በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ደደቢት ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ በደደቢት 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በቀዘቀዘ አየር የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንደ አየር ንብረቱ ቀዝቅዞ ነበር የተጀመረው። ደካማ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ይሄ ነው የሚባል ጨዋታም የግብ ሙከራም ሳይታይበት ተጠናቋል። በጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ በኀይሉ ተሻገር የደደቢት ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ሞክሮ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ይዞታል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችልም የሜዳው የመጨረሻ ክፍል ላይ ግን ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችል ጨዋታውን ለመሸነፍ ተገዷል። በደደቢት በኩል አጥቂው ጌታነህ ከበደ 36ኛው ደቂቃ ላይ በግራ እግሩ አክርሮ መቶ በረኛው በግሩም ሁኔታ ያወጣበት ኳስና የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ የሞከረው ቅጣት ምት በግቡ አናት ላይ የወጣበት ኳስ በብቸኝነት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሽለው መቅረብ የቻሉት ደደቢቶች የመጀመሪያዉን ጎል ለማግኘት የፈጀባቸው 5ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ። 50ኛው ደቂቃ ላይ በዘንድሮው የውድድር አመት ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ አቤል ያለው ግብ አስቆጥሮ ደደቢትን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ይህች ግብ ለአቤል በውድድር አመቱ 5ኛው ሆና ተመዝግባለች። ከ3 ደቂቃዎች በኋላ የአምናው እና የምንግዜውም የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ጌታነህ ከበደ 2ኛ ግብ በማስቆጠር ውጤቱን አስተማማኝ ማድረግ የቻሉ መስሎ ነበር። ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ ኢትዮ-ኤሌክትሪኮች በሙሉ አቅም ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ 63ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ ሆኖ ያመሸው በኀይሉ ተሻገር የመታውን ኳስ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ በግሩም ብቃት አውጥቶበታል። ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ሌላ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ካሉሻ አልሐሰን ከጥላሁን ወልዴ የተቀበለውን ኳስ አስቆጥሮ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሎ ነበር።
ከግቡ መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ኢትዮ-ኤሌክትሪኮች 68ኛው ደቂቃ አወት ገ/ሚካኤል በቀኝ ክንፍ ይዞት የገባውን ኳስ አሻምቶት ሄኖክ ካሳሁን ደርሶ መቶት በረኛው ይዞታል። 79ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግርማ በቀለ የደደቢት ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያገኘውን ኳስ መቶት ተከላካዮቹ ተረባርበው አውጥተውታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5ደቂቃዎች ሲቀሩት በመልሶ ማጥቃት ሄደው አቤል ያለው በግሩም ሁኔታ ተጫውቶ ያቀበለውን ኳስ አጥቂው ጌታነህ ከበደ በሚያስደንቅ አጨራረስ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ ሶስተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው በደደቢት 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኀላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የደደቢት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ
“ተጋጣሚአችን ከእረፍት ስለሆነ የመጡት ጉልበት ሰብስበው በመጀመሪያው አጋማሽ ተጭነውን ተጫውተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ተሻሽለን መቅረብ ችለናል። አጥቂዎቼ ጥሩ ብቃት አሳይተው ማሸነፍ ችለናል። በአጠቃላይ በልጆቼ በጣም ደስተኛ ነኝ።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዬ በበኩላቸው
“የማይችል ቡድን አሸነፈ፤ በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ(ደደቢት) ተመልካቾች ነበሩ። በህይወቴ እንደዚህ የወረደ ቡድን አላየሁም።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በመቀጠልም ስለ ስንብታቸው ተጠይቀው “አሁን ጊዜው ነው፣ በደብዳቤ የደረሰኝ ነገር የለም እኔም እንደ እናንተ ጭምጭምታ ነው የሰማሁት። ክለቡ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የ4 ጨዋታዎች እድሜ ሰጥቶኝ ነበር፤ አሁን ጊዜው ነው። ኢትዮ-ኤሌክትሪክን አመሰግናለሁ። መልካሙን ሁሉ እመኝላቸዋለሁ።” በማለት አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።