በ2018 የቶታል የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ 1ኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያው ቅ/ጊዮርጊስን ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ ዛሬ አ/አ ስታዲየም ላይ የሚደረግ ይሆናል።
ቅ/ጊዮርጊስ ለዚህ ውድድር የበቃው የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በማሸነፍ እና በቅደመ ማጣሪያው ደግሞ የደቡብ ሱዳኑን ቡድን አልሰላም ዋኡን በፎርፌ በማሸነፍ ሲሆን ኬሲሲኤም የዩጋንዳን ሊግ በማሸነፍ ለዚህ ውድድር መቅረብ ሲችል በቅድመ ማጣሪያው ደግሞ የማዳጋስካሩን ክለብ ሲናፕስ ስፖርት በድምር ውጤት 2-2 ቢያጠናቅቁም ከሜዳ ውጪ ብዙ ግብ ባገባ በሚለው ህግ በማሸነፍ ለዚህ ጨዋታ መድረስ ችሏል። የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ አሸናፊ 16ቡድኖች ወደሚሳተፉበት የምድብ ድልድል ማለፍ የሚችል ይሆናል።
የሁለቱ ቡድኖች አጭር ታሪክ
ቅ/ጊዮርጊስ፦ ከተመሰረተ 82 አመታት ያስቆጠረ ሲሆን በእነዚህ 82 አመታት ያገኛቸው ክብሮች እና ዋንጫዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ እግርኳስ ክለቦች ሁሉ በስኬታማነቱ አቻ የማይገኝለት ክለብ ያደርገዋል። በአጠቃላይ ቅ/ጊዮርጊስ ከምስረታው ጀምሮ 60 ዋንጫዎችን ማግኘት የቻለ አንጋፋ ክለብ ነው።
- ማሰታውቂያ -
ኬሲሲኤ፦ የዩጋንዳው ቡድን በሀገሪቱ ዋና ከተማ ካምፓላ የሚገኝ ቡድን ነው። ይህ ቡድን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1963 በከተማዋ የኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት የፍሳሽ ካውንስል ሀላፊ በነበረው ሳሙኤል ዋማላ ምስረታውን ያደረገ ሲሆን በ55 አመት የክለቡ ታሪክ እንደ እድሜው ብዙ ስኬትን ያጣጣመ ክለብ ነው። ይህ ክለብ ከምስረታው 2አመታት በኋላ በካምፓላ እና አካባቢው የእግር ኳስ ሊግ መሳተፍ የጀመረ ሲሆን በመጀመሪያው የውድድር አመት 6ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ወደ 3ኛ ዲቪዚዮን ሊያድግ ችሏል። ከሁለት አመታት በኋላ በ1968 በአንደኛ ዲቪዚዮን መወዳደር የቻለ ሲሆን በ1971 ግን መልሶ ወደ 3ኛ ዲቪዚዮን ሊወርድ ችሏል። በ1974 ወደ ዩጋንዳ ዋናው ሊግ ማለትም የዩጋንዳ ብሔራዊ ሊግ በመሳተፍ በሊጉ 2ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል። በቀጣዩ አመት በ1977 ኬሲሲኤ የመጀመሪያ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች የአፍሪካ መድረክ ታሪክ
ቅ/ጊዮርጊስ፦ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ 9ጊዜ እንዲሁም በአፍሪካ ኮንፈደሬሽን ካፕ 1 ጊዜ የተሳተፈ ሲሆን አምና(2009 ዓ.ም) በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻዎቹ 8ቡድኖች ውስጥ የገባበት ትልቁ ውጤቱ ሆኖ ተመዝግቦለታል።
ኬሲሲኤ፦ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ 3ጊዜ፣ በአፍሪካ ኮንፈደሬሽን ካፕ 1 ጊዜ፣ በካፍ ካፕ 4ጊዜ እንዲሁም በካፍ የአሸናፊዎች ዋንጫ 7ጊዜ የተሳተፈ ሲሆን በ1997 በካፍ ካፕ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰበት እንዲሁም በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ በ2009 ሁለተኛ ዙር የተቀላቀለበት ትልቁ ውጤቱ ሆኖ ተመዝግቦለታል።
የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ በ2002 በካፍ ካፕ ተገናኝተው ቅ/ጊዮርጊስ በደርሶ መልስ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር መሻገር ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች የዘንድሮ የሀገር ውስጥ ሊግ ውጤት
ቅ/ጊዮርጊስ፦ በያዝነው የውድድር አመት ቅ/ጊዮርጊስ በሊጉ 15 ጨዋታዎች ያከናወነ ሲሆን በ5 አሸንፎ በ8ቱ አቻ ወጥቶ በ2ቱ ተሸንፎ ከሊጉ መሪ ደደቢት በ6 ነጥቦች ርቆ በ23 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ኬሲሲኤ፦ 12 ጊዜ የዩጋንዳ ሊግን ማሸነፍ የቻለው ኬሲሲኤ በዘንድሮው የውድድር አመት 16ክለቦች በሚሳተፉበት ሊግ እስካሁን 18 ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 10 ጨዋታዎችን በማሸነፍ 6ቱን አቻ ወጥቶ በ2 ተሸንፎ 36 ነጥቦችን ሰብስቦ ኤስሲ ቪላ እና ቫይፐርስ እግርኳስ ክለብን ተከትሎ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች ያለፉት 5ጨዋታዎች ውጤት
ቅ/ጊዮርጊስ፦ ቅ/ጊዮርጊስ ያለፉትን 5ጨዋታዎች በሙሉ በሊጉ ሲሆን ማድረግ የቻለው ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል አንዱንም ማሸነፍ አልቻለም። ከመከላከያ እና ከደደቢት ጋር በተመሳሳይ 0-0 እንዲሁም ከአዳማ ከተማ ጋር 1-1 አቻ ሲለያይ በወላይታ ድቻ 2-1 እንዲሁም በሀዋሳ ከተማ የ4-1 ሽንፈት ደርሶበታል።
ኬሲሲኤ፦ የዩጋንዳው ክለብ ካለፉት 5ጨዋታዎች 3ቱን በሊጉ ሲያከናውን ቀሪዎቹን 2ቱን ደግሞ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ማድረግ ችሏል። ኬሲሲኤ ካደረጋቸው 3የሊጉ ጨዋታዎች ሶአና እግርኳስ ክለብን እና ኤስሲ ቪላ በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ከማሳቩ ጋር ያለግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት መለያየት ችሏል። በቻምፒየንስ ሊጉ ቅድመ ማጣሪያ ደግሞ ከሜዳው ውጪ በማዳጋስካሩ ክለብ ሲናፕስ ስፖርት 2-1 ሲሸነፍ በመልሱ ጨዋታ ካምፓላ ላይ በኬሲሲኤ 1-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታ ረቡዕ የካቲት 26/2010 ዓ.ም 10:00 ሲል በአ/አ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ከ10 ቀናት በኋላ መጋቢት 7 ወይም መጋቢት 8/2010 ዓ.ም 12:00 ሲል ካምፓላ ላይ 10,000 ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው ሉጎጎ ስታዲየም ላይ የሚካሄድ ይሆናል።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኞች፦
ዋና ዳኛ፡ ጃን ክላውድ እሽምዌ(ሩዋንዳ)
ረዳት ዳኛ፡ ሬይሞንድ ኖናቲ ብዊሊዛ
ረዳት ዳኛ፡ ዚፋኒ ኒዮንኩሩ