የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ አጋማሽ የሚደረጉ ሲሆን ሰባት ጨዋታዎች ነገ (ረቡዕ) ሲደረጉ ቀሪ አንድ ጨዋታ ደግሞ ሀሙስ የሚደረግ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል በጉጉት የሚጠበቀውን እና ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉትን የሸገር ደርቢ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የጨዋታ ቀን: ረቡዕ ጥር 20/2012
የጨዋታ ሰዓት: 10:00
የጨዋታ አርቢትር: ኢንተርናሽናል አርቢትር ብሩክ የማነብርሃን
የጨዋታ ቦታ: አዲስ አበባ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ሳምንትም በ10ኛው ሳምንት ወደ ትግራይ ስታዲየም አቅንተው ከወልዋሎ አ.ዩ. ጋር አቻ የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሜዳቸው (የዚህ ዙር ባለሜዳ ኢትዮጵያ ቡና በመሆኑ) ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳሉ።
ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው የሊግ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጫወቱ ተጋጣሚያቸው ላይ ከፍተኛ የበላይነት የሚወስዱ ሲሆን ከሜዳቸው ይህንን የበላይነት ማስቀጠል ሲያቅታቸው ታይተዋል። የካሳዬ አራጌ ኢትዮጵያ ቡና በሜዳው የተጋጣሚ ቡድንን ተጭነው ኳስ ብልጫ በመውሰድ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል የአጥቂው የአቡበከር ነስሩ ጉዳት ላይ መሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ጋር ተደምሮ ጨዋታውን ለኢትዮጵያ ቡና ፈታኝ ያደርግበታል ተብሎ ይጠበቃል። ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስም በአዲስ አበባ ስታዲየም ምንም ጨዋታ ያልተሸነፉ ሲሆን ለዚህም የተከላካዮቹ እና የአማካዮቹ ሀይደር ሸረፋ እና ሙሉዓለም መስፍን ጥምረት እንደ ዋና ጥንካሬ ይታያል። ከዚህ ባሻገርም የአጥቂዎቹ አቤል ያለው፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ጌታነህ ከበደ ለኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለቱ ቡድኖች ከ1991 ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ 40 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፍ ረገድ ከፍተኛ ብልጫውን ይወስዳሉ። ከተገናኙባቸው 40 ጨዋታዎች 18ቱን ፈረሰኞቹ ድል ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ቡና በ6ቱ ብቻ ድል ቀንቷቸዋል። የተቀሩትን 16ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። በነዚህ 40ጨዋታዎች 73ግቦች (በአማካይ 1.82 ግቦች) የተቆጠሩ ሲሆን አሁንም ፈረሰኞቹ ብልጫ ሲኖራቸው በተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና ላይ 49ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃሩ በግማሽ አንሰው 24 ግቦችን ፈረሰኞቹ ላይ አስቆጥረዋል። በ2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች በ8ኛው እና በ23ኛው ሳምንት ተገናኝተው ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሰ ሁለቱንም ጨዋታዎች መርተው ሁለቱ ቡድኖች ያለግብ ጨዋታዎቻቸውን ፈፅመዋል። ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ላይ ሲሆን በጨዋታውም ቅዱስ ጊዮርጊስ በአቤል ያለው እና የአብስራ ተስፋዬ ግቦች 2-0 ማሸነፉ ይታወሳል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ቡና ካደረጋቸው 10ጨዋታዎች 4ቱን በሜዳቸው ያደረጉ ሲሆን ከነዚህ 4ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማን፣ ሀድያ ሆሳዕናን እና ሲዳማ ቡናን ሲያሸንፉ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ብቻ አቻ መለያየት ችለዋል። በነዚህ 4የሜዳቸው ጨዋታዎች 11 ግቦች ሲያስቆጥሩ 2ግቦችን ብቻ አስተናግደዋል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጓቸው 10ጨዋታዎች 3ቱን ሲያሸንፉ 4አቻ ተለያይተው በሶስቱ ሽንፈት በማስተናገድ በ13ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ካደረጓቸው 10ጨዋታዎች 5ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጪ ሲያደርጉ በአራቱ ጨዋታዎች ማለትም ከወልቂጤ ከተማ፣ ከሀድያ ሆሳዕና፣ ወላይታ ድቻ እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ ቀሪ 1ጨዋታቸውን በጅማ አባጅፋር ተሸንፈዋል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጓቸው 10ጨዋታዎች ደግሞ በ4ጨዋታዎች አሸንፈው በ5ጨዋታዎች አቻ ወጥተው በ1ጨዋታ ደግሞ ተሸንፈው 17 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ በ2ነጥቦች ብቻ አንሰው በሊጉ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
ነገ በሚካሄደው እና ኢንተርናሽናል አርቢትር ብሩክ የማነብርሃን በሚመሩት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና የሚያሸንፍ ከሆነ ደረጃውን አስከ 4ኛ ማሻሻል የሚችልበት እድል ይኖረዋል። በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል የሚቀናው ከሆነ የሌሎች ቡድኖችን ውጤት ጠብቆ የሊጉ መሪ እስከመሆን ያደርሰዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቡበከር ነስሩ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ለዓለም ብርሀኑ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሰልሀዲን ሰዒድ በነገው ጨዋታ የማይሳተፉ ይሆናል።