የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ዓመት ከታዩት ውሳኔዎች በይዘቱ የከፋ ነው የተባለለትን የቅጣት ውሳኔ በቅ.ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ ላይና የሐዋሳው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላይ አስተላልፏል።
የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ለሁሉም የመገናኛ ብዙሃን በኢሜል እንዳሳወቀው አዳነ ግርማ፣ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ከስፖርታዊ ስነምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት ሲፈፅሙ አግኝቻቸዋለሁ በማለት ጠንከር ያለ ውሳኔ ማስተላለፉን በላከው መግለጫ አሳውቃል።በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔ መሰረት የቅ.ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ ለ6 ወር ከሜዳ እንዲርቅና 10ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት የሐዋሳው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአንድ ዓመት ዕገዳና የ30ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ቡድን በበኩሉ የ25ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ለዝግጅት ክፍላችን በኢሜል የላከው መረጃ ይጠቁማል።
የሀትሪክ ድረ-ገፅ ተከታታዮች በቂ መረጃ እንዲያገኙ በማሰብ የቅጣት ውሳኔውን እንዳለ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ.ም በ10፡00 ሰዓጇቧቧት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛው ዙር ተስተካካይ የእግር ኳስ ጨዋታቸውን ባደረጉበት እለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጫዋች የሆነው ተጫዋች አዳነ ግርማ በእለቱ ዋና ዳኛ ላይ በጨዋታው ወቅት ከስፖርትዊ ጨዋነት የወጣ ድርጊት መፈፀሙ ተረጋግጧል፡፡ ጨዋታውም ከተጠናቀቀ በኋላ ያሳይ የነበረው ከስፖርታዊ ሥነ-ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ለረጅም ጊዜ በብሔራዊ ቡድን እና በክለብ ቡድን ውስጥ ቆይታ እና ልምድ ለጓደኞቹና ለወጣት ተጫዋቾች አርአያና ለስፖርት ተመልካቹ ከበሬታ መስጠት ሲገባው ከእሱ የማይጠበቅ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ጉድለት ከማሳየቱ በተጨማሪ በዳኛው ላይ ምራቁን በመትፋቱ ጥፋት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚሁ መሠረት አዳነ ግርማ ለብሔራዊ ቡድን እና ለክለቡ ለረጅም ጊዜ የሰጠውን አገልግሎት ግምት ውስጥ በማስገባት የሚጣልበትን ከፍተኛ ቅጣት ዝቅ በማድረግ በኢ.እ.ኳ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት ለ6 /ስድስት/ ወር ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጀው ውድድር እንዲታገድ እና ብር 10,000 /አስር ሺ ብር/ የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡
· ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም በ9፡00 ሰዓት በድሬደዋ ስታዲየም ድሬደዋ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር እግር ኳስ ጨዋታቸውን ባደረጉበት እለት የሀዋሳ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በ35ኛው ደቂቃ ዋና ዳኛው ለድሬደዋ ከተማ ቡድን የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት በመቃወም ያልተገባ ድርጊት ፈፅሟል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ ለተጫዋቾች በአርአያነት መታየትና ለስፖርታዊ ጨዋነት ራሱን ማስገዛት ሲገባው በፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን ክፍል 3 አንቀጽ 68 በተራ ቁጥር 3 መሠረት 1 /አንድ/ ዓመት እንዲታገድ እና ብር 30,000 /ሰላሳ ሺህ/ እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡
· በተመሳሳይ ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ወላይታ ላይ በተጫወቱበት እለት በ90+3 ደቂቃ የወላይታ ቡድን ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ድንጋይ እና የውሃ ላስቲክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች በተጠባባቂ መቀመጫ ቦታ በሚገኙ የቡድን አመራሮች ላይ የወረወሩባቸው ስለመሆኑ ከውድድር አመራሮች ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የወላይታ ድቻ ቡድን ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ ከተማ ቡድን ጋር በሜዳው ላይ በተደረገው ውድድር በተፈፀመ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት የቡድኑ አመራር አባላት በዲሲፕሊን ኮሚቴ ተጠርተው ምክርና የቃል ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ከድርጊታቸው አልታረሙም፡፡ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ በፈፀሙት ድርጊት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በኢት.እ.ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ብር 25,000 /ሃያ አምስት ሺህ/ እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡