በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ክለቦች የ2011 ዓ.ም የውድድር አፈፃፀም ውይይትና የ2012 ዓ.ም ውድድር እጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በ 18/03/2012 ዓ.ም በራስ ሆቴል ተካሂዷል፡፡
በዚህ ኘሮግራም ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚያ እንዲሰጠው በአፀንኦት ተናግረዋል፡፡
ስፖርት በተለይም እግር ኳስ የአለማችን ትልቁ የደስታ ምንጭ ነው፡፡ ህብረተሰብን በማስተሳሰር በአንድነትና በወንድማማችነት የሚያቅፍ ትልቅ ምሰሶ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ የሚወደድና የሚከበር እግር ኳስ በሃገራችን በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት ከማቀራረብ ይልቅ እያራረቀ ከመወደድ ይልቅ የስጋት ምንጭ እየሆነ ክብሩም እየቀነሰ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የኢትዩጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዚህ አመት ለስፖርታዊ ጨዋነት ከፍ ያለ ትኩረት ይሰጣል፡፡
ክለቦችም ይህንን በመገንዘብ ከውጤት ባልተናነሰ ለስፖርታዊ ጨዋነት ትኩረት ልትሰጡ ይገባል፡፡
በእናንተ ጨዋታ ህብረተበቡ መደሰት እንጂ ማዘን የለበትም የስፖርታዊ ጨዋነትን ጉዳይ ከፍ ያለ ትኩረትና ቦታ እንድትሰጡት በፌዴሬሽኑ ስም አደራ ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ 1ኛ ሊግ ተሳታፊ ክለቦች በተገኙበት የ 2011 ዓ.ም የውድድር ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ተህሳስ 5/2012 ዓ.ም የሚጀመረው የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ክለቦች የውድድር መርሃ ግብር በስድስት ምድብ በመከፈል እጣ የማውጣት ስነስርዓት ተኳሂዷል፡፡
via – EFF