በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት የእሁድ የሊጉ ጨዋታ አ/አ ላይ ተደርጎ መከላከያ ከሲዳማ ቡና ተገናኝተው ጨዋታቸውን ያለገብ 0-0 ፈፅመዋል።
በጨዋታው መከላከያ በ4-4-2 የጨዋታ ዘይቤ ይዞ ወደ ሜዳ ሲገባ ሲዳማ ቡና በአንፃሩ በ4-4-2 የጨዋታ ዘይቤ ይዞ መግባት ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉና ወደ መከላከያ ግብ ክልል በመድረሱ ረገድ የተሻሉ ቢሆንም ኳስና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
15ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ሀብታሙ ገዛኸኝ የመታው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። በመጀመሪያዎቹ 25 እና 30ደቂቃዎች ውስጥ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ሀይል የተቀላቀለበት ጨዋታ ሲጫወቱ ተስተውሏል። 31ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ተከትሎ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት ኳሱ በርቀት ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህች ሙከራ ፫,3ደቂቃዎች በኋላ 34ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ ተነክቷል በማለት ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም የዕለቱ ዳኛ ጨዋታው እንዲቀጥል አድርገዋል። 42ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ የመታው ቅጣት ምት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጭ ወጥቷል። ይህች አጋጣሚ በጨዋታው ከታዩት አጋጣሚዎች ሁሉ የተሻለች ነበረች። ከ1ደቂቃ በኋላ የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ የሰራውን ስህተት ተከትሎ የተገኘውን ድንቅ አጋጣሚ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ በሲዳማ ቡና በኩል እጅግ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ 0-0 ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችና ጉሽሚያዎች የበዙበት ነበር። 67ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ 69ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳሙኤል ታዬ የሞከሯቸው ኳሶች ወደውጭ ወጥተዋል። 78ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ሀብታሙ ገዛኸን የመታው ኳስ ወደውጭ ወጥቷል። ከዚህ በኋላም የረባ እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት 0-0 ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ ~ መከላከያ
“በጨዋታው ከነበረብን እንቅስቃሴ አንፃር አንድ ነጥብ ማግኘት ያንሰናል። አሸንፈን መውጣት ነበረብን። ከእረፍት በፊት እና በኃላ ያገኘናቸው አራት እና አምስት የሚሆኑ አጋጣሚዎች ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ነበሩ። ጊዜ ቢፈጅም ይህን ችግራችንን እናሻሽላለን።”
አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ~ ሲዳማ ቡና
“በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ ጨዋታ ነበር። ብዙም ውበት አልነበረውም። በ2ኛ አጋማሽ መጨረሻ አካባቢ የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ የነበሩ ኳሶችን በመፍቀድ ጫና አሳድሮብን ነበር።”