እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 ኒጀር ለምታስተናግደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቡሩንዲ አቻው በሜዳው የ2-0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ እጅግ ተዳክሞ የታየው ብሔራዊ ቡድኑ እንደቡድን አንድም የሚያመረቃ እንቅስቃሴም ሆነ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳያደርግ ወጥቷል።
በጨዋታው ብሩንዲዎች በአካል ብቃትም ሆነ በጨዋታ ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ የሚሰለጥኑት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን የተጋጣሚአቸውን ረጃጅም ኳሶች እና ተክለ ሰውነት መቋቋም አቅቷቸው ታይተዋል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማግኘት የፈጀበት የ3ደቂቃዎች እድሜ ብቻ ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ ከኢትዮጵያ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ሳጥን ውጪ የተገኘውን ኳስ የቡሩንዲው አጥቂ ጁማ መሐመድ በቀጥታ ወደግብ በመምታት ግሩም ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዚህች ግብ መቆጠር የግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ደካማ አቋቋም እና የጊዜ አጠባበቅ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።
በዚህች ግብ መቆጠር ምክንያት መደናገጥ ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተጫዋቾች ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም ስኬታማ መሆን አልቻሉም። ከመጀመሪያው ግብ መቆጠር 19ደቂቃዎች በኋላ የተመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ሲተፋው የቡሩንዲው ሻካ ቢቴንዩኒ አስቆጥሮ የቡሩንዲ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጣፋጭ ውጤት ይዞ ወደ ሀገሩ ሊመለስ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ከኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በጥሩ ብቃት ሊጠቀሱ የሚችሉ 3 ወይም 4 ተጫዋቾች ብቻ ነበሩ እንጂ ቡድኑ እንደ ቡድን ሊነሳ የሚችል ጥንቃሬ አልነበረውም። ተስፋ ከተጣለባቸው እና ሊጠቀሱ ከሚችሉ ተጫዋቾች መሀከል የኢትዮጵያ ቡናዎቹ አቡበከር ነስሩ እና ሚኪያስ መኮንን፣ የደደቢቱ አቤል እንዳለ እና የቅ/ጊዮርጊሱ የግራ ተከላካይ ሳሙኤል ተስፋዬ በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ብቃታቸውን ማሳየት ችለዋል።
የመልሱ ጨዋታ ከሶስት ሳምንታት በኃላ ቡሩንዲ ንጎዚ ላይ የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ የማጣሪያ ዙር ለማለፍ በብሩንዲ ሜዳ ከሁለት በላይ ግቦችን አስቆጥሮ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብታለች፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
አጥናፉ ዓለሙ — ኢትዮጵያ
“ውድድሩ በጣም ከባድ ነው፤ ልጆቹ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ለውጤቱ ግን ሀላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ። ከዚህም በኋላ ማድረግ የምንችለው ጠንክረን መስራት ነው። በአቅም እና በአካል ብቃት ረገድ ተበልጠናል፤ ይሄ ደግሞ ለውጤቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።”
ጆስሊን ቢፉቡሳ — ቡሩንዲ
“ጨዋታው ከባድ ነበር፤ የኢትዮጵያ ቡድኖች አጫጭር ኳስ እንደሚጫወቱ እናውቃለን፤ የአየር ንብረቱም ከብዶን ነበር፤ በአጠቃላይ ግን ጨዋታው ከባድ ነበር።”