በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ
ግጥሚያውን ከመከላከያ ጋር ያደረገው
ኢትዮጵያ ቡና ቅዳሜ እለት ሳሙኤል ሳኑሚ
ባገባው የመጨረሻ ሰዓት ብቸኛ ጎል 1-0
ሊያሸንፍ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ የሶስተኛ ሳምንት
የጨዋታ መርሃ ግብር ግጥሚያውን ካደረገው
የመከላከያ ቡድን ጋር የነበረውን ጨዋታ
በድል ማጠናቀቁ ግጥሚያው የመጀመሪያው
የመክፈቻ ጨዋታው ከመሆኑ አኳያ
በቡድናቸው ላይ ለቀጣዩ ፍልሚያቸው
ከፍተኛ መበረታታትን እንደሚፈጥርላቸው
የቡድኑ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ኤፍሬም
ወንድወሰን አስተያየቱን የሰጠ ሲሆን የቡና
ቡድን በመከላከያው ጨዋታ እንደተጠበቀው
ከመጀመሪያው ግጥሚያ አንፃር ደጋፊው
የሚፈልገውን ውበት ያለው ጨዋታን
ማሳየት ላለመቻሉም ከጨዋታው ሶስት
ነጥብ ብቻ ይዞ ለመውጣት ትኩረትን
ማድረጉ ምክንያት እንደሆነውም ይናገራል፤
የቀጣዩ ጊዜ ላይ ግን የቡድኑ ደጋፊ
የሚወደውንና ጥሩ የሚባለውን እንደዚሁም
ደግሞ በማጥቃት ላይ ያተኮረም እንቅስቃሴን
በማሳየትም የእዚህ ዓመት ላይ የሊጉን
ዋንጫ ለማንሳትም እንደሚጫወቱም ያለውን
ሃሳብ ጨምሮ ሰጥቶናል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ከመከላከያ ጋር
በነበረው ጨዋታ በእንቅስቃሴ በጣሙን
ተፈትኖ የወጣበትን ጨዋታ ያደረገ ሲሆን
የመከላከያ ቡድን በጨዋታው ምንም እንኳን
ይሸነፍ እንጂ ብርቱና ጠንካራ ተፎካካሪ
መሆኑን ያሳየበትንም ግጥሚያ ለመመልከት
ችለናል፡፡
የመከላከያ ክለብ በተለይ የቡድኑ
አጥቂ ምንይህሉ ወንድሙ የግብ እድሎችን
በመፍጠርና ለመፍጠርም የሚያደርገው
ጥረት የተደነቀለት ሲሆን የኢትዮጰያ ቡና
ክለብ ተጨዋቾች ውስጥ ደግሞ የመከላከል
ክፍሉ ላይ ኤፍሬም ወንድወሰን የሚያሳየው
አበረታች ብቃት በብዙዎች ዘንድ አሁንም
አድናቆትን እያተረፈለት ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ መከላከያን 1-0
አሸንፎ የመክፈቻ ግጥሚያውን በድል ከተወጣ
በኋላ ስለነበረው ጨዋታ፣ ስለቡና አቋምና
ሌሎችንም ጥያቄዎች በማንሳት ከኤፍሬም
ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርገናል፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የመጀመሪያ ግጥሚያችሁን በድል ልትወጡ
ችላችኃል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?
በማሸነፋችሁስ ምን ስሜት ተሰማህ?
ኤፍሬም፡- የመከላከያ ክለብ ጋር የነበረን
የቅዳሜው እለት ጨዋታ ሁለታችንም አንዳችን
አንዳችንን ለማሸነፍ የተፎካከርንበት ስለነበር
እስከመጨረሻው ሰአት ድረስ የሚያስጨንቅ
ግጥሚያ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ይሄ ግጥሚያ
በተለይ ለእኛ ብዙ ጊዜ የሊጉን ውድድሮች
ስንጀምር በአቻ ውጤት የምናጠናቅቅበት
አልያም ደግሞ ነጥብ የምንጥልበትም አጋጣሚ
ስለነበር ያ የከዚህ ቀደሙ የውጤት ማጣት
ችግር ዳግም እንዳይገጥመን በማለት ወደ
ሜዳ ጨዋታውን ለማሸነፍ ብቻ የምናደርገው
ግጥሚያ ስለነበርና የሊጉን ዋንጫ ለማንሳትና
በጣም ጠንካራ ክለብን ለመፍጠር ደግሞ አሁን
ከሊጉ የጀማሬ ግጥሚያዎች አንስቶ ተከታታይ
ድሎችን ማግኘትም ስለሚያስፈልገን ያንንም
አዲሱ አሰልጣኛችንም በሚገባ ስላወቀና
ስለተጋጣሚዎቻችንም ከእኛ ጋር ሲጫወቱ
በምን መልኩ ወደ ሜዳ እንደሚመጡም
እያወቀና ከእኛም ጋር በመነጋገር መፍትሄ
ለማግኘት እየጣረም በመሆኑ ለጨዋታው
ወደ ሜዳ የምንገባው በከፍተኛ ትኩረትና
የአሸናፊነት ስሜት ላይም ሆነን ነበር፤
ያም ሆኖ ግን እንዲህ ያሉ ጨዋታዎቻችን
ላይ ማሸነፍን ስንፈልግ የመጨነቅ ነገር
ስለሚኖርም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው
ሊያምርም ይችል ይሆናልና እኛን ቅዳሜ እለት
የገጠመን ያ ነው ሆኖም ግን ጨዋታውን
በድል መጀመራችን ለእኛ በጣም ጥሩ የሚባል
ውጤት ነው፤ ድሉም በጣም አስደስቶናል፤
ከእዚያ ግጥሚያ ተንስተንም በቀጣይ ጊዜ
ሌሎች ተከታታይ ድሎችም ይኖሩናል፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና የድል
ጎሉን ያስቆጠረው በጣም ዘግይቶ ነው፤
እስከዚያው ድረስ በውስጣችሁ ጭንቀት
አልፈጠረባችሁም?
ኤፍሬም፡- የመከላከያን ክለብ በገጠምንበት
የቅዳሜው እለት ጨዋታችን ላይ ሁለታችንም
ጨዋታው ለእኛ የመጀመሪያችን ከመሆኑ
አኳያ ፈፅሞ ነጥብ መጣል የለብንም በሚል
ተነጋግረን ወደሜዳ መጥተን ስለነበር ጎልን
ለረጅም ደቂቃዎች ማስቆጠር ባልቻልንበት
ወቅት የእውነትም ራሳችንን በማሰብና
ደጋፊውንም በመመልከት ጭምር የእውነትም
የሚጨንቀን ነገር ነበር፤ ዘንድሮ ስኬታማ
ውጤት ለማምጣት ከመጀመሪያው ጨዋታ
አንስቶ ማሸነፍ አለብን በሚል ከፍተኛ
ሃላፊነትን ስለወሰድን የቅዳሜው ጨዋታም
ላይ እስከመጨረሻው ሰአታቶች ድረስ ፈፅሞ
ተስፋ ሳንቆርጥ በመጫወትም ነው የድሉን
ግብ አስቆጥረን ለማሸነፍ የቻልነውና፤ ምንም
እንኳን ጎል ለማስቆጠር እኛ ብንዘገይም
በመጨረሻ የምንፈልገውን ውጤት ልናገኝ
ችለናል፡፡
ሀትሪክ፡- መከላከያን የረታችሁበት የድል
ውጤት ለእናንተ ይገባችኋል?
ኤፍሬም፡- አዎን፤ በጨዋታው
እንደምንጠበቀው ኳሱን ተቆጣጥሮ መጫወቱ
ላይ ያን ዕለት ጥሩ ሆነን ባንቀርብም
ማሸነፋችን ግን በደንብ ይገባናል፤ በጨዋታው
እንቅስቃሴ እኮ የእኛ ቡድን ሌሎች የግብ
ሙከራዎችም ያደረገበት አጋጣሚ ነበር
ከእነዚያ ውስጥ ብረት የመለሰብን አጋጣሚም
አለ ሌላም ኳስ አግኝተን ወደ ግብም
ሞክረናልና ማሸነፋችን ዘግይቶም ቢሆን
ውጤቱ የሚገባን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
ሀትሪክ፡- የመከላከያ ክለብን በጨዋ
ታው እንቅስቃሴ እንዴት ተመለከትካቸው?
ኤፍሬም፡- የመከላከያ ክለብ ያን
እለት ጥሩ ነበሩ፤ ብዙ ጊዜ ደግሞ ከእኛ
ጋር የሚጫወቱ ክለቦች ለቡድናችን
በጣም ተዘጋጅተው የሚመጡና
አጨዋወታችንንም ለማበላሸትም ወደ
ሜዳ የሚመጡ ስለሆነም ያንን ብዙ ገዜ
እናውቀዋለን የመከላከያ ክለብንም እኛን
ያን እለት በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ
ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወትም ሆነ የእኛን
ቡድን በኳስ ተደራጅቶ እንዳይጫወትና
እንዳይወጣም በማድረግ ያሳየው
እንቅስቃሴም ነበርና ሊፈትነን ችሏል፡
፡ መከላከያ ያን እለት መከላከሉም ላይ
ጥሩ ነበሩ፤ በእዚህ እንቅስቃሴ እኛ ጎል
እንዳናገባና ጭንቀት ውስጥም ከተውን ነበር
በኋላ ላይ ግን የእኛ ቡድን የመጨረሻው
ሰአታት ላይ መጠነኛ ለውጥን በማምጣት
ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን በድል ሊወጣው
በቅቷል፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሰርቢያዊው
አዲስ አሰልጣኝ ፓፒች እየተመራ ይገኛል፤
የእሱን ልምምድ እንዴት አገኘኸው?
ኤፍሬም፡- ኢትዮጵያ ቡና ያስመጣው
አዲሱ አሰልጣኝ እየሰጠን ያለው ልምምድ
ለእኛ በጣም የተመቸን ነው፤ ክለቡ ኳስ
ይዞና በፍጥነትም የተቃራኒ ቡድን ሜዳ
ላይ ገብቶም በመጫወት በውጤትም
በውበትም ጥሩ የሆነ ቡድንን ለመስራት
ስለሚፈልግ እዚያ ላይ ትኩረትን ሰጥቶ
እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ሰርቢያዊው
አሰልጣኝ እስካሁን እየሰራ ያለው ልምምድ
ላይ ከሚመለከተው እንቅስቃሴ በመነሳት
ነው እዚያ የልምምድ ቦታው ላይ
የተመለከታቸውን ልጆች ነው በማጫወት
ላይ የሚገኘው ብዙዎቹን ተጨዋቾችም
እያሰለፈ እየተጠቀመባቸውም ይገኛልና
እሱ ላይ የምናየው ነገር የሚያበረታታ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ
የአጥቂ ስፍራው ላይ ክፍተት አለበት
እየተባለ ነው በእዚህ ላይ ምን ማለት
ይቻላል?
ኤፍሬም፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ
የአሁን ሰአት ላይ በሰርቢያዊው አሰልጠኝ
ፓፒች በመመራት እየሰራ ካለው ታክተክ
አኳያ ብዙዎቹ ቡድኑ በአጥቂ ስፍራ
ላይ ክፍተት አለበት፤ ዘንድሮ በእዚህ
እንዴት ነው የምንዘልቀው የሚል
አስተያየቶችን እያዳመጥን ቢሆንም
የክለባችን ተጨዋቾች የአዲሱን አሰልጣኝ
አጨዋወት አሁን ሙሉ ለሙሉ
ሲላመዱት ያንን ችግር ብዙ እንደማናነሳ
እርግጠኛ ነው የሆንኩት፡፡ ኢትዮጵያ
ቡናን አሁን ብዙዎች ተደጋጋሚ ጎሎችን
አለማስቆጠሩን ነው ያዩት የእኛ ቡድን
ግን በአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ብቻ ጥገኛ
ያልሆነና ሁሉም ተጨዋች እንደቡድን
በመንቀሳቀስ ጎልን የሚያስቆጥርም
ስለሆነ እዚያ ቦታ ላይ ያለው ክፍተት
በሌሎች ልጆች በጣም እንደሚስተካከል
እርግጠኛ ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ
ውስጥ ከአጥቂ ክፍሉ ውጪ የሊጉ
የአማካይ ስፍራ አጠቃላይ ተጨዋቾችም
እንደ ቡድን በመጫወት ጎል የሚያገቡም
ናቸው በእዚያ ላይ እነ አስቻለው ግርማ
ከጉዳት ድነው ሲመጡ እና ማናዬ ፋንቱ
በረከት ይስሃቅም ከጨዋታው ታክቲክ
ጋር ሙሉ ለሙሉ ሲቀናጁና ወጣቱ
አቡበከር ናስርም በጥሩ ብቃት ላይ ስላለ
እሱም ወደ ሜዳ ተደጋጋሚ የመሰለፍ
እድሉ ሲሰጠው ያ ችግራችንን ሙሉ ለሙሉ
የምንቀርፈው ነው የሚሆነውና እዚያ ላይ
ብዙ ስጋት ሊኖረን አይገባም፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ
እንዳላፉት ጊዜያቶች አንተስ በቀጣይነት
ስለምትሰጠው ግልጋሎት ?
ኤፍሬም፡- የኢትዮጰያ ቡና ቡድን ውስጥ
በተሰለፍኩባቸው በርካታ ጨዋታዎች ለቡድኔ
ጥሩ ግልጋሎትን ስሰጥ የነበረውና ያለኝንም
ብቃትም በሜዳ ላይ ስተገብር የነበረው
በጓደኞቼ እገዛ ጭምር ነው ከእነሱ ጋር
ተነጋገርን በመግባት ስላለን አጨዋወትም
በመወሰን በሜዳ ላይ ምን ማድረግ
እንዳለብኝም እወስናለው እነሱም የሚያግዙኝ
ነገር አለ፤ ከእዚያ ውጭ ደግሞ አሁንም
ቢሆን ከዚህ በፊት እንደነበሩት አሰልጣኞች
ሁሉ የአሁኑም አሰልጣኝ የሚያዘኝ አንድ
ነገር አለ አንተ የምትጫወትበት ቦታ
ከፍተኛ ሃላፊነት የሚጠይቅ ስፍራ ስለሆነ
ኃላፊነቱን በእዚህ መንገድ ተወጣ ይለኛል፡፡
የእኔ ሃላፊነትም የመጨረሻ ሰው ስለሆንኩኝ
የመጀመሪያው ኳስ ላይ ሳይሆን በቀጣይነት
ያሉትን ለምሳሌ አሁን እኛ ቡድን ላይ ቶማስ
የመጀመሪያው ኳስ ላይ ሃላፊነትን ሲወስድ
እኔ ቀጥሎ ያለውን ነገር ጥንቃቄ በተሞላበት
መልኩ በመወጣት ሚናዬን ልወጣ እችላለሁና
በእዚህ መልኩ ነው የምጫወተው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን
በተመለከተ ምን ትላለህ?
ኤፍሬም፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን
በማስመልከት ሁሌም ስለእነሱ ተናግረህ
የምትጠግባቸው አይደሉም፤ እነሱ የእኛ
መገለጫዎቻችንም ናቸው፤ ራሳችንን
እንድንገልፅ የሚያደርጉንም ናቸው፤ ሁሌ
እነሱ ሲደግፉን ብርታትና ሞራልም ነው
የሚሆኑንና በጣም እንደምንወዳቸውም
መናገርን እፈልጋለው፤ ስለዚህም ዘንድሮ በውጤት ልናስደስታቸውም እንፈልጋለን፡፡