በአፍሪካ የክለቦች የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የሆነው ወላይታ ዲቻ ነገ(ረቡዕ) በ10 ሰአት ላለበት የመልስ ጨዋታው ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።
የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ስንብት ተከትሎ በፕሪሚየር ሊጉ የተሻለ ውጤትን በማስመዝገብ ላይ የሚገኙት የክለቡ አዲሱ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ክለቡን እየመሩ በአፍሪካ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ባለፈው ሳምንት በዛንዚባር አድርጎ ከሜዳው ውጭ 1 ለ 1 በመለያየት ወደ ሀገሩ መምጣቱ ይታወሳል። የመልስ ጨዋታውንም ለማድረግ ያለፉትን 7 ቀናት በሀዋሳ ልምምዱን ሲሰራ ቆይቶ ዛሬ ማለዳ የመጨረሻ ቀለል ያለውን ልምምዱን ሰርቷል።
አሰልጣኝ ዘነበ ከሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ ቆይታ “በልዩ ትኩረት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ገልፀው በሜዳችን ነው ብለን አንዘናጋም በደጋፊያችን ፊት የተሻለ ግብ አስቆጥረን አሸንፈን የተሻለ ውጤት ይዘን ለመውጣት እንጥራለን ሜዳችን ቢሆንም አንዘናጋም” በማለት ተናግረዋል።
18 ተጫዋቾችን የያዘው ክለቡ ዚማሞቶን ከገጠሙበት ጨዋታ ምንም የተለየ ጉዳት በቡድኑ ውስጥ የሌለ ሲሆን ማረፊያቸውን ፓራዳይዝ ሆቴል በማድረግ የነገውን ጨዋታ እየጠበቁ እንደሆነ ተጫዋቾቹ ለድረገፃችን ገልፀዋል። አራቱም ዳኞች ከጎረቤት ጅቡቲ ሲሆኑ ኮሚሽነሩ ከሲሼልስ እንደሆኑ እና እስከ አሁን ግን ወደ ኢትዮጵያ እንዳልደረሱ ተገልፇል።
- ማሰታውቂያ -
ጨዋታው ነገ(ረቡዕ) ልክ 10:00 ሲል በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።