የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን
ለማንሳት ዕድሉ ካላቸው ክለቦች መካከል
አንዱ የሆነው ሲዳማ ቡና በክለቡ ውስጥ
ጥሩ ብቃታቸውን እያሳዩ ካሉትና ዘንድሮም
ውላቸውን ከሚጨርሱት ተጨዋቾች
መሀከል ለሚጠቀሱት ለወሰኑ ማዜ /ቀስቴ/፣
ለሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/፣ ለአንተነህ
ተስፋዬ /አንቱ/ እና ለለዓለም ብርሀኑ በክለቡ
ውስጥ በቀጣይ ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉበትን አዲስ
የኮንትራት ስምምነት ውል እንዳቀረበላቸው
ከክለቡ አካባቢ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ በእዚህ
ዓመት የሊጉ ሻምፒዮና ላይ በአሁን ሰዓት
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ በሚቀረው በቅዱስ
ጊዮርጊስ በ3 ነጥብ ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ
ላይ የተቀመጠ ቢሆንም የክለቡ ስኬታማነት
የብዙዎችን ቀልብ የሳበ እና የቡድኑንም
ሃላፊዎች እያስደሰተ ያለ በመሆኑ በመጪው
ዓመትም የበለጠ ጥንካሬውን እንዲያስቀጥልና
ለታላቅ ውጤትም እንዲበቃ ከወዲሁ በማሰብ
ለተጨዋቾቹ የፊርማ ማራዘሙን የውል
ጥያቄ ማቅረቡም ተገልጿል፡፡
የሲዳማ ቡና ክለብ የእዚህ አመት ላይ
እያሳየ ባለው ጥንካሬው የሊጉን ዋንጫ
ለማንሳት አሁንም የራሱን እድል በመወሰንና
የመሪውን ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ
መጣል በመጠበቅ ዕድሉ ያለው ሲሆን ይህንን
ለማሳካትም ተጨዋቾቹ በቀጣዩ ጊዜ ቀሪ
ፍልሚያዎቻቸው ላይ የተቻላቸውን ሁሉ
ጥረት እንደሚያደርጉም ተገልጿል፡፡
የሲዳማ ቡና ክለብ የእዚህ አመት
ተሳትፎው ላይ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት
ከቻለ የቡድኑ ተጨዋቾች ክፍተኛ ሽልማት
ሊሰጣቸው እንደሆነም እየተገለፀ ሲሆን
ቡድኑ የአሁን ሰአት ላይ በየጨዋታዎቹም
ውጤታማ ሲሆን ለእያንዳንዱ ተጨዋች የ4
ሺህ ብር የማበረታቻ ኢንሴንቲቭ ሽልማትም
እየሰጣቸውም እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የሲዳማ ቡና ክለብን የእዚህ አመት
የውጤት ጉዞና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ
ጉዳዮች ላይ እንደዚሁም ደግሞ በእስካሁኑ
የራሱ ብቃት ላይም ካናገርናቸው ተጨዋቾች
መካከል ዘንድሮ ለክለቡ ውጤት ማማር ጥሩ
አስተዋፅኦ ካደረገው ወሰኑ ማዜ ጋር አጠር
ያለ ቆይታን አድርገን ምላሹን ሊሰጠን ችሏል፡
፡
የሲዳማ ቡናው የግራ መስመር የኮሪደር
ስፍራ ተጨዋች የእዚህ ዓመት ላይ ክለቡ
እያስቆጠራቸው ካሉት ግቦች መካከል
ለአጥቂዎቹ ኳሶችን አሲስት በማድረግና
ራሱም 3 ያህል ግቦችን በማስቆጠር ለቡድኑ
ጥቅምን እየሰጠ እንደሆነም ልንመለከት
ችለናል፡፡
የሲዳማ ቡናውን ወሰኑን የእዚህ አመት
ላይ ክለባቸው በሊጉ እያደረገ ስላለው ተሳትፎ
ጥያቄ አቅርበንለት ሲመልስ
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ አመት
ተሳትፎችንን ምንም እንኳን በመሃል አስቆጪ
የሚባሉ ነጥቦችን ጥለን ብንጓዝም በውጤት
ደረጃ ግን እየሄድን ያለነው እኛ ባስብንበት
ሁኔታ ነው፤ በሊጉ አሁንም ከፊታችን ገና
አራት ቀሪ ጨዋታዎች አሉን፤ እነሱን
ጨዋታዎች ለማሸነፍም ተነጋግርንበታል፤
በመጨረሻም የምናልመውንም ውጤት
የምናገኝበትም ይሆናል”፡፡
የሲዳማ ቡና የእዚህ ዓመት ህልሙ
ዋንጫውን ለማንሳት ነው የሚልም ጥያቄ
የቀረበለት ወሰኑ ማዜ ሲመልስ
“ምንም ሆነ ምን አዎን፤ የሊጉን
ተሳትፎን እያደረግን ያለነው ለተሳትፎ ሳይሆን
የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ነው፤ ለእዚያም
ነው ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከእኛም
የቅርብ ርቀት ላይ ካሉት ቡድኖችም ጋር
አንገት ለአንገት ተያይዘንም እየተጫወትን
የምንገኘው”፡፡
የሲዳማ ቡና ክለብ እንደስኬታማነቱ
ውጤት ያጣባቸውም ግጥሚያዎች አሉ፤
የእነዚያን ችግሮች ልትገልፅልን ትችላለህ
“የሲዳማ ቡና ክለብ የሊጉ ተሳትፎው ላይ
አሁን ካስመዘገበው ውጤት በተሻለም ብዙ
መጓዝ ይችል ነበር፤ በራሳችን በምንፈጥራቸው
ጥቃቅን ስህተቶችና ችግሮችም ነው ጎሎች
በቀላሉ እየተቆጠረብን ነጥብን ስንጥል
የነበረውና እነዚያ ሊጎዱን ችለዋል፤ አሁን
ግን ችግሮቹን እየቀረፍንና እያረምንም ስለሆነ
በቀሪ 4ቱ ጨዋታዎች ላይ ጠንካራ ቡድንን
ይዘን በመቅረብና ጨዋታዎቹንም በማሸነፍ
ዋንጫውን ልናነሳ የምንችልበትን ዕድል
እንፈጥራለን”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ አመት
ፉክክርን እንዴት አገኘኸው፤ ለአንተስ ክስተቱ
ቡድን ማን ነው
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ
ፉክክር አራት እና አምስት ክለቦች ለዋንጫ
የሚፎካከሩበትና ወራጅ ቡድኖችንም ገና
ያለየበትም ስለሆነ ሊጉ በጥሩነቱ የሚጠቀስ
ነው፤ ለሊጉ ጥሩ ፉክክርም ውድድሩ
አለመቋረጡ አስተዋፅኦን አበርክቶለታልና
ያ የሚያስደስት ነው፤ የውድድሩ ላይ ለእኔ
ክስተት ብዬ የምጠቅሰው ቡድን ፋሲልከተማን ነው”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለሲዳማ
ቡና እያሳየህ ስላለው ወቅታዊ ብቃት ምን
ትላለህ… አዲስ አበባ ላይ በሚኖሩት
ጨዋታዎች ላይ ደግሞ አንዳንዴ ስትሰለፍ
አይታይም….
“የሲዳማ ቡና ክለብ ውስጥ ዘንድሮ
ያለኝ አቋም ጥሩ የሚባልና የሚያበረታታም
ነው፤ ለክለባችንም ውጤት ማማር
ኳሶችን ለጓደኞቼ ከማቀበል አንስቶም
ጎል በማስቆጠርም የሚቻለኝን ሁሉ
እያደረግኩም ነው፤ የአዲስ አበባ ላይ
በሚኖሩት የአንድአንድ ጨዋታዎችም
ላይ እኔ ለመሰለፍ ያልቻልኩት ምንአልባት
አሰልጣኙ ሊጠቀመው ከሚፈ ልገው
ታክቲክ አኳያም ሊሆን ይችላልና ያንን
እንደተጨዋችነቴ ልቀበለውም ችያለሁ”፡፡
የሲዳማ ቡና ክለብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን
የሌሎችም ቡድኖች ጋር ሄደህ ስትጫወት
በአጨዋወቱ በጣም የተመቸህ ተጨዋች
ማን ነው
‘‘በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ
ከብዙ ተጨዋቾች ጋር አብሬ በመጫወት
በእንቅስቃሴ ጥሩ መግባባትን ላሳይ
ብችልም የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ
ለእኔ አጨዋወት ይበልጥ በጣም የሚመች
ተጨዋች ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ ተጨዋቹ
ኳስ እንድታቀብለው የሚያስገድድህ አይነት
ተጨዋች ነው፤ ኳስ እንዳቀበልከው ድሪብል
አድርጎና ሰው ቀንሶም ስለሚጫወት ልዩ
ብቃት አለው፤ ያ አይነት አጨዋወት ለእኔ
በጣም ይመቸኛል”፡፡