የደደቢት እግር ኳስ ክለብ
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መቀመጫውን ወደ ትግራይ ክልል
ለማዞር መወሰኑን አስታወቀ።
ክለቡ ውክልናው አሁንም ለአዲስ አበባ እንደሆነና በትግራይ
ክልል ጨዋታ የሚያደርግበትን ስታዲየም በጥቂት ቀናት
እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
የፋይናንስና የበጀት ጫና ከፍተኛ ተጽእኖ በክለቡ እያሳደረ
በመሆኑ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ
መቀመጫውን በትግራይ ክልል አድርጎ እንዲጫወት ለመወሰን
እንዳስገደደው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ደሃ ሆና ሳለ በመንግስት በኩል ለእግር ኳስ
የሚመደበው በጀትና ለተጫዋቾች የሚከፈለው የክፍያ መጠን
የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን ገልጿል።
በክለቦች የፋይናንስ እንቅስቃሴን የሚቆጣጠር ስርዓት
በኢትዮጵያ እንደሌለና አሁን ያለው የክፍያ መጠን መቋቋም
የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል።
የሌሎች አገራት ክለቦች የራሳቸውን ወጪ ከመሸፈን አልፈው
የተለያዩ ማህበራዊና ልማታዊ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ አብዛኛው
የኢትዮጵያ ክለቦች በመንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱና
በጀታቸውም ሲያልቅ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ከሚመደበው
ገንዘብ እየተቆረጠ እንደሚጠቀሙ አስታውቋል።
ይህ መሆኑ ክለቦች ለአገር ጠቃሚ ሳይሆን ሸክም እንዲሆኑ
የሚያደርግ እንደሆነ ገልጾ፤ ይህ ችግር የሚመነጨው ዘመናዊ
የእግር ኳስ አሰራርና አደረጃጀት አለመኖሩ እንደሆነ ነው
የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የገለጸው።
ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት ክለቡ
ህልውናውን ለማስቀጠልና የረጅም ጊዜ ራዕዩን ለማሳካት
ከ2011 ዓ.ም የውድድር ዓመት ጀምሮ አሁን ካለው የክፍያ
ስርአትና ፉክክር በመውጣት አቅም ባገናዘበና በአነስተኛ ወጪ
ለመወዳደር መወሰኑን ጠቁሟል።
ክለቡ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የሚያገኘውን ገንዘብ ዘላቂ
የገቢ ማመንጫ ስራ ለማወል ማቀዱ በመግለጫው
ተመልክቷል።
በአገሪቷ እግር ኳስ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ያለው ከቁጥጥር
ውጭ የሆነ የክፍያ ስርዓት አዋጪ አለመሆኑን በመገንዘብ ክለቡ
ከተገነዘበበት ጊዜ ጀምሮ የበጀት ጫናውን ለመቀነስና
ከነበረበት ችግር ለመውጣት ላለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ
እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
የደደቢት እግር ኳስ ክለብ መቀመጫውን ትግራይ ሊያደርግ ነው
Hatricksport team