ከ2005 በኃላ ለ15ተኛ ጊዜ የተካሄደው ትግራይ ደርቢ በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት ተጠናቋል።ባለሜዳዎቹ ምዓም አናብስቶች አማኑኤል ገብረሚካኤል በ24ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ወሳኝ ሥስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።መቐለዎች በ4ኛው ሳምንት ሃዋሳ ላይ ሲዳማን ካሸነፈው ምርጥ 11 ሥስት ቅያሬዎችን ቢያድግልኝ ኤልያስ በላውረንስ ኤድዋርድ፣አሚን ነስሩን በዳንኤል ደምሱ፣አሸናፊ ሀፍቱን በዮናስ ገረመው ቀይረዋል።ወልዋሎዎች በበኩላቸው ከጅማ አባጅፋር ጋር በነበረው ጨዋታ በጉዳት ያልተሰለፋት ካርሎስ ዳምጠውና ፍቃዱ ደነቀ ገብተው ሰመረ ሀፍታይ ና ሚኪኤለ ለማ ወጥተዋል።
በሁለቱ ደጋፊዎች ደማቅ የሞዛይክ ትርኢት ታጅቦ የተጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ የመቐለዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ፣ተመጣጣኝ የግብ ሙከራ የታየበት ነበር።በመጀመርያ 20 ደቂቃዎች ላይ
መቐለዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ቢጫወቱም የወልዋሎን ጥብቅ መከላከልን መስበር ቸግርዋቸው ታይቷል።ወልዋሎዎች በአንፃሩ ኳሱን ለመቐለ በመተው ወደ ኃላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ቢሞክሩም በኢታሙና ኩሜይኒ የግል ጥረት አማካኝነት ከፈጠርዋቸው እድሎች ውጪ ይህ ሚባል እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።በተለይ በ19ኛው ደቂቃ ኢታሙና ኩሜይኒ ከግራ መስመር አሻምቶት ካርሎስ ዳምጠው በግምባሩ ገጭቶት ኦቮኖ በቀላሉ የያዘው እንዲሁም ሳሙኤል ዮውሃንስ አሻምቶት አሁንም ካርሎስ ጥሩ ተቆጣጥሮ በግራ እግሩ ቢመታውም ከግቡ አናት ወደ ላይ ወጥቷል።
- ማሰታውቂያ -
መሀል ላይ በላይነት ወስደው ‘ቀኝ መስመር ላይ አተኩረው በአጭር ቅብብል መጫወታቸውን የቀጠሉት መቐለ 70 እንደርታዎች በ24ኛው ደቂቃ በእማኑኤል ገብረሚካኤል ግብ ቀዳሚ ሆነዋል።አማኑኤል ከቀኝ መስመር በጠባብ አንግል ሳይጠበቅ የመታው ኳስ የአብዱላዚዝ ኬይታ መዘናጋት ታክሎበት ወልዋሎ መረብ ላይ ሊያርፍ ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ያለ መረጋጋት የታየባቸው ወልዋሎዎች አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ለማስቆጠር ከመስመር የሚሻሙ ኳሶችን ምርጫጨውን ቢያደርጉም በላውረንስ ኤድዋርድ እና አሌክስ ተሰማ ጥሩ ጥምረት ሲከሽፋ ነበር።በዚህም የመጀመርያው አጋማሽ በመቐለ 70 እንደርታ ሊጠናቀቅ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በመጠኑ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉበት፣መቐለዎችም ሁለቱም መስመር ላይ ትኩረት አድርገው የግብ እድሎችን መፍጠር የቻሉበት አንዲሁም በሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች መካከከል ሹክቻ የበዛበት ነበር።መሀል ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው ወልዋሎዎች በሁለተኛው አጋማሽ ዘሪሁን ብርሃኑን በፍቃዱ ደነቀ እንዲሁም ካርሎስ ዳምጠውን አውጥተው ሰመረ ሀፍታይን ቀይረው እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል።ሆኖም አሁንም ሚፈጥርዋቸው እድሎች ሀምሳ ሀምሳ መሆናቸው ተከትሎ በቀላሉ በፊሊፕ ኦቮኖ ና በመቐለ ተከላካይ ክፍል ሊመለሱ ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ መስመር ላይ ያተኮረ ቀጥተኛ አጨዋወትን የመረጡት መቐለዎች በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ፣አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ኦኪኪ ኦፎላቢ አማካኝነት እድሎችን አግኝተዋል።በተለይ ሙሉጌታ በወልዋሎ ፍፁም ቅጣት ሳጥን ውስጥ ያገኛቸው ሁለት እድሎች የመቐለን መሪነት ከፍ ማድረግ ሚችሉ ነበሩ።
በመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጠሩት ወልዋሎዎች ግራ ሰመረ ሀፍታይ ላይ በተሰራው ጥፋት ያገኙትን ቅጣት ምት ኢታሙና ኩሜይኒ አሻምቶት ፍፁም ቅጣት ሳጥን ውስጥ በቀኝ በኩል የነበረው ሳሙኤል ዮውሃንስ ወደ ውስጥ መልሶት በቅርብ የነበረው ሰመረ አገባው ሲባል ፊሊፕ ኦቮኖ አድኖበታል።በዚህም መሰረት በደማቅ የሁለቱም ቡድኖች ድጋፍ የታጀበው ትግራይ ደርቢ በምዓም አናብስቶች አሸናፊነት ተጠናቋል።ሜዳ ላይ ጥሩ የሆነ ስፖርታዊ ጨዋነት ና እግር ኳሳዊ የሆነ ፋክክር የታየበት ቢሆንም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከስታድየም ውጪ አንዳንድ ደጋፊዎች ያሳዩት የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ሊወገዝ የሚገባውና ለቀጣይ መስተካከል እንዳለበት እናሳስባለን።
ውጤቱን ተከትሎ ወልዋሎና መቐለ 70 እንደርታ በኩል 10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሊጉን በመምራት ላይ ይገኛሉ።