ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ!
/በፈረሰኞቹ ገጽ/
በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ሻምፒዮንስ
ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባት የቻለው ክለባችን ቅዱስ
ጊዮርጊስ የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታውን በነገው ዕለት ያደርጋል።
በምድቡ በአንድ ጨዋታ 1 ነጥብ ይዘው 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት
ፈረሰኞቹ ነገ (ማክሰኞ) በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝን ያስተናግዳሉ።
ኤስፔራንሶች በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳቸው እና
በደጋፊያቸው ፊት የዴሞክራቲክ ኮንጎ ክለብ የሆነውን ኤሲ ቪታን
ነበር። የፈረሰኞቹ ገጽ የዚህን ጨዋታ ቪዲዮ በመመልከት እንዲሁም
በጨዋታው ላይ የወጡ ቁጥራዊ መረጃዎችን በመመልከት
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ክለብ የሚተገብረውን የጨዋታ ታክቲክ እና
የጨዋታ እንቅስቃሴ ለመዳሰስ ይሞክራል።
*
ኤስፔራንስ ወደ ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ለመግባት
የማጣሪያ ጨዋታውን ያደረገው የጊኒ ክለብ ከሆነው ሆሮያ አትሌቲክ
ክለብ ጋር ነበር። የመጀመሪያ ጨዋታውን በሜዳው ያደረገው
ኤስፔራንስ 3–1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ጊኒ ላይ በተደረገው
የመልሱ ጨዋታ ሆሮያ አትሌቲክ ክለብ ኤስፔራንስን 2–1 ማሸነፍ
ችሏል። በመሆኑም ኤስፔራንስ በድምር ውጤት 4–3 አሸንፎ
የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድልን መቀላቀል ችሏል።
የቱኒዚያው ሻምፒዮን ኤስፔራንስ ደ ቲኒዝ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ
የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ከኤሲ ቪታ ጋር ሲያደርግ በ4-2-3-1
የጨዋታ ፎርሜሽን ጨዋታውን ጀምሯል፡፡ የኤስፔራንስ ደ ቲኒዝ
ተጋጣሚ የሆነው ኤሲ ቪታ ክለብ የተገበረው ይህንን የጨዋታ
ፎርሜሽን 4-2-3-1 ሲሆን ልዩነታቸው የሚና እና የታክቲክ አተገባበር
ላይ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
ኤስፔራንሶች በ4-2-3-1 የጨዋታ ፎርሜሽን ተጋጣሚን በመጫን
ረገድ እጅግ የተሳካላቸው መሆኑን በቪታ ጨዋታ ላይ አሳይተዋል፡፡
በዚያ ጨዋታ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የጎል ዕድሎችን መፍጠር
ቢችሉም 2 አበይት የጨዋታ ዕቅዶች ላይ በይበልጥ ትኩረት
እንዳደረጉ በግልጽ ይታያል፡፡
የመጀመሪያው የጨዋታ ዕቅዳቸው ተጋጣሚ ቡድን ኳስን በሜዳው
በሚመሰርትበት እና በሚጀመርበት ወቅት በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ
ሜዳ ገብቶ በመጫን ኳስን መንጠቅ ነው፡፡ በቪታ ጨዋታ ላይ በዚህ
የጨዋታ ዕቅድ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የጎል ዕድሎችን መፍጠር
ችለዋል፡፡ በተለይም የተጋጣሚ ቡድን ግብ ጠባቂ ኳስን ከመሃል
ተከላካዮች እና ከመስመር ተከላካዮች ጋር በሚጫወትበት ወቅት
በቁጥር 4 የሚደርሱ የኤስፔራንስ ከወገብ በላይ ያሉ ተጨዋቾች
ተጋጣሚን በጥልቀት ይጫናሉ፡፡ በዚህም የተጋጣሚያቸው ግብ
ጠባቂ እና ተከላካዮች ስህተትን እንዲሰሩ በማስገደድ ኳስን በቀላሉ
መንጠቅ ሲችሉ ተመልክተናል፡፡ በዚህ የጨዋታ ዕቅድ ታግዘው
ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ከማድረግ በላይ ጎል ማስቆጠርም ችለዋል።
ሌላኛው የጨዋታ ዕቅዳቸው ከመስመር እና ከመሃል ሜዳ በረጅም
የሚነሱ የቀጥታ እና የአግድሞሽ ኳሶች ናቸው፡፡ በዚህ የጨዋታ
እንቅስቃሴ የቡድኑ የአማካይ ተከላካዮች አይነተኛ ሚና አላቸው፡፡
የኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ክለብ የማጥቃት መነሻም ከእነዚህ ሁለት
የተከላካይ አማካዮች ነው። እነዚህ ተጨዋቾች ኳሶች እግራቸው ስር
ሲደርሱ ኳሶችን በአየር አሊያም በመሬት በረጅሙ ለቡድኑ አጥቂዎች
እና ለአማካይ የመስመር ተጨዋቾች እንዲደርሱ ያደርጋሉ፡፡
በዚህ ተግባር ላይ ተሳተፊ የሚሆኑት የተከላካይ አማካዮች የመሃል
ሜዳውን መስመር በማለፍ ጭምር ሲሆን ለዚህም የቡድኑ የመስመር
አማካዮች ራሳቸውን ለአግድሞሽ ሩጫ አዘጋጅተው ይጠብቋቸዋል፡፡
ይህ መሳካት ካልቻለ እነኚህ የአማካይ ተከላካዮች ኳሱን በረጅም
ለፊት አጥቂው በመጣል ይህ የፊት አጥቂ ኳሱን ለ2ኛ ኳስ
የማዘጋጀት ሥራ ይሰራል፡፡ በዚህም የቡድኑ የ10 ቁጥር ተጨዋች
ሚናው የገዘፈ ነው።
ኤስፔራንሶች በተጋጣሚ ሜዳ መስመሮች ላይ ኳሶችን ሲያገኙ
የተጋጣሚን ተከላካዮች በቁጥር በልጠው ለመቀነስ የሚያደርጉት
ጥረት ሲሳካላቸው በውስን እንቅስቃሴዎች ላይ ተመልክተናል፡፡
በተጋጣሚ መስመሮች ላይ የተጋጣሚን ተከላካይ ቀንሰው ለመግባት
አሊያም ለቡድኑ የ10 ቁጥር ተጨዋች የፍጹም ቅጣት ምት መግቢያ
ላይ ኳሶችን በማድረስ የጎል ዕድል ለመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህ
የጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ጥፋቶች ሲፈጸሙባቸው የቆመ ኳስ
አጠቃቀም ላይ የሚታይ ጥንካሬ አላቸው፡፡ የቆመ ኳስን በግንባር
የሚገጩ ተጨዋቾቻቸው በቦታ አያያዝ እና በትግል ውስጥ ኳሶችን
የመጠቀም ጥንካሬ እንዳላቸው በግልጽ ይታያል፡፡
*
ኤስፔራንስ ደ ቲኒዝ ከክለብ ቪታ ጋር ባደረገው ጨዋታ 64% የኳስ
ቁጥጥር ብልጫ ሲወስድ ተጋጣሚው ቪታ 36% ብቻ መውሰድ
ችሏል፡፡ 528 የኳስ ቅብብል ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ
84% የተሳኩ የኳስ ቅብብሎሽ ነበሩ፡፡ ስፔራንሶች 24 የጎል
ሙከራዎች ሲያደርጉ ከዚህ ውስጥ 12ቱ ኢላማቸውን የጠበቁ
ናቸው፡፡ ከ12ቱ ኳሶች ውስጥ 3 ኳሶች ወደ ጎልነት ተቀይረዋል፡፡
*
ኤስፔራንስ ከቪታ ጋር ባደረገው ጨዋታ የቡድኑ የመሃል ተከላካይ
ዳኦዲ 71 ኳሶችን በማቀበል ቀዳሚ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 59
ኳሶች የተሳኩ ናቸው፡፡ ሌላኛው የቡድኑ የተከላካይ አማካይ ሳሲ 71
ኳሶችን አቀብሎ 58 ኳሶችን በተሳኩ ሁኔታ ማድረስ ችሏል፡፡ የቡድኑ
የ10 ቁጥር ተጨዋች ሰዓድ ጉዩር 70 ኳሶችን በማቀበል ተከታይ
ሲሆን 49 ኳሶችን በተሳካ ሁኔታ ማድረስ ችሏል፡፡
*
የኤስፔራንስ የግራ መስመር አማካይ የሆነው ቤን የሱፍ በጨዋታው
ላይ 8 የጎል ሙከራዎችን በማድረግ ቀዳሚ ሲሆን ከሞከራቸው 8
ኳሶች ውስጥ 3ቱ ኢላማቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ሌላኛው የቡድኑ
የ10 ቁጥር ተጨዋች ሰዓድ ጉዩር በጨዋታው ላይ 4 የጎል
ሙከራዎችን ማድረግ ሲችል ከእነዚህ ውስጥ 2ቱ ኳሶች ኢላማቸውን
የጠበቁ ናቸው፡፡ እንዲሁም የቡድኑ የቀኝ መስመር አማካይ አኒስ
ባድሪ 4 የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ሲችል ከእነዚህ ውስጥ 2ቱ
ኳሶች ኢላማቸውን የጠበቁ ሆነዋል፡፡
*
ኤስፔራንስ ከክለብ ቪታ ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለውን የተከፋፈለ
የኳስ ቁጥጥር ስንመለከት እስከ 0–15 ደቂቃ ድረስ 56% የኳስ
ቁጥጥር ብልጫ ኤስፔራንስ መውሰድ ችሏል፡፡ ከ15–30 ደቂቃ
ድረስ 67%፣ ከ30–45 ደቂቃ ድረስ 54%፣ ከ45–60 ደቂቃ ድረስ
60%፣ ከ60–75 ደቂቃ ድረስ 61%፣ ከ75–90 ደቂቃ ድረስ 84%
የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተጋጣሚው ላይ ወስዷል፡፡
*
የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው ኤስፔራንስ ደ ቲኒዝ ከክለብ ቪታ
ጋር ባደረገው ጨዋታ 18% ኳሶችን ወደ ኋላ እየመለሰ ሲጫወት
45% ኳሶች ወደ ጎን እንዲሁም 37% ኳሶችን ወደ ፊት ይጫወታል፡፡
ምንጭ-የፈረሰኞቹ ገፅ