በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ
ኢትዮጵያ ቡና ከወልዲያ ተገናኝተው ባለ ሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ኤልያስ ማሞ ባስቆጠራቸው 2 ግቦች 2-0በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።
በጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ ለማየት የወሰደው ጊዜ 48 ሰከንዶች ብቻ ነበር። በዚህ ሰዓት ኤልያስ ማሞ የመታውን ኳስ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቤሌንጌ ኦኖህ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የወልዲያው ፍፁም ገ/ማርያም ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪትሰን አውጥቶታል። በተደጋጋሚ ወደ ወልዲያ ግብ ክልል መድረስ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ እነዲሁም 15ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማ የሞከሯቸውን ኳሶች በዕለቱ ድንቅ የነበረው የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቤሌንጌ ኦኖህ በግሩም ሁኔታ አድኖባቸዋል። በዚህ ጨዋታ 12ኛ ደቂቃ ላይ በተለምዶ ሚስማር ተራ ተብሎ በሚጠራው ቦታ እና በ ዳፍ ትራክ በኩል የነበሩ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የክለባቸውን ወቅታዊ ሁኔታ በመቃወም ከሜዳ ሊወጡ ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ሆኖም በፀጥታ ሀይሎች ከሜዳ እንዳይወጡ ተደርገዋል። ጨዋታው ቀጥሎ 25ኛው ደቂቃ ላይ የወልዲያው አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ(አቤጋ) በመቀስ ምት እንዲሁም 27ኛው ደቂቃ ላይ በግንባር በመግጨት የሞከራቸው ኳሶች ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥተዋል። ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ34ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ የሚያስቆጭ ኳስ አምልጧቸዋል። በረከት ይሳቅ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ አግኝቶ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያወጣው አስናቀ ሞገስ በድጋሚ የሞከረውን ኳስ ተከላካዩ ቢያድግልኝ ኤልያስ ከመስመር ላይ በግሩም ሁኔታ አውጥቶታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2ደቂቃዎች ሲቀሩት አስቻለው ግርማ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደግብ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። ይህ ሙከራም በመጀመሪያው አጋማሽ የተደረገ የመጨረሻ ሙከራ ሆኗል።
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተቀዛቅዞ የቀጠለው የሁለቱ ጨዋታ የግብ ሙከራ ለማስተናገድ 10ደቂቃዎች አስፈልጎት ነበር። 55ኛው ደቂቃ ላይ የወልዲያው አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ(አቤጋ) በግንባሩ በመግጨት የሞከረውን ኳስ የቡናው ግብ ጠባቂ በቀላሉ ይዞታል። 63ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ወጣት አጥቂ አቡበከር ናስር ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ኤልያስ ማሞ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ፍፁም ቅጣት ምቱ ከመቆጠሩ በፊት የወልዲያ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተነሳ አምባጓሮ የወልዲያው አማረ በቀለ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል። ከ7 ደቂቃዎች በኋላ 70ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሌላው የወልዲያ አማካይ ብሩክ ቃልቦሬ ከኳስ ውጪ የቡናን ተጫዋች መማታቱን ተከትሎ እሱም በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ከዚህ በኋላም ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ቡናዎች ሙሉ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ የመታው ቅጣት ምት የግቡን አግዳሚ ለትሞ የመለሰበት እንዲሁም ከ 2ደቂቃዎች በኋላ አስቻለው ግርማ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝተው የሞከረው ኳስ በተከላካይ ተጨርፎ ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩት ኤልያስ ማሞ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ቡናው አዲሱ አሰልጣኝ ዲዲዬር ጎሜዝ
“ለእኔ እንደ አጀማመር ጥሩ አጀማመር ነው። ዛሬ የማሸነፍ ግዴታ ነበረብን። ብዙ የማግባት እድሎችን ፈጥረናል። ጥሩም ተጫውተናል፤ ግን አሁንም ቡድኑን ለማሻሻል ብዙ ስራ ይጠበቅብናል። በዛሬው ጨዋታ ተደስቻለሁ፤ በልጆቼም ኮርቻለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ዛሬ ዋናው ነገር 3ነጥብ ነበር እሱንም አሳክተናል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
- ማሰታውቂያ -
የወልዲያው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው
“ተጋጣሚያችን ጫና ውስጥ የነበረ ቡድን ስለሆነ እኛም ጫና ፈጥረን ለመጫወት ሞክረን ነበር ነገር ግን የዕለቱ ኮከብ በነበረው በዳኛው አማካኝነት ጨዋታው ተቀይሯል። ሁለቱም ውሳኔዎች ተገቢ አልነበሩም። ለመጀመሪያ ጊዜ ልቤ ዳኛን ጠረጠረ።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።