በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት የተቋረጠው የወልዋሎ አዲግራት እና መቐለ ከተማ የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንዲደረግ ተወሰነ።
በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ 17 ሳምንት የትግራይ ደርቢ ጨዋታ በወልዋሎ አዲግራት 1-0 መሪነት እየተመራ ወደ መልበሻ ክፍል ያመራው ጨዋታ በእረፍት ሰዓት ላይ በሁለቱ የክለብ ደጋፊዎች በተነሳ ረብሻ ለመቋረጥ መገደዱ እሚታወስ ነው። በማግስቱ አርብ 4:30 ጨዋታው ከተቋረጠበት እንደሚቀጥል ተገልፆ የነበረ ፣ ሲሆን ጨዋታው በደጋፊ ታጅቦ ይካሄዳል ፣ አይካሄድም በሚል ምክንያት የሁለቱ ክለብ ሀላፊዎች ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ሳይካሄድ ቀርቷል።
በቀጣይ ቡድኖቹ ቀሪውን 45 ደቂቃ እንዲጫወቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሁለቱም ቡድኖች በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታቸው እንዲያካሂዱ የአዲስአበባ ስታዲየምና የአክሱም ስታዲዮም በምርጫነት ማቅረቡ ታውቋል። የተቋረጠው ጨዋታ መቼ እንደሚካሄድ ቀን አልተቆረጠለትም ።