የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአማካይ ስፍራ
ተጨዋች ምንያህል ተሾመ /ቤቢ/
ዋልያዎቹ የጋና አቻቸውን እሁድ እለት
በገጠሙበትና 5-0ም በተሸነፉበት የአፍሪካ
ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ በተመዘገበው
አስከፊ የሚባል ውጤት በጣም ማዘኑንና
ስሜቱንም እንደነካው ለዝግጅት ክፍላችን
አስተያየቱን የሰጠ ሲሆን ተጨዋቹ ከእዚህ
ባሻገርም ክለቡ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ
ሊግ የውድድር መድረክ ላይ እያደረገ
ስላለው ተሳትፎና የውድድር ጉዞም ላይ
አስተያየቱን ሊሰጥ ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምንያህል ተሾመ
በብሔራዊ ቡድን ሽንፈትና በክለቡ ዙሪያ
እንደዚሁም ደግሞ በተጨዋችነቱ እሱ
ለቡድኑ ተሰልፎ በማይጫወትበት ወቅት
ክለቡ ኳስን ተቆጣጥሮ አይጫወትም
እየተባለ ስላለበት ሁኔታም ጠይቀነው
አጠቃላዩን ቃለ- ምልልስ እንደሚከተለው
ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሀትሪክ፡- በኩማሲው ባባያራ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/
0 የጋና ብሔራዊ ቡድን /ብላክስታሮቹ/
5 የሚል ውጤት እሁድ ዕለት በአፍሪካ
ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ላይ
ተመዝግቧል፤ ውጤቱን ስትሰማ በውስጥህ
ምን አይነት ስሜት ተሰማህ?
ምንያህል፡- የዋልያዎቹ ስብስብ
ላይ የአሁን ስኳድ አባል ባልሆንም
እሁድ እለት በተመዘገበው ውጤት እንደ
ኢትዮጵያዊነቴም እግር ኳስ ተጨዋችነቴም
በተመዘገበው ውጤት በጣም ነው ያዘንኩት፤
የዋልያዎቹም ሽንፈት ከማዘኔም ውጪ
ውስጤንም ሊነካው ችሏል፡፡ ሀገራችን
በእዚህ ሰፊ የግብ ልዩነትም ትሸነፋለች
ብዬም ፈፅሞ አልጠበቅኩምም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- የጋና ብሔራዊ ቡድን
ዋልያዎቹን በሰፊ ግብ ለማሸነፍ የቻሉበት
ዋናው ምክንያት ምንድነው ትላለህ?
ምንያህል፡- የጋና ብሔራዊ
ቡድን በአፍሪካ እና በዓለም የእግር ኳስ
ተሳትፎአቸው ላይ ጠንካራ እና ትልቅ
ቡድን እንደሆኑ ሁላችንም እናውቃለን፤
የእኛን ቡድን ለማሸነፍ እንዲችሉም ያላቸው
ጥንካሬና ልምዳቸው ሊጠቅማቸውም
ችሏል፤ ከእዚያ ውጪ በሰፊ የግብ ልዩነት
ለመሸነፋችንም የእነሱ ተጨዋቾች
ካላቸው የተካበተ ልምድ አንፃር የእኛዎቹ
የአሁኑ ስብስብ በተወሰነ መልኩም ቢሆን
የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎና ልምድ
በሌላቸው እና በአዳዲስ ልጆችም በመገንባቱ
እንደዚሁም እንደእነሱ ሁሉ የራሳችንን
አቋም የምንለካበትና ከተጋጣሚያችን አንፃር
በምን መልኩ መጫወት እንዳለብን ለማወቅ
እንዲረዳን ተደጋጋሚ የኢንተርናሽናል
ጨዋታዎችን አለማድረጋችን ጭምር
ተደምሮበት ለጋናው ሽንፈት ምክንያት
ልንሆንና ውጤት ልናጣ ችለናል፡፡
ሀትሪክ፡- የጋና ብሔራዊ ቡድን ለድል
ሲበቃ በሜዳ ላይ የነበረው የጨዋታ ብቃትና
በተደጋጋሚስ ግብ ለማስቆጠር የቻለበት
ዋናው ምክንያት ምን ነበር.. በንፅፅር
የዋልያዎቹስ ብቃት ምን ይመስል ነበር?
ምንያህል፡- የጋና ብሔራዊ ቡድን
ዋልያዎቹን እሁድ ዕለት ለመርታት
የቻሉበት ዋናው ምክንያት በየሚጫወቱበት
ቦታ ላይ ታክቲካል ደሲፕሊን ሆነው
በመቅረባቸውና የእኛም የሜዳ ክልል ጋር
ሲደርሱም ያገኙትን የግብ ማስቆጠር
እድልም ሊጠቀሙም ስለቻሉ ነው፤
ግጥሚያውን በቀላሉና ዘና ብለውም
ነው ያሸነፉት፤ ወደእኛ የብሄራዊ ቡድን
አቋም ስንመጣ ደግሞ ቡድናችን በእነሱ
የመጫወቻ ሜዳ ላይ ሁሉ ሳይቀር
በየቦታው የሚያገኛቸውን የራሱን ኳሶችም
ያበላሽ ነበር፤ እንደመጀመሪያው ጨዋታው
ሊሆንም ይችላል በሁሉም ስፍራም
ላይ ክፍተቶችም ነበሩበትና የነበረው
ልዩነት ሰፋ ያለ ነበር፤ ስለዚህም ከእዚህ
ጨዋታ በመነሳት ብሔራዊ ቡድናችን
ለሚቀጥሉት ግጥሚያዎቹ ብዙ ነገሮችን
አርሞ በመምጣት ብቃቱን ሊያሻሽል ነው
የሚገባው፤ ደግሞም ተገቢ የሆነን ስራ
ከሰራን ራሳችንን የማናሻሽልበት አንዳችም
የሆነ ምክንያት የለም፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ደግሞ ወደ ክለብህ
ቅዱስ ጊዮርጊስ እናምራና የአፍሪካ
ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን እያደረጋችሁ
ይገኛል፤ ጉዞአችሁን እንዴት አገኘኸው?
ምንያህል፡- በዘንድሮ የአፍሪካ
ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ያለን ተሳትፎ
ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ከፍተኛ መሻሻልን
እያሳየንበት እና ውጤትም እያስመዘገብንበት
ያለ ስለሆነ ጉዞአችንን በጥሩ መልኩ ነው
የምገልፀው፤ እስካሁን ባደረግነው ጨዋታም
በመጀመሪያው የማጣሪያ ፍልሚያ
ተጋጣሚዎቻችንን በማሸነፍ የምድብ
ድልድሉ ውስጥ ገብተናል፤ ይኼም ውጤት
በአዲሱ የውድድር ፎርማትም ለአገራችን
እግር ኳስ አዲስ እና ታሪካዊ ውጤትም
ሆኖ ሊመዘገብም በቅቷል፤ የምድብ
ድልድሉ ላይ ከገባን በኋላም ከደቡብ
አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር
ስንጫወት ግጥሚያው ከሜዳችን ውጪ
ቢሆንም ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል፤
ያንን ጨዋታም ለማሸነፍ የምንችልበትም
አጋጣሚውም ነበረን፡፡ በቀጣዩ ጨዋታም
ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ጋር ስንጫወትም
ግጥሚያችንን በሜዳችን እንደማድረጋችን
እና እነሱም በጥሩ አቋም ላይም ሆነው
ስላልቀረቡ እነሱንም ማሸነፍ እንችል ነበር፤
ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ባንችልም በቀጣይ
ጨዋታ ግን የዲሞክራቲክ ኮንጎውን ክለብ
ኤኤስ ቪታን በማሸነፍ ስኬታማ ለመሆን
ችለናልና፤ እንደ አጠቃላይ ክለባችን
በቻምፒዮንስ ሊጉ ላይ እያስመዘገበ ያለው
ውጤት ጥሩ የሚባል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የቱኒዚያውን ኤስፔራንስ
በሜዳችሁ በተፋለማችሁበት እና አቻ
በተለያያችሁበት የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ
ጨዋታ ግጥሚያውን ማሸነፍ እንችል
ነበር ብለሃል? ጨዋታውን ግን ለምን
አላሸነፋችሁም….
ምንያህል፡- ኤስፔራንስን
በተፋለምንበት ጨዋታ ክለቡ በወቅቱ
ከነበረው ጥሩ ያልሆነ ወቅታዊ አቋም፣
ከነበረው የአየር ሁኔታና በሜዳችንም
ከመጫወታችንም አኳያ አሁንም ቢሆን
አዎ! ጨዋታውን ለማሸነፍ የምንችልበት
አጋጣሚው ነበረን ብዬ አፌን ሞልቼ
ለመናገር እፈልጋለው፤ ያንን ግጥሚያ
ለማሸነፍ አለመቻላችንም ሁላችንንም
ሊያስቆጨንም ችሏል፤ ላለማሸነፋችንም
ያገኘናቸውን የግብ እድሎች ለመጠቀም
አለመቻላችን እና ኳሱንም በብዙ መልኩ
ለመቆጣጠር አለመቻላችን ግጥሚያውን
እንዳናሸንፍም አድርጎናል፤ የቱኒዚያውን
ክለብ በተፋለምንበት ጨዋታ የቡድናችን
አሰልጣኝ ፋሲል ኳስን ተጫወቱ
የሚልበት አጋጣሚውን እሰማ ነበር
ያንን ለመተግበር አልተቻለም እነሱ
ተከላክለው ስለመጡም አቻ ሊወጡ ቻሉ፡
፡ ያም ሆኖ ነጥብ መጣልም በእግር ኳሱ
ላይ የሚያጋጥም አንዱ አካል ስለሆነም
በኤስፔራንሱ ጨዋታ የተቆጨንበት
አጋጣሚውም አለ፡፡
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ
ጨዋታዎች ላይ በተለይ ደግሞ
የኢንተርናሽናል ግጥሚያዎች ሲኖሩ
ምንያህል በቋሚነት ካልተሰለፈ ወይም
ደግሞ ተቀይሮ ካልገባ ቡድናችሁ ኳስን
ተቆጣጥሮ መጫወት አይችልም ሲባል
ይሰማል፤ ቡድናችሁ ኳስን ለመጫወት
እንዲችልም ያለ ምንያህልም ምንም
ነውም የሚሉም ነገሮች ይደመጣሉና
በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
ምንያህል፡- የእግር ኳሱ ላይ
ሁሉም ሰው የየራሱ አመለካከትና
አስተያየት አለው፤ ስለእኔም ብዙ ሊባልም
ይችላል፤ ያም ሆኖ ግን ክለቤ ቅዱስ
ጊዮርጊስ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ እኔ ተሰልፌ በማልጫወትበት ወቅትክለባችንን ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት
አይችልም የሚለውን ነገር እኔ ፈፅሞ
መናገር አልፈልግም፤ ምንም ነገርን ማለትም
አልወድምም፤ ቡድናችንን ኳሱን ተቆጣጥሮ
ለመጫወት እንዲችል ከእኔ ውጪ የምል
አይነት ሰውም አይደለውም፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ
እንደ ግል ሳይሆን እንደ ህብረት በጋራ
የሚጫወት ክለብም ነውና ይህን ነው ማለት
የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች
የመሃል ሜዳው ላይ የአንተን መኖር ብዙ
ጊዜ ይፈልጋሉ፤ ወደ ሜዳ እንድትገባም
ደጋፋቸውንም ሲያንፀባርቁ ይስተዋላሉና
በዚህ ዙሪያ ምን ማለት ትፈልጋለህ?
ምንያህል፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ
ደጋፊዎች የራሳቸውን ስሜት በማንፀባረቅ
የእኔን ወደሜዳ መግባትን የሚፈልጉት
ለቡድኑ የመሃል ሜዳ እንቅስቃሴ ማማርና
ውጤታማነትም አንድ ነገርን ይሰራል
ብለው አስበው እንደሆነ እኔ ጠንቅቄ ነው
የማውቀው፤ እኔም ክለቤን ወደ ሜዳ ገብቼም
ብጠቅመው በጣምም ነው ደስ የሚለኝ፤
ነገር ግን ደጋፊው ይግባ ስላለ ብቻ ዘው ብዬ
የምገባ አይነት ተጨዋችና ጀማሪም ተጨዋች
አይደለሁም፤ አሰልጣኞቹ እኔን ሊተገብሩት
ለሚፈልጉት አጨዋወትም ነው ወደ ሜዳ
የሚያስገቡኝ፤ አሰልጣኞች በየጨዋታው
የየራሳቸው ታክቲክ አላቸው፡፡ የእኔ የእዚህ
ጨዋታ ምርጦችና ተሰላፊዎችም እነዚህ
ናቸውም ብሎ ሲያስገቡን ነው ያኔ ለቡድንህ
የምትሰለፈውና ሁኔታውን እንደተጨዋችነቴ
በእዚህ መልኩ ነው የማየው፡፡
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ልክ
የዛሬ ሳምንት 4ኛውን የአፍሪካ ቻምፒዮንስ
ሊግ ጨዋታውን ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ
በማምራት ከቪታ ክለብ ጋር ይጫወታል፤
ስለጨዋታውና ወደተከታዩ ዘር ለማለፍስ
ስላላችሁ ዝግጁነት ምን የምትለው ነገር
አለ?
ምንያህል፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ
የቻምፒዮንስ ሊጉ ዋናው ተሳትፎ ወደ
ተከታዩ ዙር በማለፍ የሩብ ፍፃሜውን
መቀላቀል ነው፤ በእዚህ ውድድር ክለባችን
አዲስ ታሪክም ማስፃፍ ይፈልጋል፤ ስለዚህም
ለማክሰኞው ጨዋታም ሆነ በቀጣይ ላሉብን
ግጥሚያዎች ቡድናችን ያለበትን ቀዳዳዎችና
ክፍተቱን በመድፈን ለጨዋታው በሚገባ
እየተዘጋጀም ይገኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ
ተሳትፎአችሁ ላይ ጠንካራና ክፍተት
ጎናችሁ ምኑ ላይ ነው?
ምንያህል፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ
በቻምፒዮንስ ሊጉ ያለው ጠንካራ ጎን
እስካሁን ግብ ያልተቆጠረበት ቡድን መሆኑ
ነው፤ ይህም የመከላከሉን ጥንካሬው ሊያሳየን
ችሏል፤ ሊያስተካክል ይገባዋል የምለው ነገር
ደግሞ በተለይ የምድብ ድልድሉ ላይ ከገባን
በኋላ እስካሁን በ3 ጨዋታ ያስቆጠርነው
ግብ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ችግራችንን
በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ልናስተካከልና
ልናርመው ነው የሚገባን፡፡
ሀትሪክ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት
የጀመርከው ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ በቅርቡ
ነው፤ ቡድኔን ጠቅሜዋለሁ ትላለህ?
ምንያህል፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ
ጋር በነበረኝ የእዚህ አመት ቆይታ ረዘም
ላለ ጊዜ በጉዳት ላይ ስለነበርኩ ቡድኔን
በምፈልገው መልኩ እና ደረጃ ላይ ልጠቅመው
አልቻልኩም፤ አሁን አሁን ግን በጤናዬ
በኩል መሻሻልን በማሳየቴና ወደፊትነሴም
ከምሰራው ልምምድና ከማድረጋቸውም
ጨዋታዎች በመነሳት አሁን በጥሩ ሁኔታ
ላይ የምገኝ ተጨዋች ስለሆንኩ ቅዱስ
ጊዮርጊስን እንደበፊቱ በጥሩና በምርጥ የሆነ
ብቃቴ እንደማገለግለው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች
የእዚህ አመትን ድጋፍ እንዴት
ተመለከትከው?
ምንያህል፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ
ደጋፊዎች ዘንድሮ እኛን ለማበረታታት
ይዘው የመጡት ድጋፍ የተለየ አይነትና
በሁሉም ዘንድም ያስደነቃቸው ነው፡
፡ ደጋፊዎቹ ለሁሉም ተጨዋቾች እኩል
የሆነ አመለካከትም አላቸው፤ ይህ
ድጋፋቸው የሚያምርና እኛንም ለውጤት
ለማብቃትም በማስቻሉ በኩል እኛን በጣም
ያነቃቃን ስለሆነም በእዚህ አጋጣሚ እነሱን
ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን
ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፉ አንድ አንድ
የቀድሞ ተጨዋቾች ራሳቸውን ከዋልያዎቹ
ውጪ በማድረግ እና ለብሄራዊ ቡድንም
መጫወት በቃኝ በማለትም ራሳቸውን
ሲያገሉ ነበር፤ ምን ያህልስ በቃኝ ይላል
ወይንስ ወደብሄራዊ ቡድን በድጋሚ መጥቶ
መጫወት ይፈልጋል?
ምንያህል፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ
ቡድን የቱን ያህል ጊዜ ተጫውቼ ነው
አሁን ላይ በቃኝ የምለው፤ የዋልያዎቹን
ስብስብ በድጋሚ መቀላቀል እና ሀገሬንም
በጣም ማገልገል እፈልጋለሁ፤ ለእዚያ
ለመብቃት ግን በቅድሚያ አሁን ከክለቤ ጋር
የማደርጋቸው ጨዋታዋች ላይ በቅርብም
ከጉዳት የተመለስኩ ተጨዋች ስለሆንኩ
ራሴን በሚገባ በማዘጋጀትና በሙሉ ብቃትም
ላይ ራሴንም በማስገኘት የብሄራዊ ቡድን
ተመራጭ ተጨዋች ለመሆን እፈልጋለሁ፤
እና እኔ ይህን ነው አሁን ላይ እያሰብኩ
ያለሁት፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ?
ምንያህል፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ
የእዚህ አመት የውድድር ቆይታዬ ላይ
ረጅሙን ወቅት በጉዳት ባሳልፍም አሁን
ላይ ወደ ሜዳ ተመልሼ ቡድኔን በምችለው
አቅም እያገለገልኩ መሆኔ አስደስቶኛል፡
፡ ወደ ሜዳ ቶሎ እንድመለስም የፓራጎን
ፊዚዮትራፒዎችም ያደረጉልኝ እገዛ ከፍ
ያለም ነበር፤ እነሱን እንደዚሁም ከጎኔ
የነበሩትን የቡድኔ ደጋፊዎችና ክለቤን
እንደዚሁም ቤተሰቦቼንና ጓደኞቼን
ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡