ወልዲያ ከተማ በሜዳው የሊጉን መሪ ደደቢት በማሸነፍ ከወራጂ ቀጠና ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የተጠጋበትን ወሳኝ 3 ነጥብ ሲያስመዘግብ ተጋጣሚው ደደቢት ከመሪዎቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 7 የሚያሰፋበትን ዕድል አባክኗል፡፡በኘሪሚዬር ሊጉ 14ኛ ሳምንት ሳይደረግ በይደር ተይዞ የቆየው የወልዲያ ከተማና ደደቢት ጨዋታ ዛሬ በወልዲያ ሼህ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲዬም ተደርጎ በባለሜዳዎቹ የ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ወልዲያ ከተማ 1ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከወላይታ ዲቻ ጋር እያለው የሊጉን 14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያውን ዙር የሜዳውን የመጨረሻ ጨዋታ ሲያከናውን፡እንግዳው ደደቢት በተቃራኒው የሊጉን 15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከባለሜዳዎቹ ወልዲያ ከተማዎች ጋር በማድረግ አጠናቋል፡፡
ልክ 9:10 ሲል በተጀመረው የወልዲያ ከተማና ደደቢት ጨዋታ ፡ባለሜዳዎቹ ወልዲያ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት በሜዳቸው መከላከያን 2ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታ የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች የ1 ተጨዋች ለውጥ በማድረግ፡መከላከያን ባሸነፉበት ጨዋታ 2ኛውን ጎል ያስቆጠረው ብርሃኔ አንለይን በነጋ በላይ በመቀየር ወደ ሜዳ ሲገቡ፡እንግዳው ደደቢት ከቅ/ጊዬርጊስ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲዬም ያለ ግብ ነጥብ በተጋሩበት የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች የሶስት ተጨዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብ ጠባቂውን አማረህ ክሌመንትን በታሪክ ጌትነት ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ ፡ተከላካዩን ከድር ኩሊባሊ ፡በኦንዶህ ኩዊኩ፡አማካኙን አስራት መገርሳ በፋሲካ አስፋው በመቀየር በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተዋል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ እንግዳው ደደቢት ኳስን መስርተው በመጫዎት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ፡የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ውሰደው በመጫዎት የግብ ዕድል በመፍጠር በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የተሻሉ ቢሆኑም ያገኟቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማቸው በተለይም አቤል ያለውና ፡ኤፍሬም አሻሞ ያመከኗቸው የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።
- ማሰታውቂያ -
ባለሜዳዎቹ ወልዲያዎች ወደ ሇላ አፈግፍገው ሙሉ በሙሉ መከላከልን መሰረት አድርገው ቢጫዎቱም ለ20 ደቂቃ ያህል ቡድኑ ከተወሰደበት የኳስ ብልጫ አንፃር መረጋጋት ተስኗቸው ሲጫዎቱ በተደጋጋሚ ጥፋት ሲሰሩ ተስተውሏል።
ባለሜዳዎቹ ወልዲያዎች አልፎ አልፎ በካውንተር ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶ በመስመር በኩል አንዷለም ንጉሴ (አቤጋ) በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ሳይጠበቅ ምንያህል ተሾመ በግንባሩ በመግጨት በ21’ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጠረ፡፡
ከጎሏ መቆጠር በሇላ ወልዲያ ከተማ ወደ ጨዋታ የተመለሱበት ፡ደደቢት በተጋጣሚው የጨዋታ የበላይነት የተወሰደበት ፡የተሻለ ፍክክር የተመለከትንበት፡በ41ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ከወልዲያው ግብ ጠባቂ ኢሚሪክል ቢሊንጌ ፊት ለፊት ተገናኝቶ ኳሷን ያመከነበት ምናልባትም የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በእኩል ውጤት የሚጠናቀቅበትን ዕድል ደደቢት ሳይጠቀሙበት የመጀመሪያው አጋማሺ በባለሜዳዎቹ 1ለ0 መሪነት ተጠናቀቀ፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያዎች ነጥባቸውን አስጠብቀው ይወጣሉ ፡ወይስ ደደቢት ጎል አስቆጥሮ ነጥብ ይጋራል አልያም ተጨማሪ ጎሎችን አስቆጥሮ ያሸንፋል ፡የሚሉት የሚጠበቅ ቢሆንም በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የነበረበት፡ወልዲያዎች ሙሉ ለሙሉ ተከላክለው ውጤቱን ለማስጠበቅ
የተጫዎቱበት፡የደደቢት የአማካኝ ስፍራ ሳስቶ የታየበት ፡የወልዲያ ተጨዋቾች የበለጠ በላቀ ፍላጎትና ተነሳሺነት የተጫዎቱበት ፡ጨዋታው በተደጋጋሚ የተቆራረጠበት ፡ግብ፡ያልተስተናገደበት አጋማሺ ሲጠናቀቅ፡ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በምንያህል ተሾመ/ቤቢ/ አማካኝነት በ22ኛው ደቂቃ ባስቆጠሩት ጎል ከወራጂ ቀጠና ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የተጠጉበትን ፡ውጤት አስመዝግበው ጨዋታው ተጠናቋል፡፡
ወልዲያ ከተማ ካደረጋቸው 14 የሊግ ጨዋታ በሜዳው ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች 4 አሸንፎ፡በ3አቻ ሲለያይ፡በ1ተሸንፎ 8 ጎል ሲያስቆጥር 2 ጎል ተቆጥሮበት ፡ከሜዳው ውጭ ካደረጋቸው 6 ጨዋታዎች በ3 ጨዋታ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በ3ጨዋታ ተሸንፎ ፡8ጎል ሲያስተናግድ 2 ጎል አስቆጥሮ በአጠቃላይ ወልዲያ ከተማ 10 ጎል ሲቆጠርበት ፡10 ጎል አስቆጥሮ በ18 ነጥብና ያለ ምንም ጎል 1 ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ ከዲቻ ጋር እያላቸው በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለት ደረጃዎችን አሻሽለው ወደ 10ኛ ከፍ ብለዋል፡፡
የሊጉን የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በሽንፈት ያጠናቀቀው የሊጉ መሪ ደደቢት ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 8 ጨዋታ በሜዳው ሲያደርግ 6 ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ሲጫዎት በሜዳቸው ካደረጓቸው 8 ጨዋታዎች 5ቱን በማሸነፍ 2አቻ ሲለያዩ በ1 ጨዋታ ተሸንፈው፡17 ጎል ሲያስቆጥሩ 6ጎል ተቆጥሮባቸው፡ከሜዳቸው ውጭ ካደረጓቸው 7 ጨዋታዎች 3አሸንፈው 3አቻ ሲለያዩ በ1 ጨዋታ ተሸንፈው 7ጎል ሲያስቆጥሩ 3 ጎል ተቆጥሮባቸው በአጠቃላይ በ14 ጨዋታ፡24 ጎል ሲያስቆጥሩ 9 ጎል ተቆጥሮባቸው በ29 ነጥብና በንፁህ 15 ጎል ከተከታዬቹ ጅማ አባቡና እና መቆለ ከተማ ያለውን በ4 ነጥብ በልጠው የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞የወልድያ ከተማ ~ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ
“በጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር አድርገናል፡፡በአመዛኙ ተሽለን በነበርንበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጎል አስቆጥረን ሶስት ነጥብ አስመዝግበናል፡፡ማሸነፋችን ለቀጣዩ ጨዋታ መነሳሳትን ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡”
☞የደደቢቱ ም/አሰልጣኝ ~ጌቱ ተሾመ
“በጨዋታው እኛ የተሻልን ነበርን ፡የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች በቅጣትና በጉዳት ባይኖሩም ጥሩ ተጫውተን ተሸንፈናል፡፡ሜዳ ላይ ሰዓት ለማባከን የነበረው ነገር ቅር አሰኝቶኛል ሲል ገልጿል፡፡”