20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር አንድ ጨዋታ ዛሬ ተደርጓል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከወልድያ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
በሁለተኛው ዙር የሊጉ መርሃ ግብር ነጥብ መያዝ የተሳነው ፋሲል ከተማ፥ በይስሃቅ መኩሪያ ብቸኛ ጎል ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ውጤቱን ተከትሎም ፋሲል ከተማ በ19 ጨዋታ 29 ነጥብ መያዝ ችሏል።
ፋሲል ጎንደር ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫዎት በተፈጠረ የደጋፊ ረብሻ ምክንያት፥ አንድ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ እንዲጫዎት በመወሰኑ ምክንያት ነበር የዛሬውን ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ያደረገው።
ሌሎች ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው ሲካሄዱ አዲስ አበባ ላይ መከላከያ ከሃዋሳ ከተማ ይገናኛሉ።
አርባ ምንጭ ላይ ደግሞ አርባ ምንጭ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሁሉም ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ይሆናል።
ከነገ በስቲያ ሃሙስ ደግሞ በሃዋሳ ስታዲየም በቡና ደርቢ፥ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ።
ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ19 ጨዋታዎች 35 ነጥብ ይዞ ሲመራ፥ ደደቢት በ20 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ይከተላል።
ሲዳማ ቡና በ19 ጨዋታ 33 ነጥብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ጨዋታ 32 ነጥቦች በመያዝ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ በ20 ጨዋታ በተመሳሳይ 15 ነጥቦች የደረጃውን ግርጌ ይዘዋል።