በይስሐቅ በላይ
“ያለሁበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን ነው፤ሌሎች መከራዎችንና ፈተናዎችን ይሁን ለበጎ ነው ብዬ ተቀብያለሁ፤ አሁን ግን በቂ ህክምና ካላገኘህ የአይንህን ብርሃን ታጣለህ ማየት አትችልም አስብበት የሚለው የሐኪሞች ምክር አዘል ማስጠንቀቂያ በጣም አስደንግጦኛል፤አሁን በገጠመኝ ፈተና ላይ ይሄ ሲጨመርበት ህይወቴ ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም፡፡ ከሁሉም በላይ ያሳሰበኝና ተስፋ እንድቆርጥ እያደረገኝ ያለው እጄ ማጠሩ ነው፤ሀኪሞች በቂ ህክምና ካላገኘህ አይንህ መጥፋቱ አይቀሬ ነው ብለውኛል በአሁን ሰዓት እንኳን ለህክምና የሚሆን ገንዘብ ቀርቶ የሚላስ የሚቀመስ ለማግኘት የማልችልበት ደረጃ ላይ ነኝ፤ በቃ ምንም ማድረግ አልችልም አምላኬ ይሁን ያለውን መቀበል ብቻ ነው ምርጫዬ፡፡”
ይህን ከላይ የሠፈረውን ልብን የሚነካ ቃል የእንባ ሳግ በተናነቀው፣በተስፋ መቁረጥና በህመም ስሜት ሆኖ ለዝግጅት ክፍላችን የገለፀው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች የነበረው ተሾመ ተፈራ ነው፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ተሾመ ተፈራ (ተሼ ብርቱ) አሁን በከፋ ችግርና ህመም ላይ ወድቋል፤ባሳለፍነው ሣምንት በገጠመው ድንገተኛ ህመም ዘነበወርቅ አካባቢ በሚገኘው አለርት ሆስፒታል አንድ አይኑን ቀዶ ጥገና (ኦፕሬሽን) አድርጓል፡፡ ተሼ ብረቱ በሚለው ቅፅል ስሙ ተለይቶ የሚታወቀው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች አሁን በአለርት ሆስፒታል ሲያደርገው የነበረውን ህክምና አጠናቆ ቢወጣም በቀጣይ በቂና ተከታታይ ህክምና ካላገኘ የአንድ አይኑን ብርሃን ሊያጣ እንደሚችል በሁሉም ባለሙያዎች መነገሩ ቀጣዩን ጊዜ በስጋት አሻግሮ እንዲመለከት አድርጎታል፡፡
ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡናን ማልያ ለብሶ በተጫወተባቸው ከስድስት ዓመታት በላይ በዘለቁት የጨዋታ ዘመኖቹ የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ፣የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫና ሌሎች የመታሰቢያ ዋንጫዎችን ከክለቡ ጋር በማንሳት የራሳቸውን ታሪክ በደማቁ አፅፈው ኢትዮጵያ ቡናን ከፍ አድርገው ካለፉ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው በተለያዩ መከራዎችና ፈተናዎች እየተፈተነ ያለውን የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ባለውለተኛ ተጨዋች ተሾመ ተፈራ (ተሼ ብርቱ)ን አይንህ ላይ ምን ገጠመህ?በማለት የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ህመሙን ተጋርቶ ሊያጋራን በስልክ አነጋግሮታል፡፡
ሀትሪክ፡- …ተሼ ሆስፒታል መግባትህን ሰምቼ ነበር ምን ገጠመህ…?
ተሾመ፡- …አይኔን የሆነ ጥሩ ስሜት አልተሰማኝም ነበር፤ በኋላ ለምን አልታየውም አልኩ፤ ስታየው ህመሙ ትንሽ የከበደ ነገር ስለነበር ቀዶ ጥገና (ኦፕሬሽን) መደረግ አለብህ አሉኝ…ከሐኪሞች ትዕዛዝ ውጪ መሆን ስለሌለብኝ እሺ አልኩኝ፤አለርት ሆስፒታል ተኝቼ የግራ አይኔን በተሳካ ሁኔታ የቀዶ ጥገና (ኦፕሬሽን) አድርጌ ወጥቻለሁ፡፡ በ28 ደግሞ ሌላ ቼክ አፕ (ድጋሚ ምርመራ) አለኝ ለዛ ቀጠሮ ይዣለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ቀዶ ጥገና (ኦፕሬሽን) ካደረክ በኋላ ያለው ስሜት…?…የጤንነትህ ሁኔታስ…?
ተሾመ፡-…አሁን ያለው ስሜት ትንሽ ጠንከር ያለ ነው…በየ 4 ሰዓት የምወስደው ፈሳሽ መድሃኒት አለ ባክቴሪያ የሚገድል ነው…የእሱን ስቃይ ትንሽ አልቻልኩም፤ ሚጥሚጣ ታውቃለህ?…ልክ ሚጥሚጣ አይንህ ውስጥ ገብቶ እንደሚያቃጥልህ ልክ እንደዛ ነው የሚለበልበኝ፤ብቻ ተመስገን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ህክምና ካደረክ በኋላ ለውጥ አይተሃል…?…ኦፕራሲዮን የተደረገው አይንህስ የማየት ሁኔታው…?
ተሾመ፡-አሁን ገና ኦፕራሲዮን ከተደረኩ ሳምንት አካባቢ ነው…ብዙም ለውጥ የለም፤ አይኔ ውስጥ ሌንስ ስለገባ ብርሃን አላይም፤ማየቱን ተወውና ጎንበስ ብዬ እንኳን ጫማ ከመሬት ማንሣት አልችልም፡፡ ስተኛ እራሱ በስቃይ ነው፤ኦፕራሲዮን ባልተደረገው አይኔ በኩል ወይም በጀርባዬ ነው ተኝቼ የማድረው፤እንደ ድሮው እንደፈለኩ ተገላብጬ መተኛት እንኳን አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም አይኔ ውስጥ የተተከለው ሌንስ በእንቅስቃሴ መነቃነቅ የለበትም፤ከተነቃነቀ ደግሞ ሌላ ችግር ስለሚያመጣ በጣም ተጠንቅቄ ነው የምተኛው፤ እንዳልኩህ ጎንበስ ብዬ ጫማ እንኳን አላነሳም፡፡
ሀትሪክ፡- …ተሼ አንተ የኢትዮጵያ ቡና ብቻ ሣይሆን የሀገር ባለውለተኛ ተጨዋች ነህ…መታመምህና አይንህን ኦፕሬሽን መደረግህ ከተሰማ በኋላ መተው የጠየቁህ… አለንልህ…ብለው አጋርነታቸውን ያሳዩህ አሉ…?
ተሾመ፡- …እውነቱን ልንገርህ በአሁን ሰዓት ማንም የደረሰልኝም፤የጠየቀኝም የለም፡፡ ከህመሙ ባልተናነሰ የተሰማኝም ይሄ ነው፤በዚህ አጋጣሚ ግን ማመስገን የምፈልገው ሰው አለ፤የቀድሞ የተጨዋቾችና የደጋፊዎች የመረዳጃ ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነው ሸዋረጋ ደስታን፤ሸዋረጋ መታመሜን እንደሰማ ወዲያውኑ ሆስፒታል ድረስ መጥቶ ነው የጠየቀኝ…አይዞህ ብሎ ያበረታታኝ ሸዋ ነው፡፡ በፊትም በታመምኩ…ስራ በፈታሁ ጊዜም ሥራ ያስያዘኝ…ደጋግሞ የሚጠይቀኝ…አይዞህ እያለ የሚደግፈኝ ሰው በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ ሸዋን ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተም ቤተሰብህም ቋሚ የገቢ ምንጭ የላችሁምና ከዚህ አንፃር የህክምናህን ወጪ የምትሸፍነው በምድነው…?…
ተሾመ፡- …እንዳልከው ነው ምንም የገቢ ምንጭ የለኝም…እንኳን ለህክምና የማወጣው ለሚላስ ለሚቀመስ የሚሆን ገንዘብ የለኝም፤ግን እንደ ወርቁ ሺረጋ አይነት ለሰው ልጅ አዛኝ…የሰው ልጅ ህመምና ማጣት የሚሰማቸው ሰዎች፣አንዳንድ ጓደኞቼና በቅርቡ ደግሞ ዩ ቲዩብ ላይ የእኔ ቃለ-ምልልስ ከተለቀቀ በኋላ ያንን የተመለከቱ አሜሪካን ሀገር የሚኖሩ የቀድሞ ተጨዋቾች ከላኩልኝና ከቀለብ ከተረፈች ትንሽ ገንዘብ ነው የአይኔን ብርሃን ለመታደግ እየተፍጨረጨርኩ ያለሁት፤እሷም እንዳልኩህ ዘጠኝ ቦታ ስለተበጣጠሰች ብዙ ርቀት አትወስደኝም፡፡
ሀትሪክ፡- እንደዚህ ከሆነ ታዲያ…አሁን ገና ህክምናህን አልጨረስክም…ከዚህ አንፃር ቀጣይ ህክምናህን በምን ልታደርግ ነው…?…ከስፖርት ቤተሰቡስ ምን ትጠብቃለህ…
ተሾመ፡- …እውነት ነው ገና ህክምናዬን አልጨረስኩም…ሀኪሞቹ ለድጋሚ ቼክ አፕ ለታህሳስ 28 ቀጥረውኛል፤መቅጠር ብቻ ሣይሆን ህክምናዬን በአግባቡ ካልተከታተልኩ የአንድ አይኔን ብርሃን እንደማጣና ማየት የማልችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንሚችል አስረግጠው ነግረውኛል፡፡ ትልቁ ስጋቴና ጭንቀቴ በየትኛው ገንዘብ ነው የምታከመው? በየትኛው ገንዘቤ ህክምናዬን ተከታትዬ አይኔን ከመጥፋት የማድነው? የሚለው ነው፤ይሄን ባሰብኩ ቁጥር መልስ አጣለሁ፡፡ ከዚህ በፊት የረዳኝም አሁን ይሄንን ዜና የሚያነቡትም…የሚሰሙትም…ህክምናዬን እንድከታተልና የአይን ብርሃኔን ከማጣት እንዲታደጉኝ በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፤አንተም ህመሜ ተሰምቶህ ለህዝብ ለማጋራት ደውለህ ስላናገርከኝ ከልብ አመሰግናለሁ፤እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡