በ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሊግ ከመከላከያና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ ቀጥሎ በተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ከመመራት ተነስተው በጨዋታው ማገባደጃ ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2-1 አሸንፈዋል፡፡
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ለወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት እና ስጦታ በማበርከት ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር አዲግራት ላይ የነበራቸውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ኢትዬጵያ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ክልል ላይ በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ካስተናገዱበት የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች አቡበከርና ንታምቢን በማሳረፍ ትግስቱና ወንዲፍራውን ተክተው ሲገቡ እንግዳዎቹ ቢጫ ሰርጓጆቹ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት በሜዳቸው ከኢትዬ ኢለክትሪክ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የመጀመሪያ 11ተሰላፊዎች የ3 ተጨዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ዬሃንስ፡ሙሉዓለምና ኤፍሬምን በማስቀመጥ በረከት ፡ማናዬና ብርሃኑን ተክተው ገብተዋል፡፡
ልክ 11:35 ሲል በጀመረው የኢትዮጵያ ቡና እናወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታ ከመጀመሪያው የጨዋታውን ጅማሮ እስከ ጨዋታው ፍፃሜ ሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ለተመልካች አዝናኝና ማራኪ ነበር፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ኳስን መስርተው በአጭር ቅብብሎሽ ለመጫወት ሲሞክሩ በሁለቱም በኩል ወደ ግብ ቢደርሱም የጠራ የግብ ሙከራ ለማድረግ 18 ያህል ደቂቃዎችን መጠበቅ የግድ ሁኖባቸው ያመሹትና ግልፅ የግብ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ባለሜዳዎቹ በዚሁ ደቂቃ ሳኖሚ በቀኝ መስመር ሳጥኑ ውስጥ ሁኖ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በወልዋሎ ተከላካዮች ተጨርፎ በመውጣቱ የተገኘውን የማዕዘን ምት ወንድፍራው በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው የወልዋሎው ግብ ጠባቂ በረከት ሲያድንበት በዚሁ ደቂቃ ላይ ሌላ የማዕዘን ምት ቢያገኙም ቡናዎች አልተጠቀሙበትም፡፡
በተደጋጋሚ የጠራ የግብ ሙከራ ባይሆንም የተደረገባቸው ወልዋሎዎች ከ30 ደቂቃ በላይ አጠፋውን ለመመለስ ቢጠብቁም በቀኝ መስመር በኩል ሰብረው በመግባት ወደ ግብ ሲሞክሩት የቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ወደ ውጭ አውጥቶት የማዕዘን ምት ቢሆንም ቢጫ ሰርጓጆቹ ሳይጠቀሙበት ሲባክን በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ በ43ኛው ደቂቃ በአጥቂያቸው ኦዶንጎ አማካኝነት የጠራ የግብ ሙከራ ሳጥኑ ጠረዝ ላይ በረጂም ወደ ግብ የሞከረው ኳስ የቡናው ሀሪሰን በቆመበት የግቡ ቀኝ ቋሚ የመለሰበት የሚያስቆጭ ሙከራ የነበረ ሲሆን በዚሁ ወደ መልበሻ ክፍል ለእረፍት አምርተዋል፡፡
3 ግቦች የተቆጠሩበት የሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሜዳ ላይ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነበር፡፡ባለሜዳዎቹ ቡናዎች ኳስን መስርተው በአጭር ቅብብል ከመጫዎት ወጥተው ረጃጂም ኳሶችን ለአጥቂ ክፍላቸው ለማድረስ ሲጫዎቱ እንግዳዎቹ ወልዋሎዎች የመጀመሪያ ምርጫቸው ከጥብቅ መከላከያ ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር በመስመሮች በሚደረጉ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ሲጫዎቱ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾች ከትሪቡን ወደ ግብ ለመድረስ 4 ያህል ተጨዋቾችን አልፈው ለመግባት ባደረጉት እንቅስቃሴ ቡናዎች በሜዳቸው ግራ መስመር ከሳጥን ውጭ በሰሩት ጥፋት ወልዋሎዎች ያገኙትን ቅጣት ምት አፈወርቅ ወደ ግብ ሞክሮት በሀሪሰንና በተከላካዬች ተጨርፎ የተመለሰውን ኳስ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ሲያደርግ በስታዲየሙ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መደናገጥን ፈጥሯል፡፡
ከግቧ መቆጠር ከ3 ደቂቃዎች በሆላ ግብ አስቆጣሪው ኦዶንጎ በድጋሚ ኳስን ይዞ ወደ ቡና የግብ ክልል ለመግባት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የቡናው ወንድፍራው ጥፋት በመስራቱ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ባለሜዳዎቹ የበለጠ ጫና ውስጥ የገቡበት ቅፅበት ነበር፡፡34 ደቂቃዎችን የተጨዋቾች ቁጥር ብልጫ ተወስዶባቸው ያመሹት ቡናዎች ግብ ለማግኘት እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ሲያደርጉ እንግዳዎቹ ወልዋሎዎች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ በጥብቅ ሲከላከሉ በዋሉበት ምሽት በ87ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው አስቻለው ለቡድኑ የአቻነቷን ግብ ሲያስቆጥር በ8 ጭማሪ ደቂቃዎች 96ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ከወልዋሎ የግብ ክልል በግምት 30 ሜትር ያገኙትን ቅጣት ምት መሱድ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ በመግባት ቡናን እየታደገ ያለው ቁመተ ለግላጋው ፓፕቲስቴ ፋዬ ትናንትም ተቀይሮ በመግባት በግንባሩ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ክለቡ መታደግ ሲችል ያላቸውን የቁጥር ብልጫ በአግባቡ ያልተጠቀሙት ቢጫ ሰርጓጆቹ ዋጋ ከፍለው ወጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች የዛሬውን ድል ተከትሎ በ32 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 2ኛነት ከፍ ሲሉ ወልዋሎዋ አዲግራት ዩኒቨርስቲዎች 1ቀሪ ጨዋታ እያላቸው በ17ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ተቀምጠዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ-ዲዲዬ ጎሜዝ
በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ጥሩ አልተጫዎትም ነበር፡፡በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል፡፡ጫና ውስጥ ገብተን ነበር ግብ አስቆጥረንም አሸንፈናል፡፡በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ ደጋፊዎቻችንም ምርጦች ናቸው፡፡
☞የወልዋሎ አ/ዩው አሰልጣኝ-ፀጋዬ ኪ/ማርያም
በዛሬው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችን ማሸነፍ ይገባን ነበር፡፡እንዳለመታደላችን ግን በጨዋታ ተሸንፈናል ፡፡የተሸነፍነው በኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡በቀጣይ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን፡፡