የ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ ማጠቃለያ ሆኖ አዲስአበባ ላይ አመሻሹን የተካሄደው ጨዋታ በበርካታ ተመልካችና ማራኪ ግቦች ታጅቦ 2-2 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ወትሮውንም ሁለቱ የመዲናዋ ክለቦች ሲገናኙ በርካታ ተመልካች የሚታደምበት ጨዋታ ፡በርካታ ግቦችም ይቆጠሩበታል፡፡ዛሬም የተመለከትነው ይህንኑ ነበር በጨዋታው 4 ግቦች ከመረብ አርፈዋል፡፡ ተቀዛቅዞ በጀመረው ጨዋታ ጌታነህ ከበደ በቅጣት ምት ወደ ግብ የመታውን ኳስ የቡና ተከላካዮች ከግባቸው ለማራቅ በሞከሩበት ሂደት ኳስ ተጨርፎ የደረሰው ስዩም ተስፋዬ ኳስን ከመረብ ጋር አገናኝቶ ቡድኑን በጊዜ ቀዳሚ አድርጓል፡፡ከጎሏ መቆጠር በሇላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር ስንመለከት የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል ጥሩ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን መስርተው በመስመሮች በኩል የበለጠ የማጥቃት አማራጭ አድርገው የግብ ዕድል ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ፡ደደቢቶች ለጌታነህ ከበደ በረጂሙ በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች የግብ ዕድል ለማግኘት ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም ነበር፡፡እምብዛም ኢላማውን ባልጠበቀ እና የጠራ የግብ ሙከራ ያልታጀበው የመጀመሪያ ጨዋታ አጋማሽ በመስመርና በመሀል ሜዳው በሚንሸራሸሩ ኳሶች የቀጠለው ጨዋታ በ45+1 ደቂቃ አስራት መገርሳ ፡ኤሊያስ ማሞ ላይ በሰራው ጥፋት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ሳሙኤል ሳኖሚ ወደ ግብነት በመለወጥ ቡናን ወደ አቻነት መልሶ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ለእረፍት ወጥተዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን 2 ወሳኝ ግቦችም የተመለከትነው በዚሁ አጋማሽ ነበር፡፡በ47ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል ሳሙኤል ሳኖሚ ሰብሮ ገብቶ ጥሩ የግብ ሙከራ ሲያደርግ፡ በደደቢት በኩል በ49ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከቡና የግብ ሳጥን ውጭ ከርቀት አክሮ በመታው ኳስ ሌላ ጎል ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ፡ ቡናዎች በ66ኛው ደቂቃ በአቡበከር ነስሩ አማካኝነት ለግብ የተቃረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡
በ71ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ለማጥቃት በሄዱበት ቅፅበት ከሇላ ትተውት የሄዱትን የሜዳ ክፍል በመጠቀም የጌታነህ ድንቅ ችሎታና አጨራረስ ተጨምሮበት ኳስና መረብን አገናኝቶ ቡድኑ በድጋሚ መሪ የሆነበትን ግብ ሲያስቆጥር ፡ኩዌኩ አንዶህ ፡አቡበከር ነስሩ ላይ በሰራው ጥፋት ከሜዳ በቀይ ካርድ ወጥቷል፡፡ከዚህ ደቂቃ በሇላ ጨዋታው ለደደቢት እጂጉን ፈታኝ ነበር፡፡ያገኙትን የተጨዋቾች ብልጫ በአግባቡ ለመጠቀም የሞከሩት ቡናዎች ቢዘገይም በ89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ተስፈኛው ታዳጊ ቃልኪዳን ዘላለም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ከሽንፈት ታድጓል፡፡ ጨዋታው በዚሁ 2-2 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁ ቡና ከመሪዎቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠብበት ዕድል ሲባክን፡ደደቢት በበኩሉ ከዋንጫው ፉክክር የወጣበት ውጤት ተመዝግቧል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞ኢትዮጵያ ቡና – ዲዲዮ ጎሜዝ
ጨዋታውን ተቆጣጥረን እንደመጫዎታችን ማሸነፍ ይገባን ነበር፡፡ከተጋጣሚያችን እኛ የተሻልን ነበርን፡፡አሁን ካለንበት ደረጃና ካስመዘገብነው ነጥብ አንፃር ቀሪ ጫዋታዎችን አሸንፈን የሚሆነውን አብረን እናያለን፡፡
☞ደደቢት – ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ
በጨዋታው ሁለታችንም ጥሩ ተጫውተናል፡፡ፍክክሩም ተመጣጣኝ ነበር፡፡የሜዳው ምቹ አለመሆን ያገኘናቸውን የግብ ዕድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ተቸግረን ነበር፡፡ተጨዋቾቻችን ለማሸነፍ የነበራቸው ፍላጎት እና ተነሳሽነት ጥሩ ነበር፡፡