የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን ነገ (ቅዳሜ) በሚደረጉ 3 ጨዋታዎች ሲጀመር እሁድ ደግሞ ቀሪ አምስት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።በነገው እለት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ወላይታ ድቻ ከመቐለ 70 እንደርታ የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ወላይታ ድቻ ከ መቐለ 70 እንደርታ
የጨዋታ ቀን: ቅዳሜ ጥር 16/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: አንተርናሽናል አርቢትር ለሚ ንጉሴ
የጨዋታ ቦታ: ሶዶ ስታዲየም
ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ የሊጉ አናት ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ ወላይታ ተጉዘው ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ።ከገብረ ክርስቶስ ቢራራ ጋር ተለያይተው ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ ጅማ አባጅፋርን ያሸነፋት ወላይታዎች ከወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ በነገው ጨዋታ ከፍተኛ ፋክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
- ማሰታውቂያ -
ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር የተለያዩት ወላይታዎች በምክትል አሰልጣኝ አንደመመራታቸው ነገ ይዘው ሊገቡ የሚችሉትን አጨዋወት ለመገመት ከባድ ቢያደርገውም ጨዋታ ቁጥጥር ላይ መሰረት ያደረገ የመስመር አጨዋወትን ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል።በተለይ መስመር ላይ ፈጣን ተጨዋቾች ያልዋቸው ድቻዎች ከመስመር እየተነሱ ከባዬ ገዛሀኝ ጋር ሚኖራቸው ጥምረት ከሜዳው ውጪ ብዙ ግቦችን ሚያስተናግደውን የመቐለ 70 እንደርታን ተከላካይ ክፍልን ሊፈትን ይችላል።
በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች ከተከታዮቻቸው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማስጠበቅ ጥንቃቄ ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወትን ምርጫጨው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።የተጋጣሚ ክልል ላይ ለመድረስ ማይቸገሩት መቐለዎች አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ኦኪኪ ኦፎላቢ ላይ መሰረት ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም የግብ እድሎችን በመፍጠር ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ሊሞክሩ አንደሚችሉ ይገመታል።
ወላይታ ድቻዎች በሜዳቸው 5 ጨዋታዎችን አድርገው በአንዱ ሲያሸንፋ(ሲዳማ ቡናን በ1ኛው ሳምንት) በሁለቱ አቻ ወጥተው፣በቀሪዎቹ ሁለት ተሸንፈዋል።በአንጻሩ መቐለዎች ከሜዳቸው ውጪ 4 ጨዋታዎችን አድርገው በሁለቱ አሸንፈው በሁለቱ ተሸንፈዋል።
የጦና ንቦች በሜዳቸው ባደረጉዋቸው 4 ጨዋታዎች 3 ግቦችን አስቆጥረው 4 ግቦችን ሲያስተናግዱ ምዓም አናብስቶቹ በበኩላቸው በአራቱ የሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎች 6 ግቦችን አስቆጥረው በተመሳሳይ 6 ግቦችን አስተናግደዋል።