በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲውሉ አዲስ አበባ እና ክልል ላይ 4ጨዋታዎች ተከናውነዋል።
በአ/አ ስታዲየም በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ መከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ተገናኝተው ባለሜዳው መከላከያ 1-0 በሆነ ማሸነፍ ችሏል።
ለመከላከያ ብቸኛዋን ግብ በዘንድሮው የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ወጣቱ ምንይሉ ወንድሙ በ13ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችሏል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጥሩ የሚባል እና ነቃ ያለ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ነበር። በመጀመሪያ አጋማሽ መከላከያ የተሻለ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለማስጠበቅ ተከላክለው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማ ውጤቱን ለመቀልበስ ተጭነው ተጫውተዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኀላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የመከላከያ አሰልጣኝ ሻ/ል ምንያምር ፀጋዬ “እስካሁን የተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች የራሳችን ስህተት ነው። ወይ ያገኘናቸውን የግብ ማግባት አጋጣሚዎች በአግባቡ አለመጠቀም አልያም በጥቃቅን ስህተቶች ጎል ማስተናገዳችን ነበር። በእኔ ብቻ ሳይሆን በበላይ አካላትም ጭምር ተገማገምን እና ችግራችንን ፈታን። ቡድኑ ጥሩ ይጫወታል፤ ጎል የማግባት ችግር ስለነበረበት ውጤታማ አልነበረም። ከእረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች ተጭነውን ነበር እኛ ደግሞ ስንከላከል ነበር። በአጠቃላይ ድሬዳዋ ከተማ ጥሩ ቡድን ነው።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ም/አሰልጣኝ ስምዖን አባይ በበኩላቸው “በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው የቡድናችን ቅርፅ እና ሁኔታ አጥጋቢ አልነበረም። በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ(መከላከያ) ሙሉ በሙሉ በልጠውን ነበር፤ በሁለተኛው አጋማሽ እኛ የተሻልን ነበርን። ያም ሆነ ይህ ግን ጎል አግብተን እስካላሸነፍን ድረስ ቡድኔ ጥሩ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ስለዚህ ውጤቱ እንቅስቃሴአችንን የሚገለጽ ነው፤ መሸነፋችን ተገቢ ነው።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ድሬዳዋ ከተማ ከ7 ጨዋታዎች 7ነጥቦች ብቻ በመሰብሰቡ አደጋ ውስጥ ነው ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ ” በ8ኛ ሳምንት ላይ ስለ አደጋ ማውራት ተገቢ አይመስለኝም። ሆኖም ግን አሁን የምንሸነፋቸው ጨዋታዎች እና የምንጥላቸው ነጥቦች በኋላ ላይ ዋጋ ሊያስከፍሉን ይችላሉ።” በማለት አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።