስጥ ተጫዋቾች ብቻ በሚከናወነዉ በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮና (ቻን) ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሱዳን አቻው ጋር ነገ ምሽት 2 ሰአት የመልስ ጨዋታውን ያካሂዳል።
ባለፈው ሳምንት እሁድ ሀዋሳ ላይ ሱዳንን ገጥመው 1 ለ 1 የተለያዩት ዋልያዎቹ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ልምምዳቸውን አድርገዋል።
ከፓስፖርት ችግር ጋር በተያያዘ ከ18 ተጫዋቾች ውጪ የነበረው ፍሬው ሰለሞን ፓስፖርቱ ታድሶለት ከቡድኑ ጋር ተጉዟል 19 ተጨዋቾን ጨምሮ በአጠቃላይ 27 የልዑካን ቡድንን የያዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ሱዳን ገብቷል።
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ካርቱም ሲደርሱ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ “ሱዳን የመጣነው ለማሸነፍ” ነው ብለዋል።
ዋልያዎቹ ወደ ኬንያው ውድድር ለማለፍ የነገውን የመልስ ጨዋታ ማሸነፍ አልያም ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥሮ አቻ መለያየት ይጠበቅባቸዋል።
በሃዋሳ ከተማ በተደረገው ጨዋታ የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ሰይፈዲን መኪ በ77ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ጨዋታውን 1 ለ 0 መምራት ችሎ ነበር።
አብዱራህማን ሙባረክ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ለዋልያዎቹ የአቻነቷን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናነቀቁ ይታወሳል።