የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ ወጣ ገባ የሚል አቋም እያሳየ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ በሜዳው ባህርዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ የሚገኘውን ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ማሸነፍ ችሏል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሁለቱም ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ማሸነፍ የሚቸገሩ ቡድኖች ሲሆኑ እስካሁን ከሜዳቸው ውጪ ምንም ድል ማስመዝገብ አልቻሉም።
በዛሬው ጨዋታ ባህርዳር ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን 3-2 በሆነ ውጤት ነው ማሸነፍ የቻለው። በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍተኛ ጫና መፍጠር የቻሉት ባለሜዳዎቹ ባህርዳር ከነማዎች በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡናን የግብ ክልል እንደልብ ሲመላለሱበት ውለዋል። በዚህም አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሙከራ ብዛት ባለሜዳዎቹ ተሽለው የተገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ብቅ ጥልቅ የሚል ጨዋታ ነበር ሲያደርጉ የነበረው።
- ማሰታውቂያ -
ባለሜዳዎቹ ባህርዳር ከነማዎች በጨዋታው የመጀመሪያውን ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው 16ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 14ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ሀይሉ ያገኛትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር 2ደቂቃዎች በኋላ 16ኛው ደቂቃ ላይ በዘንድሮው የውድድር አመት ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳየ የሚገኘው ፍፁም ዓለሙ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ 2-0 ከፍ ማድረግ ችሏል። በዚህ ያላበቁት እና በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡናን የግብ ክልል መደብደብ የጀመሩት ባህርዳር ከነማዎች ከ4 ደቂቃዎች በኋላ 20ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ 3ኛውን ግብ አስቆጥሮ በመጀመሪያዎቹ 20ደቂቃዎች ውስጥ ባህርዳር ከነማን 3-0 እንዲመራ አስችሎታል። ከሶስቱ ግቦች በኋላ ባህርዳር ከተማ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ግብ ሳያስተናግድ ለመውጣት ወደኋላ አፈግፍገው መጫወትን መርጠዋል። ይህም ለኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የግብ እድልን እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል። በተደጋጋሚ በአቡበከር ነስሩ እና በአቤል ከበደ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርተዋል። ሆኖም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 3ደቂቃዎች ሲቀሩት 42ኛው ደቂቃ ላይ የባህርዳር ከነማ ተጫዋቾች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት በጨዋታው ጥሩ ሆኖ የዋለው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ነስሩ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ውጤቱን ወደ 3-1 በማጥበብ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅተው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ የባህርዳር ከተማ ተከላካዮችን ሲያስጨንቁ ተስተውሏል። ሆኖም ግን 53ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን መልክ ሊቀይር የሚችል አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር የኢትዮጵያ ቡናው አቤል ከበደ የባህርዳር ከነማው ግርማ ዲሳሳ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት የእለቱ ዳኛ ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሰ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል። ከዚህም በኋላ ባህርዳር ከነማዎች የተገኘውን የቁጥር ብልጫ ይወስዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ለኢትዮጵያ ቡና ሰፊ የመጫወቻ ቦታ ሊሰጧቸው ችለዋል።
ማራኪ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 71ኛው ደቂቃ ላይ በፍ/የሱስ ተ/ብርሀን ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው የተመለሱ መስለው ነበር። ከዚህም ግብ በኋላ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም በባህርዳር ተከላካዮች እና በግብ ጠባቂው ሀሪትሰን ሄሱ ድንቅ ብቃት ሲከሽፍባቸው ተስተውሏል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ባህርዳር ከነማ በ11ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በ9ነጥቦች 7ኛ ደረጃን ይዟል።
ሊጉን ወልዋሎ አ.ዩ. በ14 ነጥቦች ሲመራ መቐለ 70 እ. እና ፋሲል ከተማ በቅደም ተከተል በ13 እና በ12 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የኮከብ ግብ አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ7 ግቦች ቀዳሚ ሲሆን የባህርዳር ከነማው ፍፁም ዓለሙ በ6 እንዲሁም የመቐለ 70 እ. አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ5ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።