በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የመጨረሻ 1ጨዋታ ዛሬ አ/አ ላይ ሲደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ የወሰነው የወልዋሎ አ.ዩ. እና የወልዲያ ስፖርት ክለብ ጨዋታ ያለግብ 0-0 በሆነ ውጤት መለያየት ችለዋል።
ሞቅ ደመቅ ብሎ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመልካቾችን ቁጭ ብድግ በሚያደርጉ ሙከራዎች የታጀበ ነበር። ወልዋሎ አ.ዩ. በ4-3-3 የጨዋታ ዘይቤ ወልዲያ ስፖርት ክለብ በበኩሉ በ4-4-2 የጨዋታ ዘይቤ ወደሜዳ በመግባት ጨዋታቸውን አከናውነዋል። በወልዋሎ በኩል ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ በቁጥር ብልጫ መውሰድ ሲችሉ የቀኝ እና የግራ ተከላካዮቹ ለዚህ ቁጥር ብልጫ ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክተው ነበር።
በወልዲያ በኩል ወደግብ የሚደርሱት ኳሶች መነሻቸውን በግራ ክንፍ በኩል በምንያህል ተሾመ እና በፍፁም ገ/ማርያም ያደረጉ ነበሩ። ሆኖም አጥቂው ኤዶም ኮድዞ በቀድሞው ብቃቱ ላይ ባለመገኘቱ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ወጥተዋል።
በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በተለይ ደግሞ የመጀመሪያው 30 ደቂቃ ላይ ወልዋሎ አ.ዩ. ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ብልጫ መውሰድ ችሎ የነበረ ሲሆን ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ የወልዋሎው እዮብ ወ/ማርያም በድንቅ ሁኔታ ተከላካዮችን አታሎ የሞከረውን ኳስ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቤሌንጋ ኤኖህ በቀላሉ ይዞበታል።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ 5ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ብርሃኑ አሻሞ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። ወደ ወልድያ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የቻሉት ወልዋሎዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ አፈወርቅ ሀይሉ ከሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭታ ወደውጭ ወጥታለች። ይህች ሙከራ በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበሩት ሙከራዎች ድንቋ ነበረች። 26ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው እዮብ ወ/ማርያም ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ ቺፕ አድርጎ የሞከራትን ኳስ በረኛው ጨርፎ ወደውጭ አውጥቷቷል። በመጀመሪያው 25 ደቂቃዎች ውስጥ እጅግ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው እዮብ ወ/ማርያም ይህችን ሙከራ ከሞከረ በኋላ በሜዳ ውስጥ መቆየት የቻለው ለ2 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በጉዳት ምክንያት በቢኒያም አየለ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል። የመጨረሻዎቹን 15ደቂቃዎች ይሄ ነው የማይባል ሙከራ ሳይደረግበት ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወልድያዎች መነቃቃት ያሳዩ ሲሆን ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል በመቅረብም ሆነ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው አምሽተዋል። ሆኖም ግን በሁለተኛውም አጋማሽ የሙከራ ቅድሚያውን የወሰዱት ወልዋሎዎች ነበሩ። 48ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው መኩሪያ ደሱ የሞከረውን ኳስ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቤሌንጋ ኤኖህ ቢተፋውም በአቅራቢያው ሰው ባለመኖሩ የሚጠቀምበት ጠፍቷል። ከ4ደቂቃዎች በኋላ 52ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው አፈወርቅ ሀይሉ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል።
- ማሰታውቂያ -
በመልሶ ማጥቃት ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ወልዲያዎች 55ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው የቀድሞው የቅ/ጊዮርጊስ አማካይ ተስፋዬ አለባቸው(ቆቦ) ከመሀል ሜዳ አካባቢ በቀጥታ ወደ ጎል ሙከራ ቢያደርጉም ኳሱ ወደ ውጭ ወጥቷል። እጅግ ከፍ ያለ የተጫዋቾች ግጭት በበዛበት በዚህ ጨዋታ ከሁለቱም ቡድኖች ሶስት ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ተቀይረው ሊወጡ ችለዋል።
71ኛው ደቂቃ ላይ የወልዲያ ስፖርት ክለቡ አጥቂ ፍፁም ገ/ማርያም ከበረኛው ጋር በ3ሜ ርቀት ተገናኝቶ የሞከረውን ኳስ በቀላሉ ይዞበታል። ይህ ሙከራ እጅግ ያለቀለት እና መቆጠር ቢችል ኖሮ የጨዋታውን ውጤት ሙሉ ለሙሉ መቀየር የሚያስችል ነበር።
78ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎ ተከላካይ እስሪ አልማህይ ከቀኝ ክንፍ በኩል በቀጥታ የመታውን ኳስ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቤሌንጋ ኤኖህ ይዞታል። 83ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ብርሃኑ አሻሞ ከመሀል ሜዳ በቀጥታ የሞከረውን ኳስ በረኛው እንደምንም ብሎ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። መደበኛ የጨዋታው ክ/ጊዜ ሊጠናቀቅ 4ደቂቃዎች ሲቀሩት 86ኛው ደቂቃ ላይ አንዱአለም ንጉሴ (አቤጋ) ከግራ በኩል ከፍፁም ገ/ማርያም የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶት ወደውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ በመውደቅ ሰዓት ሲያባክኑ ተስተውለዋል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ ያለግብ ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
የወልዋሎ አ.ዩ. ዋና አሰልጣኝ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር
“በጨዋታው ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አልተጠቀምንባቸውም፤ በእንቅስቃሴው ግን በጣም ረክቻለሁ። የግብ ማግባት ችግር ነው እንጂ እንቅስቃሴያችን ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ ነው፤ እንቅስቃሴ ደግሞ እርማት ይፈልጋል።”በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ጉዳት ላይ ስላሉ ተጫዋቾች ተጠይቀው አሰልጣኙ ሲመልሱ “በዛሬው ጨዋታ ሙሉዓለም ያለመኖሩ በጣም ጎድቶናል። እሱ ቢኖር ኖሮ አሸንፈን መውጣት እንችል ነበር። ከደደቢት ጋር በሚኖረን ጨዋታ ሙሉዓለምየሚመለስ ይሆናል፤ በርግጠኛነት ከደደቢት 3ነጥቦች እንወስዳለን።” በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።
የወልዲያ ስፖርት ክለብ ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ በመጀመሪያው አጋማሽ ወልዋሎዎች በስሜትና በፍላጎት የተሻሉ ነበሩ። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ወስደን ነበር፤ እንዳገኘናቸው የግብ አጋጣሚዎች 3ነጥብ ይገባን ነበር።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።