የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተመዝጋቢዎች የመለያ ቁጥር
ካለጠፉ ወደ መሮጫ ቦታ እንደማይገቡ የውድድሩ መስራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ
ገብረስላሴ ገለፀ።
በተሳታፊዎች ብዛትና በድምቀቱ በዓለም ላይ ከሚደረጉ ታላላቅ የጉዳና ላይ ሩጫዎች
አንዱ የሆነውና በአፍሪካ በቀዳሚነቱ የሚጠቀሰው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የፊታችን
እሁድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በዓመቱ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ የሚካሄደው ይህ ሩጫ በዚህ ዓመትም
”100 ሚሊዮን ምክንያቶች ለሴት ልጆች በጋራ ለመሥራት” በሚል መሪ ሐሳብ
የሚካሄድ ይሆናል።
ለ17ኛው ጊዜ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መነሻውን በአዲስ አበባ መስቀል
አደባባይ አድረጎ በሜክስኮ አድርጎ በደጃዝማች በየነ መንገድ ዞሮ በአጎና ሲኒማና
በግሎባል ሆቴል አድርጎ መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደርጋል።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በዚህ ሩጫ ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሯጮች የመሮጫ
ቲ-ሸርታቸውን ሲወሰዱ አብሮ የሚሰጣቸውን የመለያ ቁጥር መለጠፍ እንዳለባቸው
አስገንዝበዋል።
የመለያ ቁጥር ያለጠፈ ሰው ወደ ሩጫ ቦታው እንደማይገባ የተናገረው ሻለቃ ኃይሌ፤
ይህም በህገ ወጥ መልኩ የመሮጫ ቲ -ሸርት አሳትመው በሩጫው ለመሳተፍ የሚመጡ
ሰዎችን ለመቆጣጠር እንደሆነ ገልጿል።
በዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተለየ መልኩ የሙዚቃ ኮንሰርት
የተዘጋጀ ሲሆን፤ በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ይሰጥ የነበረውን የገንዘብ ሽልማት
በእጥፍ በማሳደግ ወደ አንድ መቶ ሺህ ብር ከፍ ተደርጓል።
ታላቁ ሩጫ በአገሪቱ የሚገኙ አትሌቶች ልምድ እንዲገኙ እድል ከመፍጠሩም በላይ
የማህበረሰቡን የስፖርት ባህል በማሳደግ ጤናን በመጠበቅ በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው።
የህብረተሰቡን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ረገድም ቀላል የማይባል ፋይዳ አለው።
ውድድሩ የበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን እያገኘ በመሆኑ ለአገር ገጽታ
ግንባታ ትልቅ አስተጽኦ እያበረከተም ይገኛል።
ለ17ኛ ጊዜ በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውጭ አገር የመጡትን ጨምሮ 44
ሺህ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 7 ሺህ የሚሆኑት 10 ኪሎ ሜትሩን
ከአንድ ሰዓት በታች ለመግባት የሚሮጡ ናቸው።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዋና ስፖንሰርነትና በአጋርነት የሚሰራው ቶታል መሆኑን ተከትሎ
‘ ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ’ በሚል መጠሪያ የሚደረግ ይሆናል።