THE BIG INTERVIEW WITH SHEWAREGA DESTA
“ፕሮጀክት ያቋቋምኩት የሀብታም ልጅ እያሰለጠንኩ ገንዘብ ለመሰብሰብ
ሳይሆን ጎዳና ላይ ቤንዚን የሚስቡ ታዳጊዎችን ለመታደግ ነው”
- ማሰታውቂያ -
በይስሀቅ በላይ
እግር ኳስ ተጨዋቾች መጽሐፍ ይፅፋሉ ቢባሉ ያምናሉ? አሁን ግን ሆኗል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨዋች የነበረው 3-
5-2 የጨዋታ ሲስተም ፈጣሪ ወይም ተግባሪ በሚል በብዙዎች የሚወደሰው ሸዋረጋ ደስታ በእግር ኳስ ተጨዋቾች ላይ ሲሰነዘር
የነበረውን አመለካከት የሰበረ አዲስ ገድል ፈፅሟል፡፡ ቀደም ሲል “እግር ኳስ፣ እርዳታና ዲያስፖራ” የሚል ርዕስ የተሰጠውን
የበኩር መጽሐፉን ለአንባቢያ እነሆ በረከት ያለው ሸዋረጋ ደስታ አሁን ደግሞ በብዙዎች ያልተደፈረውንና ያልተነካካውን የክለቦች
ህብረትና “የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውዝግብ እውነታዎች” የሚል ርዕስ የተሰጠውን ሁለተኛውን መጽሐፉን በድፍረት ጽፎ
በማስመረቅ የድርሰቱን አለም በይፋ መቀላቀሉን አውጇል፡፡ የቀድሞ ተጨዋች ሸዋረጋ ደስታ በዚህ ሳያበቃ ቁጭት የወለደው
“የባንኮች እግር ኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክትን” ከመጽሐፉ ጋር በማስመረቅ ተጨማሪ አዲስ ታሪክ አጽፏል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና
አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያምን ጨምሮ በርካታ የታላላቅ ባንኮች
ፕሬዚዳንቶችን የቢዝነስ ሰዎችና የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት በአንድ ቀን ሁለት ታላላቅ ክንውኖችን በኢትዮጵያ ሆቴል የፈፀመውን
ሸዋረጋ ደስታን የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክሲኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ እንዲዚህ አይነት መጽሐፍ መፃፍ አያስፈራም? ሲል
በወፍራሙ ጠይቆታል፡፡ “የሚያስፈራኝ መጽሐፍ መፃፌ ሳይሆን የእግር ኳሱን ሸፍጥ እያየሁ ዝምታን ብመርጥ ነበር” ሲል ረገጥ
አድርጎ ምላሽ ሰጥቶታል፡፡ “ከሀብታም ልጆች ሳንቲም ለመሰብሰብ ሳይሆን ጎዳና ላይ ወጥተው ቢንዚን የሚስቡትን ታዳጊዎች
ለመታደግ ነው ፕሮጀክት ያቋቋምኩት” የሚለው የቀድሞው ተጨዋች የአሁኑ ደራሲና የፕሮጀክት ባለቤት የሆነው አመለ ሸጋው
ሸዋረጋ ደስታ ከጋዜጠኛው ጋር የነበረው ቆይታ ከዚህ በታች ባለው መልኩ ተጠናክሮ ቀርቧል፡፡
ሀትሪክ፡- …በየትኛው ስምህ ልጥራህ…?
ሸዋረጋ፡-…ዳቦ ተቆርሶ በወጣልኝ ሸዋረጋ ደስታ በሚለው ነዋ… (ሳቅ)… ከዚህ ውጪ ደግሞ…ማን ብለህ ልትጠራኝ
አስብክ…?
ሀትሪክ፡- …ማለት በየትኛው የማዕረግ ስምህ ልጥራህ… የቀድሞው ተጨዋች ሸዋረጋ…?…የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት
ባለቤት… ሸዋረጋ…?… ወይስ ደራሲው ሸዋረጋ ደስታ…?… በየትኛው… ብጠራህ… ምቾት ይሰማሀል…?
ሸዋረጋ፡-…እ….(ሳቅ)… እውነት ለመናገር ከሆነ እኔ ለደራሲነት ገና አልበቃሁም…እንደው…ከውስጤ ገንፍዬ ካልወጣሁ
እያለ የሚታገለኝን የመፃፍ ረሃቤን ለማስታገስ የአቅሜን ሞነጫጨርኩ እንጂ ደራሲ ለመባል አልበቃሁም…፤… ደራሲ የሚለውን
ከባድ ኃላፊነት ወይም መጠሪያ ለመዋስ ገና ብዙ የሚቀሩኝ ነገሮች አሉ፤…ከሁሉም… ከሁሉም ግን… የቀድሞ ተጨዋች… ብለህ
ብትጠራኝ…በጣም ደስ ይለኛል…፤ … በትክክልም ይገልፀኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …ብዙዎች እግር ኳስ ተጨዋች ቅሪላ ከመጠለዝ ባለፈ እውቀት እንደሌላቸው… መጽሐፉ መፃፍ አይደለም መፅሀፉ
የማንበብ አቅም እንደሌላቸው አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ይታያል…፤…አንተ ከአንድም ሁለቴ መፅሐፍ በመፃፍህ ይሄን አመለካከት
የሰበርከው ይመስልሃል…?
ሸዋረጋ፡- …እግር ኳስ ተጨዋችን በስፖርት ቤተሰቦች በህዝቡም ዘንድ እንደ ደደቦች ምንም እውቀት እንደሌላቸው አድርጎ
የማሰብ ነገር በስፋት ይስተዋላል፡፡ ግን ይሄ ፍፁም የተሳሳተ በትክክል የተጨዋቾችን ማንነት የማይገልፅ የተሳሳተ ድምዳሜ ነው፡፡
በጨዋታ ዘመናቸውም ይሁን የጨዋታ ዘመናቸው ከተጠናቀቀ በኋላ በርካታ ዶክተሮች፣ ኢንጂነሮች፣ ፕሮፌሰሮች ወይም ሀገር
ወክለው በአለም ደረጃ በትልቅ ኃላፊነት የሚሰሩ አሉ፤ ይሄንን ከመዘንጋት ወይም ለማወቅ ካለመፈለግ እግር ኳስ ተጨዋቾችን
ቅሪላ ከመጠለዝ ውጪ ስማቸውን እንኳን በደንብ መፃፍ የማይችሉ ደደቦች አድርጎ የማሰብ ስህተት በስፋት ይታያል፡፡ ይሄ
አመለካከት ግን በትክክል ተጨዋቾችን የማይገልፅ መሆኑን ነው ማንሣት የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- …ብዙው ጊዜ በእግር ኳስ ተጨዋቾች ባልተለመደና ባልታየ ሁኔታ ከአንድም ሁለት መጽሐፎችን ፅፈህ ለአንባቢያን ጀባ
ብለሃል፤ ይሄ የስነ ፅሁፍ አቅምህ አሁን የመጣ ወይስ በተጫዋችነት ዘመንህ አብረህ የነበረ ነው…?
ሸዋረጋ፡- …እንዲህ እንድ አሁኑ ሞልቶ አይፈስስ እንጂ…ነፍሴ ወደ ስነ ፅሁፉ ትጎትተኝ ነበር…፤…ባንክ እያለሁ በተጫዋችነት
ዘመኔ አንድ ቀን መጽሐፍ እንደምፅፍ የቅርብ ጓደኛዬ ለሆነው ፍቅሩ ተፈራና በአካባቢው ለነበሩ ሁሉ እርግጠኝነት በተሞላበት
ስሜት እናገር ነበር፡፡ በወቅቱ ምክንያቱን በትክክል በማላውቀው ሁኔታ ውስጤ ፃፍ ፃፍ እያለኝ እሞነጫጭር ስለነበር መጽሐፍ
የመፃፍ ምልክት ይታይብኝ ነበር፡፡ በዚህ በኩል በተለይ ደግሞ አሰልጣኞቼ የሚያስለጥኑኝን ነገር በሙሉ ማታ ገብቼ የመፃፍ ልምዱ
ነበረኝ፤ እንደዚህ እንደ አሁኑ ለመጽሐፍነት ይበቃል ብዬም ባይሆን ለስሜቴ ማስታገሻ የተማኝን፣ የታዘብኩትን ያየሁትን
እሞነጫጭር ነበር፡፡ ቀኑን በትክክል ባላውቀውም አንድ ቀን በስፖርቱ ዙሪያም ይሁን በሆነ ትልቅ ርዕስ ጉዳይ መጽሐፉ እንደምፅፍ
ውስጤ ደጋግሞ ይነግረኝ እንደነበር ሳስታውስ ከበፊት ጀምሮ የመጣ ጉዳይ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ የተጨዋችነት ስሜቴ አይሎ ሸፍኖት
እንጂ አብሮኛ የኖረ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የደራሲነት ዓለምን በይፋ መቀላቀልህን ያበሰረው “የክለቦች ህብረትና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውዝግብ እውነታዎች”
የሚለው መፅሐፍ ጭብጡ ምንድነው…?
ሸዋረጋ፡- …የመጽሐፉ ርዕስ አፍ አውጥቶ እንደሚናገረው በከፍተኛ ሁኔታ ስለቆሸሸው እግር ኳስ፣ ስለተሰሩ
ሸፍጦች፣ስለውዝግቡ መነሻና መድረሻ ለመዳሰስ ይሞክራል፤ መፍትሔ ነው ያለውንም ይጠቁማል። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ከ1995 ወዲህ ሠላሙን ተነጥቋል፤ ሠላሙን ያጣው ደግሞ ወደ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በመጡ እውቀትም ሆነ አቅሙ
የሌላቸው የእግር ኳስ ሣይሆን የስልጣን ፍቅር እንቅልፍ ያሳጣቸው፣ በእግር ኳሱ ለመነገድ በፖለቲካ ሽፋን የሚመጡ ሰዎች እግር
ኳሱን ከፉኛ አቆሽሸውታል፡፡ ይሄ ነገር እንዲለወጥ ውስጡ ሆኜ ታግያለሁ፤ ግን ይሄ ብቻውን በቂ ሆኖ ስላላገኘሁት የችግሮቹን
ምንጮች ለመጠቆም፣ ቀጣዩ ትውልድም፣ የእግር ኳሱ አመራርም የመስታወት ያህል እንዲመለከትበት፣ የውዝግብ መከላከያ
ብቻ ሣይሆን ለውዝግብ መፍቻም መነሻ (ሪፈረንስ) እንዲሆን የተፃፈ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ያልታደለ ነው፤
በተለያየ አጋጣሚ ፖለቲካን ተንጠላጥለው፣ ገንዘባቸውን ረጭተው ወደ ደካማው እግር ኳስ የመጡ ሰዎች ስቃዩን
አብዝተውበታል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የተነሳውን ውዝግብ ቁልጭ አድርጎ ለማሣየት የሚሞክር
በእውነተኛ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- “የክለቦች ህብረትና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውዝግብ እውነታዎች” የሚል ርዕስ በሰጠኸው ሁለተኛው መጽሐፍህ
በብዙዎች የማይደፈርና የማይነካካ ነገር ነው የነነካኸው፤ ይሄንን መፃፍ አያስፈራም…?
ሸዋረጋ፡- …ለአኔ እውነትን መፃፍ አያስፈራም፤ በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች መፃፍ እያፃፍኩ እንደሆነ ከተለያየ ሚዲያ ሲሰሙ
“ምን አለ ቢቀርብህ…፤መኖር አትፈልግም…እንዴ?”…የሚሉ አሸማቃቂ ቃላትን ሳይቀር በመጠቀም ብዕሬ እዲነጥፍ ታግለዋል፡፡
ይሄ እኮ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም ስፖርት ነው፤ እኔ ደግሞ የሀገሬ እግር ኳስ ይመለከተኛል፤ እግር ኳሱን የማውቀው በወሬ ደረጃ
አይደለም… ተጫውቼያለሁ߹ ላቤን አፍስሼያለሁ߹ ደምቼበታለሁ፡፡ በዚህ ደረጃ ዋጋ የከፈልኩበት እግር ኳስ የተለያዩ ሸፍጦች፣
በደሎች ሲሰሩበት አይቼ ማለፍ የምችልበት አዕምሮ የለኝም፡፡ ህመሙ ውስጤ ድረስ ዘልቆ ስለሚሰማኝ “እባክህ ይቅርብህ”
ብለው የመከሩኝን ለምክሩ አመሰግናለሁ ብዬ መፃፌን ነው የቀጠልኩት፡፡ አሁን መጽሐፉ ሲመረቅ ብዙዎች ደንግጠዋል፡፡ አይነኬ
የተባሉ የማይደፈሩ ነገሮችን ደፍረሃል፤አትፈራም ወይ ብለውኛል። እኔን የሚያስፈራኝ መጽሐፍ መፃፌ ሳይሆን ይሄንን ሁሉ የእግር
ኳሱን ሸፍጥ እያየሁ ምንቸገረኝ የራሱ ጉዳይ ብዬ ዝምታን ብመርጥ ነበር፡፡ ይሄን ከመፃፍ ይልቅ በዝምታ በማለፌ ሁሌም
አዕምሮዬ በጥያቄ እየወጠረ ሲያስጨንቀኝ ከምኖር መተንፈስን ነው የመረጥኩት፡፡
ሀትሪክ፡- “የክለቦች ህብረትና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውዝግብ እውነታዎች” የማለው ሁለተኛው መጽሐፍህ ለእግር ኳሱ ጥሎት
የሚያልፈው ቁም ነገር ያለው መልዕክት አለ ትላለህ…?
ሸዋረጋ፡-ይሄ መጽሐፍ እኔ በውዝግቡ ወቅት አንደኛው ተዋናይ ስለነበርኩ ችግሮቹ በወሬ ሣይሆን በተግባር ነው የማውቀው፤
የፃፍኩትም ከዚህ በመነሣት ነው። ሀገራችን እስከመታገድ፣ የስፖርት ቤተሰቡ ስሜት እስከመጎዳት ፣ደካማው እግር ኳስ ላይ
ጭካኔ የተሞላበት ፍርድ እስከመፍረድ የደረሰ ሠላሙን ሲነጥቁ የነበሩ ወገኖች እነማን እንደሆኑ የስፖርት ቤተሰቡም ህዝቡም
ጥርት ያለ ምስል የለውም፤ የተደበላለቀ ነገር ነው የነበረው። የእግር ኳሱን መንደር ሲያሸብር የነበረው ማነው? ለሠላሙ ዋጋ
ሲከፍልስ የነበረው? የሚለው ጥርት ብሎ አልታወቀም፡፡ ይህ መጽሐፌ ግን ይሄንን ፍንትው አድርጎ ማሣየት ይችላል ብዬ
አምናለሁ፡፡ ለወደፊት እግር ኳሱ ተመሳሳይ ችግር ላይ እንዳይወድቅ ለታዳጊዎች፣ ወደ ፌዴሬሽኑ አመራርነት ለሚመጡ፣ የእግር
ኳሱን ችግር መነሻና መድረሻውን ማወቅ ለሚፈልጉ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግር ላይ ጥናት (Reserceh) ማካሄድ ለሚፈልጉ
ትልቅ ግብአት(Reference) ይሆናቸዋል፤ ትምህርት ይሰጣል ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄን መጽሐፍ የፃፍከው የሆነ ወገንን ለማጥቃት ነው ብለው የሚያስቡ ቢፈጠሩ መልስ አለህ…?
ሸዋረጋ፡- መጽሐፍ የሚፃፈው ለበቀል አይደለም፤ ይሄ መጽሐፍ ለታሪክ የሚቀመጥ፣ ትናንት የነበረው የእግር ኳሱን ጉድፍ
የሚያሳይ ለዛሬ መማሪያ እንጂ መበቂያ፣ ግለሰብን ወይም የሆነ ቡድንን ለማጥቃት አይደለም፡፡ በመጀመሪያ በዚህ ደረጃ የተቃኘ
አዕምሮ መጽሐፍ ለመፃፍም አቅም የለውም፡፡ በአጭሩ በመፅሐፌ የማንንም ስም ለማጥፋት ወይም ማንንም ለመጥቀም
አሊያም ለመጉዳት ስል እንዳልፃፍኩና እግር ኳሱን ለመታደግ የተፃፈ ተደርጎ እንዲወሰድልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ብዙዎች በዚህ በመፅሐፍህ ዙሪያ የሚዛናዊነት ጥያቄን ያነሱብሃል፤ በዚህ ብዙዎችን ለሁለት ከፍሎ ሲያወዛግብ የነበረው
ጉዳይ ላይ አንደኛው ተዋናይ አንተ መሆንህን የሚያውቁ ሸዋረጋ ከስሜት ወጥቶ ምን ያህል ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ሚዛናዊ መጽሐፍ ሊፅፍ
ይችላል? ብለው ይጠይቁሃል።አንተስ ከዚህ አንፃር ምን ያህል ሚዛናዊ ነኝ ትላለህ?
ሸዋረጋ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳህው፤ እንዳልከው በውዝግቡ ውስጥ እኔም ነበርኩ፤ ይሄ የሚካድ አይደለም፡፡ የእኔ
በውዝግቡ ውስጥ መኖር ሚዛኑን ከማሳት ይልቅ ይጠብቅኛል የሚል እምነቱ ነው ያለኝ፡፡ ምክንያቱም “… ማን
ይናገር…የነበረ…ማን ያርዳ…የቀበረ…”…እንዲሉ አበው… ከውጪ ሆኖ በስማ በለው ከምፅፍ ውስጥ ሆኜ ያየሁትን፣ የታዘብኩትን
በማስረጃ አስደግፌ መፃፌ ይበልጥ ሚዛኑን እንዳይስት ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ የመሐፉን ሚዛናዊነት ከእኔ ይልቅ
አንባቢ ነው የሚፈርደው፤ሚዛናዊ ነው አይደለም የሚለውን ትዝብቱን ለአንባቢው እንተውለት፡፡
ሀትሪክ፡- …ብዙዎች ዝምታን በመረጡበት ሰዓት አንተ በዚህ ዙሪያ መጽሐፍ እንድትፅፍ ምን ገፋህ ወይም አስገደደህ?
ሸዋረጋ፡- ተጫውቼ፣ በተለያየ ኮሚቴ ውስጥ በአመራርነት ውስጥ ሠርቼ ያለፍኩ በመሆኑ የህመሙ ስሜት ለእኔ ከፍተኛ
ነው፤ ይሄ በራሱ ብዕርን ከወረቀት እንዳገናኝ፣ ኃላፊነቴን እንድወጣ ያስገደድኛል፤ አይቶ እንዳላየ ማለፍ ለእኔ አይቻለኝም።
የለፋሁለት፣ የደማሁለት እግር ኳስ ነው ጠምዝዞ እንድፅፍ ያስገደደኝ፡፡ በዚህ ደረጃ ግዴታዬን ባልወጣ ሁሌም አዕምሮዬ
በሚጠይቀኝ ጥያቄ ስወጠር ነው የምኖረው፡፡
ሀትሪክ፡- መፅሐፉ በርካታ ግለሰቦችን ቡድኖችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚነካ ከመሆኑ አንፃር መፅሐፉ ለንባብ ከመብቃቱ
በፊት እንዳይፃፍ በርካታ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስህ እንደነበር የሰማሁት ነገር አለ፤ እስቲ በዚህ ዙሪያ አጫውተኝ…?
ሸዋረጋ፡- …ለዛቻና ለማስፈራሪያ ፊት የምሰጥ ሰው ባለመሆኔ እንጂ መጽሐፉ ገና ወደ ህትመት ሳይገባ በጠዋቱ ብዙ
ማስፈራሪያና ዛቻዎች በተለያየ መንገድ አስተናግጄያለሁ፡፡ በተለያዩ ሰዎች “አትመከሩትም እንዴ?” በማለት የቅርብ ወዳጆቼና
ቤተሰቦቼ ድረስ ተኪዶ አርፌ እንድቀመጥ ተነግሮኛል፡፡ በጣም የሚገርመው በእጅ ስልኬ (ሞባይሌ) ሣይቀር እየተደወለ “መኖር
አትፈልግም ወይ?” ሁሉ ተብያለሁ፤ በአጭሩ ያልተባልኩት የለም።እነዚህ ሁሉ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች ብዕሬን ከማድረቅ፣ እኔን
ወደ ኋላ ከመጎተት ይልቅ ይበልጥ ጉልበት ነው የሆነኝ፡፡ እኔ ልፈራ አልችልም፤ ምናልባት መፍራት ካለብኝ እንደ እግር ኳሱ
ባለድርሻ ዝም ብዬ ብቀመጥ ነበር፤ በጣምም የሚያስፈራው ይሄ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ መጽሐፍ በስተጀርባ ሌላውን ወገን ማጥቃት የሚፈልጉ አካላት አሉ፤ የገንዘብ ምንጮችም እነሱ ናቸው፤ በሚል
ለሚነሣብህ ጥያቄ አሳማኝ መልስ አለህ…?
ሸዋረጋ፡- …ይሄ የሰውን ልፋትና ድካም አፈር ለማስበላት የተወራ ልብ ወለድ ወሬ ነው፤ ከዚህ መጽሐፍ በስተጀርባም ሆነ
ከፊት ያለው አንድ ሸዋረጋ ደስታ ብቻ ነው። መጽሐፌን ለማሳተምም የማንንም ደጅ አልጠናሁም፤ የማንንም እጅም አላየሁም፡፡
በቤተሰቦቼ ጉሮሮ ላይ ፈርጄ፣ ከቤተሰቦቼ አፍ ላይ ነጥቄ ነው ያሳተምኩት፤ እውነቱም ይሄ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ሌላው የክለቦችና የፌዴሬሽኑ ውዝግብ ከተፈጠረ 10 አመታት አልፈውታል፤ ከዚህ አንፃር መጽሐፉን ለመፃፍ
አልዘገየህም?
ሸዋረጋ፡- …ምናልባት አደባባይ የወጣውን ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረውን ውዝግብ መሆኑ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ከውዝግብ ወጥቶ አያውቅም፤ አሁንም እግር ኳሱ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ካልመጣና ስፖርት ስፖርት የሚሸቱ ሰዎች በፖለቲካ
ውክልና ሳይሆን እውቀትን መሠረት አድርገው እስካልመጡ ድረስ መወዛገባችንም የሚቀጥል ነው። ውዝግቡ 10 አመት አልፎታል
አልዘገየህም ወይ? ለተባለው ጊዜውን ብቻ ከቆጠርነው ሊመሰል ይቸላል፡፡ ግን የዚህ መጽሐፍ ዋና አለማ ለታሪክ የሚቀመጥ፣
ለነገ ችግሮቻችን መነሻ የሚሆን ግብአትና ትምህርት ለማግኘት የሚረዳ ነው፡፡ በእግር ኳሱ ችግርና መፍትሔ ዙርያ ጥናትና ምርምር
ለማድረግ ለሚፈልጉ መነሻ እንዲሆን ሲሆን ሌላው በውዝቡ ለሁለት የተከፈለው የስፖርት ቤተሰብና ህዝቡ የችግሩን ምንጭና
ተዋናዮች እንዲያውቅ ከፍ ሲልም እንዲማርበት ከዚህ በተመነሳት ለለውጥ የሚረዱ ሃሳቦች እንዲፈልቁበት በማሰብ ነው
የተፃፈው፡፡ ለታሪክ ከማስቀመጥ መነሻ እንዲሆን ከማሰብ አንፃር መጽሐፉ አሁን መውጣቱ ብቻውን ዘገየ ያስብለዋል ብዬ
አላስብም፡፡
ሀትሪክ፡- መጽሐፉ ያለውን አነጋጋሪነት ተከትሎ እንዲሁም ያልተደፈረና ያልተነካካ አካባቢው የሚዳስስ ከመሆኑ አንፃር ምን
አይነት ምላሽ ትጠብቃለህ… ከአዎንታዊዉ ይልቅ የምትሰጋው ነገር ይበረታል?
ሸዋረጋ፡- …እንግዲህ እኔ አንድ የማውቀው ነገር ምንድነው አንድ መጽሐፍ ስትፅፍ አዎንታዊ ነገር ብቻ መጠበቅ
የለብህም፤እንደውም የሚባለው ምንድነው መጽሐፍ ፀሐፊ ወይም ደራሲ ማለት እርቃኑን የቆመ ሰው ማለት ነው፤እርቃኑን
የቆመ ሰው ለተቋውሞም ይሁን ለድጋፍ የተጋለጠ ነው፤ እኔ የአቅሜን ሞክሬ ገምገሙኝ ተቹኝ እያልኩ ነው ያለሁት፡፡ ደግሞ ድጋፍ
እንዳለ ሁሉ ትችትም አለ፤ ሁለቱም ተነፃፃሪ ናቸው፡፡ ሙገሣ ብቻ እገኛለሁ ብዬ የፃፍኩ የዋሀ ሰውም አድርገህ አታስበኝ፡፡ እኔ
ሞክሬያለሁ፤ አንባቢ የጎደለውን እየሞላ፣ የተጣመመውን እያቃና፣ የተሳሳትኩትን እያረመ እንዲያነብ ነው የምጠይቀው። ከዚህ
ውጪ የሚመጣ ነገር ካለም ለመቀበል የተዘጋጀሁ ሰው ነኝ፤ በተለይ ሃሣብን በሃሣብ ለሚታገሉ ክብር አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-እስከ አሁን ሁለት መጽሐፎችን ፅፈሃል፣ የደራሲያንን አለምም በሁለቱ መጽሐፎችህ በይፋ ተቀላቅለሃል ከዚህ አንፃር
ሸዋረጋ ራሱን እንደበቃላት ደራሲ (ፀሐፊ) ይቆጥራል…?
ሸዋረጋ፡- …በነገራችን ላይ እኔ ደራሲ የሚል ስም ሊሰጠኝ አይገባም፤ ለደራሲነት አልበቃሁም እኔን ደራሲ ማለት የደራሲነትን
ክብር ማሣነስም ነው። እኔ ገና ተማሪ ነኝ፤ ቤተሰቦቼም ስሰራበትና አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ትልቁን ድርሻ የተወጣው ንግድ ባንክ
ያስተማረኝ መታበይን አይደለም፡፡ ከመታበይ ይልቅ ዝቅ ማለትን ከቤተሰቦቼና ከንግድ ባንክ ተምሬያለሁ፤ ታንፅቼ ያደኩትም በመ
ታበይ አይደለም፡፡
እኔ እኮ ሞከሪኩ እንጂ መጽሐፍ ፅፌያለሁ ብዬ አላብስም፤ የስነ ፅሁፉ አለም ትንሹ ተማሪ ነኝ፡፡ በርካታ ታላላቅ ፀሐፍትና
ደራሲያን ባሉበት ሀገር እኔ ጀማሪው ራሴን በዚህ ደረጃ የጠራሁ እለት አለአዋቂነቴን ራሴው በራሴው እንደመሰከርኩ ነው
የሚቆጠረው፡፡ ስለዚህ ራሴን በዚህ ደረጀ እንኳን ልጠራ አስቤውም አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡-ሁለተኛው መጽሐፍህ የመጨረሻ…ወይስ ሌላ የአእዕምሮ ጥማቂ ውጤት የሆነ መጽሐፍን ለአንባቢያን እነሆ በረከት
የማለት ሃሳቡ አለህ…?
ሸዋረጋ፡-…ከውስጤ ገንፍዬ ወጥቼ ካልፈሰስኩ እያለ የሚወተውተኝ የመፃፍ ረሃብ እስካልታገሰልኝ ድረስ መፅሐፍ መፃፌን
አቋርጣለሁ ብዬ አላስብም፤ የሚገርምህ ነገር እነዚህ ሁለት መጽሐፎቼን አዕምሮዬ በጥያቄ እየወጠረ ፋታ ስላሳጠኝና ባለችኝ
ትንሽ የመፃፍ አቅም የአቅሜን ጡብ ላስቀምጥ ብዬ ከህልምነት ወደ እውነትነት ተቀይረው መፅሐፍ ሆነው አንባቢ እጅ ደረሱ
እንጂ በየዕለቱ የምፅፋቸው ብዙ መፅሐፍ መሆን የሚችሉ ፅሑፎች ተጠርዘው ተቀምጠዋል፡፡ አምላክ ሲፈቅድ እነዚህ ሁሉ
በቅድም ተከተል ለአንባቢያን ይበቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን በይፋ ከተመረቀው መፅሐፍ እኩል ተፅፎ ወደ መጨረሻው የህትመት
ምዕራፍ የተጠጋ “ክፉ ሰው” የሚል ርዕስ የሰጠሁት መጽሐፍ አለ፤ እሱን በፈጠረኝ አምላክ እርዳታ በቅርቡ ለንባብ የሚበቃው
3ተኛው መጽሐፌ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- “ክፉ ሰው” የሚለው ርዕስ ያልተለመደና ወጣ ያለ ይመስላል፤ ይህ መጽሐፍ በምን ላይ የሚያጠነጥነው ወይም መቼቱ
ምንድነው…?
ሸዋረጋ፡-አሁን ገና ወደ ህትመት ባልገባው 3ተኛው መጽሐፌ ዙሪያ ብዙ ባትጎረጉረኝ ደስ ይለኛል፤ እኔም ብዙ ነገር
አልነግርህም፡፡ ግን የመጽሐፉ ጭብጥ ክፋትን ህይወታቸው፣ክፋትን የሀይማኖት ያህል አጥብቀው የክፋት ጥይታቸውን በሰላማዊ
ሰዎች ላይ ያርከፈከፉ ሰዎች ሴራና ተንኮል ላይ የሚያጠነጥን ነው፤ እንደምታውቀው አለማችን ብዙ ደጋግ ሰዎችን አቅፋ እንደያዘች
ሁሉ ብዙ ክፍ ሰዎችንም በጉያዋ ሸጉጣ ይዛለች፡ ይሀ መጽሐፍ በእነዚህ ክፋትን የኃይማኖታቸው ያህል አጥብቀው የያዙ ሰዎችን
በተለይ የክፋት ጥግ የሆነን አንድ ግሩፕ ገሃዳዊ ዓለም ዕውነታ በመጨለፍ ብዙዎች ይማሩበታል፤ ይለወጡበታል ከሚል ነው
በአቅሜ ለመሞነጫጨር እየሞከርኩ ያለሁት፡፡
ሀትሪክ፡-በተለይ የክፋት ጥግ የሆነን አንድ ግሩፕ ስትል አብራራልኝ እስቲ…?
ሸዋረጋ፡-አሁን በዚህ ዙሪያ ባትወተውተኝ ደስ ይለኛል፤ በጣም ቸኩለህ ከሆነ መጽሐፉ በቅርቡ ታትሞ ሲወጣ መልሱን እዛው
ታገኘዋለህ፤ይዐን ካልኩህ ይበቃል፡፡
ሀትሪክ፡-ባለፈው ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሆቴል በአንድ ቀን ሁለት ታላላቅ ኹነቶችን አከናውነሃል፣ “የክለቦች ህብረትና የእግር ኳሱ
ፌዴሬሽኑ ውዝግብ እውነታዎች” የሚል መጽሐፍ አስመርቀሃል፣ ከዚህ ውጪ የነገ የእግር ኳሱ ትንሳኤ የሚሆን “የባንኮች እግር ኳስ
ፕሮጀክት ማሰልጠኛ” የሚል አካዳሚ በይፋ መከፈቱን አብስረሃል፤ ሁለት የእግር ኳስ ታላላቅ ጉዳዮችን በአንድ ላይ ለስኬት ማብቃት
አይከብድም…?
ሸዋረጋ፡- እውነት ለመገር በጣም ከባድ ነው ብቻ ሣይሆን በጣም ፈታኝ ነው፤ አንዲት ሴት መንታ ልጆችን አርግዛ፣ምጥ
አምጣ መንታ ልጆችን እንደምትወልድ ሁሉ እኔም ሁለቱን ታላላቅ ነገሮች እምጬ የወለድኩ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ ሁለቱን ታላላቅ
የእግር ኳስ ጉዳዮች በአንድ ቀን ባማረና በደመቀ ሁኔታ አስመርቄ ስጨርስ ደግሞ የተሰማኝ ስሜት የተወለዱትን ልጆቼን አሣድጌ፣
ኩዬ የዳርኩ ያህል በቃላት የማልገልፀው የደስታ ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ እውነት ለመናገር ያለፉትን አመታት በመጽሐፌና በፕሮጀክቱ
ምክንያት ቤተሰቦቼን በድያለሁ፤ ፍቅር ነፍጌያቸዋለሁ፣ ማህበራዊ ግንኙቴንም አጥቼ ብዙ ወዳጆቼን አስቀይሜያቸዋለሁ፡፡ ብዙ ዋጋ
ከፍዬ አምላኬ የልፋቴን ዋጋ ስላሳየኝ የጠየኩትን ስላልነሳኝ ከልቤ አመሰግነዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-“የባንኮች እግር ኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት”ን ለማቋቋም ሃሳቡ በውስጥህ እንዴት ተጠነሰሰ…?
ሸዋረጋ፡-ሌላ ምን ምክንያት የለኝም፤ ቁጭትና ቁጭት ብቻ ነው፤ ይሄ ፕሮጀክት ቁጭት የወለደው ፕሮጀክት ነው ፤እኔ ለንግድ
ባንክ የተለየ ቦታና ክብር ነው ያለኝ፤ንግድ ባንክ ኳስ የተጫወኩበት ብቻ ሣይሆን ያስተማረኝ፣ አብልቶ አጠጥቶ ያሳደገኝ
ባለውለተኛ ድርጅቴ ነው፡፡ የለፋሁለት፣ የደማሁለት፣ ትልቅ ታሪክ ያለው የእግር ኳስ ክለብ በ30 ደቂቃ መግለጫ የመፍረሱን
መጥፎ ዜና ውስጤ ሊቀለው አልቻለም፤ ልክ የቅርብ ዘመዴን በሞት የተነጠቅኩ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ እግር ኳስ ክለቡን
ከመፍረስ ለመታደግ ያልረገጥኩት ደጅ፣ ያለመንኩት ባለስልጣን የለም፡ ከዚህ አልፎም ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ስዎችን
ፊርማ (ፒቲሽን) በማስፈረም በወቅቱ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ጋጭምር ድረስ ሄጄ አቤት ብልም
ሰሚ ጆሮ አላገኘሁም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስምና አስተዋፅኦ ያለው ክለብ በ30 ደቂቃ መግለጫ ፈረሶ ታሪክ ሆኖ
መቅረቱ በውስጤ ከፍተኛ እልህና ቁጭት ፈጠረ፤ ቀደም ሲል በውስጤ የነበውን የሀገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ መፍትሔው
በታዳጊዎች ላይ መስራት ነው ስለዚህ ፕሮጀክት ማቋቋም አለብኝ የሚለው በውስጤ የበረውን ሃሣቤን ቀስቀሰው፡፡ የትልቁ ታሪክ
ባለቤት የሆነው የባንክ ስምና ታሪክ ተነስቶ መቅረት የለበትም ስሙ የሚታወስበት የሚዘከርበት አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ
ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ በመጨረሻ የባንኮች እግር ኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክትን ወደ ማቋቋም ገብቼ ባለፈው ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሆቴል
በተደረገ ደማቅ ስነ-ስርዓት ምስረታውን ይፋ ለማድረግ በቅቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የፕሮጀክቲ ስም “የባንኮች እግር ኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት” ነው፤ ይሄ ስያሜ ከንግድ ባንክ ጋር ፕሮጀክቱን የሚያገናኘው
ነገር አለ…?
ሸዋረጋ፡-ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፤ የፕሮጀክቱ ስምም ታላቁን የባንክ እግር ኳስ ክለብ እንዲታወስ፣ እንዲዘከር
የአቅሜን ሀውልት ለማቆም እንጂ የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡
ሀትሪክ፡-ብዙ የታዳጊዎች ፕሮጀክቶች በተመሰረቱበት ፍጥነት ሲፈርሱ ታይተዋል፣ከዚህ ምን የተማርከው ወይም የወሰድከው ነገር
አለ…?
ሸዋረጋ፡- እንዳልከው ነው እኛ ሀገር መጀመር ቀላል ነው፤ በጥንካሬ መቀጠሉ ነው ከባድ፡፡ በእኛ ሀገር ባለሀብቶች መንግሥትና
ግለሰቦች ፕሮጀክት አቋቁመው አይተናል፡፡ ተመስረቱ ተብሎ ተነግሮን ከመቼው እንደሚከስሙ አይታወቅም፡፡ አሁን የመጣው ፋሽን
ደግሞ ምንድነው ፕሮጀክት አቋቁሞ የሀብታም ልጆችን እያስከፈሉ ማሰልጠን ነው፤ የእኔ ፕሮጀክት ግን ከዚህ የተለየ አላማን ያነገበ
ነው…
ሀትሪክ፡- …የተለየ አላማን… ያነገባ ነው ስትል…?
ሸዋረጋ፡- …እኔ የሀብታም ልጆችን እያሰለጠንኩ ገንዘብ የመሰብሰብ አላማ ይዤ አይደለም ፕሮጀክቱን ያቋቋምኩት፤ ትውልድ
የማዳን ሀገርን የሚጠቅም ዜጋን የመፍጠር ትልቅ ራዕይን የሰነቀ ነው፤ በለጋ እድሜያቸው አሣማኝ ባልሆነ ምክንያት ወይም
በተለያየ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ጎዳና ላይ ወጥተው ቤንዚን እየሳቡ በየትራፊክ መብራቱ ላይ አስከፊ ህይወት የሚገፉትን
ታዳጊዎች ወደ ማሰልጠኛ ማዕከላችን በማምጣት ከሱሳቸው ፀድተው ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጋ
የማድረግ አላማን ያነገበ ነው፡፡ በእግር ኳስ ችሎታቸው ነጥረው የሚወጡትን ቡተለያዩ ክለቦች ታቅፈው ራሣቸውንም
ሀገራቸውንም እንዲጠቅሙ ማድረግ ነው፡፡ ሌሎቹን ደግሞ በሚወዱት እግር ኳስ አማካይነት ህይወታቸውን ወደ ትክክለኛው
መስመር የመመለስ ትልቅ አለማን ሰንቄ ነው የተነሣሁት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገና ከወዲሁ ብዙዎች ይዤ የተነሣሁትን አላማ
በመደገፍ ታዳጊዎቹን በትምህርትና በሙያ ሥልጠና ሊያግዙኝ ወደፊት እንደየዝንባሌያቸው ከእግር ኳሱ በተጨማሪ ሊደግፉኝ ቃል
ገብተዋል፡፡ ዋናው ትልቁ ነገር እግር ኳሱን የሚጥቅሙ ተጨዋቾችን መፍጠር ቢሆንም ከጎዳና ህይወትና ከሱስ የመገላገል
አላማንም ደርቦ የያዘ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የማሰልጠኛ ፕሮጀክት የራሱ የሆኑ ወጪዎች አሉትና የገቢ ምንጭህ ምንድነው…?
ሸዋረጋ፡-እስአሁን ድረስ እየሠራሁ ያለሁት ወደፊትም እሰራለሁ ብዬ የገባሁበት ከብተሰቦቼ ጉሮሮ እየነጠኩ ፕሮጀክቱን
ለማንቀሳቀስ ነው፤ እስከአሁን ከኪሴ እያወጣሁ ነው የምሠራው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሆቴል ፕሮጀክቱ በይፋ ሲመሰረት
በርካታ ታላላቅ ሰዎች ይዤ የተነሳሁትን ሃሣብ በመወደድ ከጎኔ እንደሚቆሙ ቃል ገብተውልኛል፡፡ ከክብር እንግዶቼ ያገኘሁት ተስፋ
ይበልጥ እንድገፋበት ብርታትን የሚሰጥ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
ሀትሪክ፡-ፕሮጀክቱን በሙያተኛ በማገዙ በኩልስ ምን የታሰበ ነገር አለ…?
ሸዋረጋ፡- ካለ ሙያተኛ ያውም ታዳጊዎችን እንደ እርሣስ መቅረፅ የሚይታሰብ ነው፤ በተቻለኝ አቅም ፕሮጀክቱን በሙያተኞች
ለማጠር ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ከእኔ የግል ጥረት በተጨማሪ የተከበረ ስብዕና ያላቸው በጎ ፍቃደኛ ሙያተኞችንም አግኝቻለሁ።እንደ
አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ፣ እንደ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አይነት ታላላቅ ሙያተኞች በማንኛውም መልኩ እናግዝሃለን፤ እንደግፍ ሃለን
በማለት በጠዋት ከጎኔ መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል፡፡ ከእነሱ ውጪ የባንክ አሰልጣኝ ሲሳይ የቀድሞ የባንክ ተጨዋት በላቸው
አበራ (ትንሼ)ና ሌሎች ያልጠቀስኳቸው እናግዝሃለን ብለውኛል፡፡ በተይ በላቸው አበራ (ትንሼ) “ኳስ ሰብስብ ብትለኝም
እሰበስባለሁ” ብሎኛል፤ እኔ አሰልጣኝ አይደለሁም፤ ያለሙያዬም ገብቼ አልዘባርቅም፤ ስራውን ለሙያተኛ ነው የምሰጠው፡፡ ያለ
እውቀታችሁ፣ ያለሙያችሁ አትስሩ እያልኩ ገና ለገና ባለቤት ነኝ ብዬ ያለሙያዬ ብገባ ወንጀል ነው፡፡ ገና ለገና እግር ኳስ ተጨዋች
ስለሆንኩ በቂ የስልጠና ሙያ ሳልወሰድ ማሰልጠንን አላስብም፡፡ በበጎ ፈቃድ ለማገዝ አጋርነታቸውን ላሳዩኝና ለሙያተኞች ቦታውን
ሰጥቼ ዞር ነው የምለው፡፡
ሀትሪክ፡- ፕሮጀክቱ በቦርድ እንደሚመራ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፤ አወቃቀሩና የቦርዱ ስብስብ ምን ይመስላል?
ሸዋረጋ፡- ቦርዱ የተለያየ እውቀት ባላቸው ሰዎች የተዋቀረ ነው፤ ካላቸው እውቀት በተጨማሪ በሙያቸው አንቱ የተባሉ ሰዎች
የተካተቱበት ነው፡፡ ለምሣሌ የቦርዱ የበላይ ጠባቂን አቶ ሙሉጌታ ገ/መድህንን ብትወስድ የቀድሞ የንግድ ባንክ ምክትል
ፕሬዝዳንት የነበሩ አሁን የኢስት አፍሪካን በፕሬዚዳንነት በማገልገል ተጨባጭ ስራ በመስራት የሚታወቁ፤ በእውቀት የተሞሉ
እስከጥግ የተማሩ ሰው ናቸው፡፡ የቦርዱን ፕሬዝዳንት አቶ ፍቅሩ ተፈራንም ብትወስድ በቢዝነስ የተሳካለትለት አንቱ የተባለ ሰው
ነው፤ አቶ በድሩ ሙዘይንም እንዲሁም የቢዝነሱን አለም በስኬት የሞላ ሰው ነው፡፡ ከደጋፊዎች አቶ እሸቱ ከበደድ ለስፖርቱ ጥልቅ
ፍቅር ያው ሰው ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ፀሐፊ አሠለፈች ደስታም እንዲሁ በእውቀትዋ በሙያው የምትደግፍ አጋዣችን ናት፡፡ የሚዲያ
ጉዳዮችን በተመለከተ የዚሁ ጋዜጣ ኤክሲክዩቲሽ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ተካቶበታል፡፡ አጭሩ የተለያየ እውቀትና የሙያ
ባለቤቶች ስብጥር ያለው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ ባነሳው የምትለው ካለ እድሉን ልስጥህ?
ሸዋረጋ፡-በመጨረሻ የመጽሐምፉ ሆነ ፕሮጀክቱን ኮጥንስስ አሁን የደረስበት ደረጃ እንዲደርስ በሃሣብ በእውቀታቸውና በሞራል
ጭምር ድጋፊቻውን ያለስስት የሰጡኝን ሁሉ በተለይ ቤተሰቦቼን፣ የቦርድ አባላቱን ከልብ ማመስገን እወዳለሁ፡፡ በዚህ መጽሐፍ
ፐሮጀክት ምክንያት ፍቅር የነፈኳቸው ቤተሰቦቼን ባለቤቴን ወ/ሮ ለምለም ፍቅሬን ልጆቼን ሜሮንና መቅደስ ሸዋረጋን፣
ወንድሞቼንና እህቶቼን እዚህና ከአገር ውጪ ያሉትን፣ ጓደኞቼን ለከፈሉት መስዋዕትነት ምስጋና ይበዛቸው እንደሆነ እንጂ
ስለማያንሣቸው ብታመሰግንልኝ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አሊ አህመድን፣የንግድ ባንክ
ስፖርት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ፣ የባንኩን ማህበረሰብ በጠቅላላ እንዲሁም ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ከጎኔ
የቆመውን ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይና የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡