-በዘጠነኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የሊጉ መሪዎች ደደቢት እና አዳማ ከነማ ከሜዳቸው ውጭ ሻምፒዮኖቹ በጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ከዚህ ሳምንት አገልግሎትየማያገኙ ይሆናል፡፡
የ 9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 26/2009 ዓ. ም እስከ ፊታችን አርብ ታህሳስ 28/2009 ዓ . ም ድረስ በአዲስ አበባ እና ሌሎች የክልል ስታዲየሞች ቀጥለው ይከናወናሉ፡፡
ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ 10ኛ ላይ የሚገኘው እና ባሳለፍነው ሳምንት በሊጉ መሪ ደደቢት 2 ለ 1 የተሸነፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘውን እና ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በተደጋጋሚ ጨዋታወች እየተመራ አሸንፎ በመውጣት በ 14 ነጥቦች በሊጉ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን መከላከያ ን የሚያስተናግድብት እንዲሁም 11 ፡30 ላይ ደግሞ ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀሉት አዲስ አበባ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ የሚያከናውኗቸው ሁለቱም ጨዋታወች በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጠበቃሉ፡፡
ፕሪሚየር ሊጉ በነገው እለትም ቀጥሎ ሲከናወን ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው እሁድ በምንጊዜም ተቀናቃኙ ኢትዮጵያ ቡና ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም እና ከሻምፒዮንነት ፉክክሩ ላለመራቅ ያለ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ሮበርት ኦዶንካራ ፣ በሀይሉ አሰፋ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ምንያህል ተሾመ እና አሉላ ግርማ በተከታታይ ነጥብ እየጣለ የሚገኘው የዘላለም ሽፈራው ቡድን ድሬዳዋ ከነማን 11፡ 30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ 9 ፡00 ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ 15 ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው እና እስካሁን በሊጉ አንድም ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከደደቢት ጋር በእኩል 17 ነጥቦች በሁለት የጎል ክፍያ ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን አዳማ ከነማን ያስተናግዳል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉ በዚሁ እለት ሌሎች ሶስት ጨዋታዎችን በክልል ስታዲየሞች የሚያከናውን ሲሆን ሀዋሳ ላይ በሊጉ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከነማ ወላይታ ድቻን ፣ ጅማ ላይ ጅማ አባቡና ሲዳማ ቡናን እንዲሁም አርባ ምንጭ ላይ በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ አርባ ምንጭ ከነማ ደደቢትን የሚያስተናግዱ ይሆናል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ሁለት በሊጉ በምርጥ ወቅታዊ አቋም እና ግስጋሴ እንዲሁም በደረጃው አናት ላይ የሚገኙ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ ሲሆን አርባ ምንጭ ከነማ ባሳለፍነው ቅዳሜ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከነማን 1 ለ0 ፣ ደደቢት በበኩሉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በምርጥ አቋም ላይ በሚገኘው እና የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በ 8 ጎሎች እየመራ በሚገኘው ውጤታማ አጥቂው ጌታነህ ከበደ ሁለት ጎሎች አማካኝነት 2 ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸው ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል፡፡
አርባ ምንጭ ከነማ በሊጉ ደካማ የሚባል አጀማመር ቢያሳይም ያለፉት ሳምንታት ተከታታይ ድሎቹ በሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2 ነጥቦች ብቻ አንሶ በ 12 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧ፡፡ ተጋጣሚው ደደቢት በበኩሉ በ17 ነጥቦች እና 7 ተጨማሪ ጎሎች የሊጉ አናት ላይ ይገኛል፤ ነገር ግን ክለቡ እስካሁን ካስቆጠራቸው 10 ጎሎች 8ቱን ጌታነህ ከበደ ብቻውን ማስቆጠሩ በተጫዋቹ ያለው ጥገኝነት የሚያመላክት ሲሆን ተጫዋቹ በሆነ ምክንያት ከሜዳ ቢርቅ ክለቡ ውጤታማ ለመሆን ሊቸገር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ የዚህኛው ሳምንት የመጨረሻ መርሀ ግብር አርብ በ 9፡ 00 ሰአት ወልዲያ ላይ ወልዲያ ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ሲሆን ፤ ኢትዮጵያ ቡና ካለፈው የሸገር ደርቢ ጣፋጭ ድል በኋላ በአሸናፊነቱ ለመቀጠል አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙትን አምበሉን መስኡድ መሀመድ እና አብዱልከሪም መሀመድን ሳያካትት በሊጉ አንድ ጎል ብቻ ያስቆጠረውን እና ለመጨረሻ ጊዜ በመልካ ቆሌ ሜዳ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የሚያደርገውን ወልዲያ ከነማ የሚፋለም ይሆናል፡፡