በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ 1ጨዋታ ዛሬ (ዕሁድ) ተደርጎ መከላከያን ከመቐለ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ምንይሉ ወንድሙ ለመከላከያ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት መከላከያን ከ2003-2008 ለ5 ዓመታት ላገለገለው የአሁኑ የመቐለ ከተማ አምበል ሚኬኤሌ ደስታ 13 ቁጥር የታተመበት ማልያ በፍሬም ተደርጎ ከመከላከያ ተበርክቶለታል።
በርካታ ደጋፊ በታደመበት እና እንደተለመደው የመቐለ ከተማ ደጋፊዎች ደምቀው ባመሹበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መከላከያ ከተጋጣሚው በተሻለ የማሸነፍ ፍላጎት ተስተውሎበታል። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ ለማስተናገድ የወሰደበት የ6ደቂቃዎች እድሜ ብቻ ነበር። 6ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ታፈሰ ሰርካ ከማዕዘን ያሻገረለትን ኳስ ተከላካዩ አወል አብደላ ሞክሮት የመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ ፊልፕ አቮኖ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። ከዚህ በኋላ መከላከያ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል ለመድረስ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ላይ መሰረት ያደረገ ጨዋታን ሲያደርግ ተስተውሏል። ለዚህም አጨዋወት ዋነኛ ሚና ሲወጡ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል ማራኪ ወርቁና ምንይሉ ወንድሙ ተጠቃሽ ናቸው። በግራ ክንፍ በኩልም የታፈሰ ሰርካ ፍጥነቱን በመጠቀም ወደ ግብ ያሻገራቸው የነበሩት ኳሶች እጅግ አስፈሪ ነበሩ።
- ማሰታውቂያ -
ወደኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉት መቐለ ከተማዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግሩም ሁኔታ በግራ እግሩ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ የተመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራቸው ነበር።39ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ ፊልፕ አቮኖ የሰራውን ስህተት ተከትሎ የተገኘውን ኳስ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከ2 ደቂቃዎች በኋላ 41ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ ፊልፕ አቮኖ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። በተደጋጋሚ ከቆሙ ኳሶች የመቐለ ከተማን ግብ ያንኳኩት መከላከያዎች 44ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰርካ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ በግሩም አቋቋም ላይ ቢገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይህንንም ተከትሎ መከላከያ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ መውሰድ ቢችልም ያገኛቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ባለመቻሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተሽለው የቀረቡት መቐለ ከተማዎች ከመከላከያ በተሻለ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል። በዚህም እስካሁን ይስተዋል የነበረው የመቐለ ከተማ የመከላከል አጨዋወትን ትቶ ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በ5 ደቂቃ ውስጥ 3ጊዜ ያህል ወደ ግብ በመድረስ አስደንጋጭ ሙከራዎች ማድረግ መቻላቸው ነው። 51ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከቀኝ በኩል ያሻገረለትን ኳስ ያሬድ ከበደ ወደግብ ሞክሮት የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ በቀላሉ ይዞታል። ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ 53ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከቀኝ ክንፍ በኩል አግኝቶ የሞከረው ኳስ ወደ ውጭ ሲወጣበት 55ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበደ ከግብ ጠባቂው ጋር 1-1 ተገናኝቶ ያባከነው ኳስ በመቐለ ከተማ በኩል እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ከዚህ ሙከራ 6ደቂቃዎች በኋላ 61ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የኋላ መስመር ሽመልስ ተገኝ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ በጨዋታው ድንቅ ሆነው ያመሹት ምንይሉ ወንድሙና ማራኪ ወርቁ ተቀባብለው ምንይሉ በቀጥታ በመምታት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከ1ደቂቃ በኋላ 62ኛው ደቂቃ ላይ በመቐለ ከተማ በኩል ድንቅ ሆኖ ያመሸው ወጣቱ ድንቅ አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ በቀጥታ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ መከላከያ ነጥቡን አስጠብቆ ለመውጣት እንዲሁም መቐለ ከተማ ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ 70ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው ሚካኤል ደስታ ከማዕዘን ምት ያሻገረለትን ኳስ ጋይሳ አፖንግ ሞክሮት ወደ ውጭ ወጥቷል። 85ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከሳጥን ውጭ የሞከረውን ኳስ የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ሲተፋው አማኑኤል ገ/ሚካኤል በድጋሚ አግኝቶ ሞክሮት አቤል ማሞ በድጋሚ በድንቅ ሁኔታ አድኖበታል። ከዚህም በኋላ መከላከያዎች በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ በመውደቅ ሰዓት ለማባከን ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ የመቐለ ከተማ ደጋፊዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በዚህም ጨዋታው በመከላከያ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ሻ/ል ምንያምር ፀጋዬ—- መከላከያ
” መቐለ ከተማ እንደ ድሮው በመከላከል ሳይሆን በማጥቃት ለመጫወት ሞክሯል። ሁለቱም ቡድን ኳስ ይዞ ለመጫወት ጥረት ሲያደርግ ነበር። እንቅስቃሴው ጥሩ ነበር። ”
ም/አሰልጣኝ ጎይቶም ሃይለ—- መቐለ ከተማ
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ 90 ደቂቃ ሙሉ አጥቅተናቸው ነበር፤ እንደ አጋጣሚ 1ጎል ተቆጥሮብናል፤ በፀጋ እንቀበላለን። የአጨራረስ ድክመት ነበረብን፤ እሱንም በሁለተኛው የውድድር አመት ቀርፈን እንመጣለን። በሁለተኛው ዙር የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ጥረት እናደርጋለን፤ እሱንም እናሳካለን።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ስለ ዕለቱ ዳኛ የተጠየቁት ም/አሰልጣኙ “ስለ ዳኛ ስትናገር ሌላ ነገር ስለሚመጣ ምንም ነገር መናገር አልችልም።” በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።