በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም በሀዋሳ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መጀመር በፊት የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ለቀድሞ የሀዋሳ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ደግሞ ለወልቂጤ ከተማ እየተጫወተ ለሚገኘው ድንቅ አጥቂ አዳነ ግርማ የማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል። ማራኪ እንቅስቃሴ እና ብዙ የግብ ሙከራዎች በታየበት ጨዋታ ገና ከመጀመሪያው ደቂቃዎች አንስቶ ሁለቱም ቡድኖች ወደግብ ለመድረስ ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
- ማሰታውቂያ -
ፋታ የለሽ እንቅስቃሴ የነበረው ቀጥሎ ጨዋታው በተጀመረ 10ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማው አክሊሉ ተፈራ ባደረጋት ሙከራ ተጀምሯል። ከዚህች ሙከራ በኋላም የጨዋታው ሙከራዎች ፍሬ አፍርተው ጨዋታው በተጀመረ በ20ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሀዋሳ ከተማው አለልኝ አዘነ ሲመልሰው በዚህ አመት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ወጣቱ ብሩክ በየነ የቀድሞ ክለቡ ላይ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ወልቂጤ ከተማዎች ኳስ ተቆጣጥረው ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ የወልቂጤ ከተማው ጃኮ አረፋት ግብ አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራለች።
በዚህ ውጤት ጨዋታው ቀጥሎ 34ኛው ደደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማው ዳንኤል ደርቤ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረው ሄኖክ አየለ በግንባሩ ገጭቶት የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ሌላ ተጨማሪ ሙከራ እና ግብ ሳይስተናገድበት የመጀመሪያው አጋማሽ በሀዋሳ ከተማ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት 1 ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀባቸው። 46ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ አጥቂው ጃኮ አረፋት ያሻገረለትን ኳስ ጫላ ተሺታ አስቆጥሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ሀዋሳ ከተማዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ከሄኖክ ድልቢ የተቀበለውን ኳስ ወደግብነት ቀይሮት ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ሀዋሳ ከተማን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል። ሀዋሳ ከተማዎች በዚህ ሳይገቱ ዘላለም ኢሳያስን ቀይረው በማስገባት ወደ ወልቂጤ ከተማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። ከዚህ በኋላም 84ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አየለ ለሀዋሳ ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ 3-1 በማሳደግ ባለድል እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።