በኤሌክትሮኒክስ እና ህትመት ሚዲያዎች ረዘም ላሉ አመታት በስፖርት ጋዜጠኝነት ያገለገለው እና እያገለገለ የሚገኘው ምስጋናው ታደሰ በእግሩ ላይ ያጋጠመው ጉዳት ከቤት ሊያውለው ችሏል። ጋዜጠኛ ምስጋናው በተለያዮ ጋዜጦች እና መፅሄቶች በተለይም ሀትሪክ ስፖርት ላይ በሬዲዮ ደግሞ ብሔራዊ ሬዲዮ, Fm 96.3 ፕላኔት ስፖርት የሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ከምስረታው ጀምሮ አብሮ እየሰራ ይገኛል። ሆኖም ግን ከቅርብ ቀናት ወዲህ ባጋጠመው ከፍተኛ ህመም ከሚወደው ሙያ ለመራቅ ተገዷል። ጋዜጠኛ ምስጋናው በድንገተኛ ወድቆ የነበረ ሲሆን ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ እና ችላ በማለቱ የቀኝ እገሩ ላይ እስከ መቆረጥ ሊያደርሰው የሚችል የከፋ ጉዳት ሊዳረግ ችሏል። ትናንት ምሽት ከሀትሪክ ስፖርት ድረገጽ ጋር በስልክ አጭር ቆይታ አድርጎ የነበረው ጋዜጠኛ ምስጋናው 2የስቃይ ለሊቶችን እንዳሳለፈ እና ህክምናውን በአግባቡ መከታተል በመጀመሩ ወደ ማታ ላይ ትንሽ ሻል እንዳለው ተናግሯል። አያይዞም ጋዜጠኛ ምስጋናው የሙያ አጋሮቹ እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ እየደወሉ ለጠየቁት ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል። ምስጋናው በተጨማሪም የህክምና ወጪው ከሱ አቅም በላይ በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳው በፀሎት እና በገንዘብ አቅም እንዲረዳው ተማጽኗል።
በጋዜጠኛ መሰለ መንግስቱ፣ በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 አብሮት የሚሰራው የሙያ አጋሩ ታደለ አሰፋ እና ጓደኛው ሰለሞን ኃ/ሚካኤል የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለምስጋናው ታደሰ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በመጨረሻም ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ በጋዜጠኞች የWhatsApp ግሩፕ ላይ ይህንን መልዕክት አስፍሯል።
“ከምስጋናው ታደሰ
ውድ የሙያ ባልደረቦቼ እኔን ለመታደግ ሁላችሁም በየፊናችሁ እያደረጋችሁልኝ ላለው ርብርብ በፈጣሪ ስም እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ። እውነት ለመናገር መታመሜን ፖስት ሳደርግ እንዲሁ ቀለል አድርጌው እንጂ ጉዳዩ ይሄን ያህል ትኩረት ያገኛል ብዬ በፍፁም አላሰብኩም ነበር፤ ነገር ግን የእናንተም ሆነ የህዝቡ ቀናኢ ምላሽ ከጠበቅኩት በላይ ሆኖ አስደንግጦኛል። እንደ ቀልድ ችላ ያልኩት ነገር ነው ተባብሶ እዚህ ደረጃ ያደረሰኝ። ከቀናት ስቃይ በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ቀለል ብሎኛል። በርካታ የሙያ ጉዋደኞቼና እኔን ለመጠየቅ የፈለጉ ሁሉ ለማግኘት መቸገራቸውን የማገኛቸው ሚስድ ኮልስ ይነግሩኛል። በሌላ ምክንያት አይደለም። ሌሊቱን ስሰቃይ ያለ አንዳች እንቅልፍ ቁጭ እንዳልኩኝ ይነጋብኝና ጠዋት መርፌ ለመወጋት እሄዳለሁ። መርፌው በጣም ከባድ ነው። እሱን ከወሰድኩና ኪኒን ከዋጥኩኝ በሁዋላ በጣም ነው የሚያስተኛኝ። ድንገት የምሳ ሰአት ኪንን ለመዋጥ ስቀሰቀስ አጋጣሚው የጠቀማቸው ብቻ ያገኙኝ ነበር፤ አንዳንዶቹንም በደመነብስ ነበር የማወራቸው። ማታ ድጋሚ ስነሳ በርካታ ምልክቶች አገኛለሁ፤ ግን ድካሙ ስላለ ሁሉንም ማውራት አልቻልኩም። ይህንን ተረዱልኝ። ዛሬ ግን በአፃራዊነት ደህና ስለሆንኩኝ ስልክ ማንሳት ጀምሬያለሁ።”
ኮሚቴው የሚያመጣው ተለዋጭ ሀሳብ ካለ በፍጥነት አሳውቃለሁ
ሁላችሁንም ፈጣሪ ያክብርልኝ
N.B፦ ፀሎት እና ዱአው እንዳይረሳ
ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰን መርዳት ለምትፈልጉ በሚከተሉት የባንክ አካውንቶች መርዳት ትችላላችሁ።
ንግድ ባንክ
1000268456639
አዋሽ ባንክ
01320148371700
የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣና ድረገጽ መላው አባላትም ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ ከህመሙ በቶሎ አገግሞ ወደሚወደው ስራው በቶሎ እንዲመለስ ልባዊ ምኞታቸውን መግለጽ ይወዳሉ። ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ ፈጣሪ ምህረቱን ይላክልህ።
የስፖርት ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ ባጋጠመው ህመም ምክንያት ድጋፍ እየተጠየቀ ይገኛል።
Hatricksport team