የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ፡በ10 ሰዓት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ለስፖርት መገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥቷል ፡፡ ከአጣሪ ኮሚቴዎች ውስጥ ኢንስፔክተር ጌታቸው የማነብርሃንና አቶ ሸረፋ ደሌቾ በዋና ጸሃፊው ወንድምኩን አላዩ እየተመሩ መግለጫውን ሰጥተዋል ።
የመግለጫው ዝርዝር ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል
ኢንስፔክተር ጌታቸው የማነብርሀን
ከክልሉ ደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር ሰኔ 17 ላይ በሀዋሳ እና ኤሌክትሪክ መካከል በተደረገው ጨዋታ ዙርያ በስፋት ተነጋግረናል፡፡
ኤፍሬም ከኤሌክትሪክ ስልክ ተደውሎለት የሌላ ተጫዋች ስልክ እንዲሰጡት መጠየቁን ገልጿል፡፡ ነገር ግን ስልክ ከመስጠቱ በፊት ተጫዋቹን አናግሮ ቁጥሩን ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆነ በመግለፁ ሳልሰጥ ቀርቻለሁ የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ በተጨማሪም ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ ለክለቡ ያልተጫወትኩ በመሆኑ ከጉዳዩ ጋር ሊያገናኘኝ የሚችል ነገር የለም ብሏል ::የክልሉ ደህንነት ቢሮ ከሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ኤፍሬም ውጤት ለማስለወጥ እያስተባበረ ስለሆነ ክትትል ይደረግበት በሚል በደረሰው ጥያቄ መሰረት ተጫዋቹን እንዳናገረ ገልጿል፡፡ ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ የተገኘ ምንም አይነት ማስረጃ እንደሌለ ገልጸውልናል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ከኮማንደር በላይነህ በቀለ የወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ጋርም ውይይት አድርገናል፡፡ የተከፈቱ የክስ ፋይሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ችለናል፡፡ በዚህም በሀዋሳ እና ኤፍሬም ዘካርያስ መካከል የክስ አቤቱታ እንዳልቀረበ አረጋግጠናል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ እጅ ከፍንጅ የተያዘም ሆነ የታሰረ ግለሰብ እንደሌለ አረጋግጠናል፡፡
በሀዋሳ የነበረውን ማጣራት አጠናቀን ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የኤሌክትሪክ ክለብ ኃላፊዎችን ቃል ተቀብለናል፡፡ ክለቡም ከየትኛውም የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች ጋር የማግባባት ሴራ አልተሰራም፡፡ ተጫዋቾቹ እንዲህ አይነት ጉዳይ ውስጥ እንዳይገቡ እና ከሆቴል እንዳይወጡ ስንቆጣጠር ነበር፡፡ ሆኖም ከሆቴል የወጡ ተጫዋቾች እንደነበሩ አውቀናል፡፡ ብለውናል ከኤሌክትሪክ ክለብ ከተጠረጠሩት 3 ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ በውጪ የሚገኙ በመሆናቸው የአንድ ተጫዋችን ቃል ተቀብለናል፡፡ ይህ ተጫዋችም ከሀዋሳ ተጫዋቾች ጋር የተገናኘው ስለ ክረምቱ ዝውውር መረጃ ለመለዋወጥ እንጂ ውጤት አላግባብ ለማስቀየር አይደለም ብሏል፡፡
ሀዋሳ ከተማ በዚህ ዙርያ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን በሚድያ ቀርበው ማቅረባቸውን ብናደንቅም ማስረጃ የሌለው ጉዳይን ለሚድያ ማቅረባቸው ፣ የፌዴሬሽኑን ደንብ ለክለብ ቅጣት መጠቀማቸው እና ተጫዋቹን ሳያናግሩ በቀጥታ ከራሳቸው ወገን ብቻ ተመልክተው ቅጣት ማስተላለፋቸውን እንደ ደካማ ጎን ወስደነዋል
አቶ ሸረፋ ደሌቾ
እኛ እንደ አጣሪ ኮሚቴ በማጣራት የደረስንባቸው ጉዳዮችን ለህዝብ የመግለጽ እንጂ ተጨማሪ ምርመራ የማድረግ ስልጣን ያለው የፍትህ አካሉ ነው
በተጫዋቾች ውጤት የማስቀየር ሙከራን እንደክለብ ሙከራ የመቁጠር እና እርምጃ ለመውሰድ ስልጣን ያለው የአጣሪ ኮሚቴው ሳይሆን የፍትህ አካል ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የተገኘው ማስረጃ በቂ አይደለም፡፡ ሆኖም የደረስንበትን ደረጃ ለህዝቡ ለማሳወቅ ነው መግለጫውን የጠራነው፡፡ አዲስ ተጨማሪ ማስረጃ ሲቀርብ ማጣራቱ የሚቀጥል ይሆናል
የጅማ አባ ቡናን ክስ የሪፖርቱ አካል ያላደረግነው ይህን የማድረግ ስልጣን ስለሌለን ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው የፍትህ አካል ነው፡፡ ሆኖም ጅማ አባ ቡና የሰጠንን የስልክ ጥሪ መረጃዎች ለማጣራት ስራው ተጠቅመንበታል፡፡