የቅዱስ ጊዮርጊስንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በአጥቂ ስፍራ በመምራት የላቀ ግልጋሎትን በመስጠት የሚታወቀው ሳላሃዲን ሰኢድ ትናንት በነበረው የክለቡ ማይነር ጌም ልምምድ ላይ የእግር ላይ ጉዳትን ሊያስተናግድ ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ሳላህዲን ሰኢድ በተጨዋችነት ዘመኑ ሀገር ውስጥ ሲጫወት ለሙገርና ለቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ ግቦችን ጤነኛም ሆኖ ጉዳት ላይም ሆኖ ግብ ሲያስቆጥር የነበረ ሲሆን በተጨዋችነት ዘመኑም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊጉን ዋንጫዎች ከማንሳት ባሻገር በግሉም በ2000 ላይ ኮከብ ግብ አግቢ ተብሎ ተሸልሟል፡፡
ከእዚያ ውጪም በአፍሪካ ክለቦች የዘንድሮ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤት ማማርና የ16ቱ ክለቦች የምድብ ድልድል ውስጥ መግባትም ትልቅ አስተዋፅኦ ከማድረጉ ባሻገር የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ በጋራ ሊሆንም ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ሳላህዲን በትናንቱ የክለቡ ልምምድ ላይ መጎዳቱ በእሁዱ ከመቐለ ከተማ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ላይ መሰለፉን አጠራጣሪ ያደረገው ሲሆን የጉዳቱም መጠን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገቢው ህክምና እየተደረገለት መሆኑም ተገልጿል፡፡