ወላይታ ዲቻ በካፍ ኮንፌደሬሺን ካፕ ዛማሌክን ባሸነፈበት ማግስት ለግብፅ ጉዞው የሚሆነውን ስንቅ በሜዳው ወልዲያ ከተማን 2ለ0 በማሸነፍ ሰንቋል፡፡
በኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ማጠቃለያ ብቸኛ ቀሪ ተስተካካይ መርሃ ግብር ጨዋታ ዛሬ በሶዶ ስታዲዬም ወላይታ ዲቻ በሜዳው ወልዲያ ከተማን በማሸነፍ ደረጃውን ያሻሻለበትን ውጤት ባስመዘገበበት ጨዋታ የመጀመሪያ ዙር ተጠናቋል፡፡
በይደር ተይዞ የቆየው የወላይታ ዲቻና ወልዲያ ከተማ ጨዋታ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ፡ወልዲያ ከተማ በሊጉ 7ኛ ደረጃን በመያዝ የመጀመሪያውን ዙር የሚያጠናቅቅበትን ዕድል ሲያመክን፡ባለሜዳዎቹ ዲቻዎች በሰንጠረዡ ወደ ደረጃ መዳቢነት ከፍ ያሉበትን ውጤት ከማስመዝገባቸውም ባሻገር በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመልስ ጨዋታ ብርታት የሚሆናቸውን ትልቅ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ስንቅ ሰንቀዋል፡፡
ለዛሬው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ወላይታ ዲቻዎች በሊጉ ከሜዳቸው ውጭ ጅማ ስታዲዬም በጅማ አባጅፋር 2ለ1ተሸንፈው ፡በካፍ ኮንፌደሬሺን ካፕ የግብፁን ዛማሌክ በሜዳቸው 2ለ1አሸንፈው ሲቀርቡ የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች በነበሩ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ሲገቡ፡እንግዳዎቹ ወልዲያ ከተማዎች በተመሳሳይ በሜዳቸው የሊጉን መሪ ደደቢት 1ለ0 አሸንፈው ለጨዋታው ሲቀርቡ ፡ደደቢትን ሲያሸንፉ የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች ለውጥ ሳያደርጉ አስገብተዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ዲቻዎች ኳስን ተቆጣጥረው በመጫዎት የተሻሉ ሁነው ባመሹበት ጨዋታ እንግዳዎቹ ወልዲያዎች ባንፃሩ መከላከልን መርጠው ወደ ግብ ክልላቸው ተጠግተው አምሺተዋል፡፡ባለሜዳዎቹ የጦና ንቦቹ ዲቻዎች ኳስን መስርተው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ሳጥን በመግባት በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርጉ በተለይም ጃኮ አረፋትና በዛብህ መለዬ ያመከኗቸው ኳሶች ለግብ የተቃረቡ ነበሩ፡፡
እንግዳዎቹ ወልዲያ ከተማዎች በበኩላቸው ከግብ ክልላቸው ሳይርቁ በረጅሙ ለአንዷለም ንጉሴ /አቤጋ/በሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢጫዎቱም ግልፅ የሚባል የማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
2 ግቦች በተስተናገዱበት እና ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ በተመለከትንበት የሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጎል የማግባት ፍላጎት ስንመለከት በዲቻ በኩል በአጫጭርና በመስመር በኩል የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በወልዲያ በኩል ከመጀመሪያ አጋማሽ ባልተለዬ መልኩ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የግብ ዕድል ለማግኘት ተጫውተዋል፡፡
ባለሜዳዎቹ የሇላ ሇላ ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ ዘላለምን ቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው በአምረላ ደልታታ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል፡፡ከጎሏ መቆጠር በሇላ እንግዳዎቹ የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ቢጫዎቱም ሳይሳካላቸው የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስር ፊሺካ ድምፅ በሚጠበቅበት ሰዓት በወላይታ ዲቻው ጃኮ አረፋት ድንቅ አጨራረስ ሌላ ግብ አስተናግደው ከሜዳቸው ውጭ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበትን ዕድል አምክነው የመጀመሪያውን ዙር የሊግ ጨዋታ በ2ለ0 ሽንፈት አጠናቀዋል፡፡
ባለሜዳዎቹ ዲቻዎች በሜዳቸው ወልዲያ ከተማን 2ለ0 ማሸነፋቸውን ተከትሎ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ውጤት አስመዝግበው የመጀመሪያው ዙር የሊግ ጨዋታ ሲያጠናቅቁ የፊታችን ሀሙስ ለካፍ ኮንፌደሬሺን ጨዋታ የግብፁን ዛማሌክ ለመግጠም ወደ ካይሮ ያቀናሉ፡፡
ባለሜዳዎቹ የጦና ንቦች በደረጃ ሰንጠረዡ በ15 ጨዋታ በ19 ነጥብና ያለምንም ግብ 8ደረጃ በመሆን የመጀመሪያውን ዙር ሲያጠናቅቁ፡ ወልዲያዎች በደረጃ ሰንጠረዡ በ15 ጨዋታ በ18 ነጥብ በ2 የግብ ዕዳ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዘነበ ፍስሀ—ወላይታ ድቻ
“በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጋጣሚያችን ይዞ የገባው የጨዋታ አካሄድ እንደፈለግነው እንዳንቀሳቀስ አድርጐናል ።በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ይህን በመመልከት የተጨዋችና የጨዋታ ስልት በመቀየራችን ማሸነፍ ችለናል።በውጤቱም ደስተኛ ነኝ።የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፋችን ለግብፁ ጨዋታ ትልቅ ስንቅ ይሆነናል፡፡አሁን የምናስበው ስለ ቀጣዩ የዛማሌክ የመልስ ጨዋታ ነው፡፡”
ዘማርያም ወ/ገዬርጊስ -ወልዲያ
“በጨዋታው የሜዳው ምቹ አለመሆን ረጃጅም ኳሶችን ለመጫዎት ተገደናል፡፡ከዚህም በላይ ያገኘናቸውን አጋጣሚ አለመጠቀማችንም ዋጋ አስከፍሎናል፤ በሚቀጥለው ሁለተኛው ዙር ተጠናክረን እንመጣለን፡፡”