ትላንት ምሽት በሜዳቸው ኪርኮፕ ዩናይትድን ያስተናገዱት ቢርኪርካራዎች ሎዛ ኣበራ እና ስቴፍ ፋሩግያ እያንዳንዳቸው ባስቆጠርዋቸው ሁለት ግቦች ታግዘው አሸንፈዋል።በመጀመርያው አጋማሽ ያለ ግብ የተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ አራት ግቦችን ሲያስተናግድ የግብ አዳኝዋ ሎዛ ኣበራ በ54ኛው እንዲሁም በ86ኛው ደቂቃ ሁለት ግቦችን አስቆጥራለች።
ውጤቱን ተከትሎ ቢርኪርካራዎች በ2019 ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን ሲያስቀጥሉ ኢትዮጵያዊታ ሎዛ አበራም በሊጉ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ 19 ከፍ በማድረግ የቢኦቪ የሴቶች ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ሠንጠረዥን እየመራች ትገኛለች።ከቀናት በፊት የሱፐር ካፕ ዋንጫን ያነሱት ቢርኪርካራዎች ቢኦቪ ተብሎ የሚጠራውን የማልታ የሴቶች ፕሪምየር ሊግን ሰፊ ሊባል በሚችል የነጥብ ልዩነት እየመሩ ይገኛሉ።