በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ሐዋሳ ከተማ በሜዳው መቐለ ከተማ አስተናግዶ 0ለ0 በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል፡፡ በሁለቱም ክለቦች ደጋፊ ያማረ ዝማሬ ነበር ጨዋታው የተጀመረው፡፡ በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች በአመዛኙ ተመጣጣኝ ኳስ ነበር፡፡ ሐዋሳ ከተማዎች ከወትሮ የሚታወቁበትየመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር፡፡
በ20ኛው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጋይስ ቢሰማርክ አጊንቶ የሞከራት የሐዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሳሆሆ ሜንሳህ በቀላሉ አድኖበታል፡፡በ22ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ ዳዊት ፍቃድ ያገኘውን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
በ25ኛው ደቂቃ አዲስ ተስፋዬ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ለፍሬው ሰለሞን አቀብሎት ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ለሀይቆቹ መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ለግብ የቀረበ ሙከራ የተመለክትንው በ33ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ መዳኔ ታደሰ ከቅብ ርቀት የመታት ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ ልትወጣ ችላለች፡፡በ45ኛው ደቂቃ ፍርዳወቅ ሲሳይ ለፍሬው ሰለሞን ያቀበለውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡በዚሁ ውጤት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ መቐሌ ከተማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸው ሙከራ በማድረጉ ረገድ ሐዋሳ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ፡፡በ52ኛው ደቂቃ ከዳዊት ፍቃዱ የተቀበለውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ሳይጠቀምበት ሲቀር ከ2 ደቂቃ በኃላ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ አዲስ ተስፋዬ መቷት በግቡ ቋሚ ታካ ወጣለች፡፡ ሐዋሳ ከተማ ኳስ መስርቶ ለመጫዎት ሲሞክር መቐለ ከተማዎች በማጨናገፍ ባለሜዳዎቹን ተጭነው ተጫወተዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በ72ኛ ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከሳጥን ውጪ የተሰጠውን ቅጣት ምት አዲስ ተስፋዬ መቶት የመቐሌ ከተማ ግብ ጠባቂ ፍሊፕ አቬኖ ለጥቂት አድኖበታል፡፡በ90ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ተከስተ ከርቀት የመታትን ኳስ ሳሆሆ ሜንሣህ በቀላሉ ሊያድንበት ችሏል፡፡ በጨዋታው የመጨረሻዎ ደቂቃዎች ባለ ሜዳዎቹ ሐዋሳ ከተማዎች ተጭነው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ 4ኛው ዳኛ ጭማሪ 4ደቂቃ ጭማሪ ካሳዩ በሗላ ሙላለም ረጋሳ ከርቀት በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገነኝቶ ያመከናት ኳስ እምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀረ ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ፍርዳወቅ ሲሳይ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ የመታት ኳስ ወደ ውጪ ወጣለች፡፡ በዚሁ ጨዋታው 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ-ሀዋሳ ከተማ
“በሜዳው ላይ የታየው ነገር በቲማችን የተለመደ አይደለም ጫዋታውን መቆጣጠር አልቻልንም፡፡በተጋጣሚያችን ጥንካሬ ሳይሆን በራሳችን ክፍተት ነጥብ ተጋርተናል፡፡መጥፎ ቀናችን ነበር ችግራችን ምን እንደሆነ ከልጆቼ ጋር አውርተን የምንፈታው ይሆናል፡፡”
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ-መቐለ ከተማ
“ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር በአርቴፊሻል ሜዳ እንደምንጫወት አናቅም ነበር፡፡ ዛሬ ነው ያወቅንው ስናውቅ ተረብሸን ነበር፡፡ለሊጉ አዲስ እደመሆናችን በሊጉ ለመቆየት ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን፡፡ ደረጃ ለኛ ዋጋ የለውም ዋናው መቆየታችን ነው፡፡”